ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ ከተካሄዱ ግጭቶች ሁሉ የኢትዮጵያው ጦርነት በርካቶች የሞቱበት ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በዓለም ዙሪያ ከተካሄዱ ግጭቶች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ሞት መመዝገቡን አንድ አዲስ የወጣ ሪፖርት አመለከተ።
በዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት እና ሰላም ተቋም (አይኢፒ) ይፋ በተደረገው የዓለም ሰላም ጠቋሚ ጥናት መሠረት፣ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ እና በዩክሬን ውስጥ በተካሄዱ ጦርነቶች ምክንያት የሰዎች ሞት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
ሪፖርቱ እንዳለው ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 2022 ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
ይህ ጦርነት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተደረሰ የሰላም ስምምነት ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ያበቃ ሲሆን፣ ሪፖርቱ ያመለከተው በአንድ ዓመት ውስጥ የደረሰውን ጉዳት ብቻ ነው።
ነገር ግን በሁለት ዓመቱ ውስጥ አስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በእርስ በርስ ጦርነቱ ሳይሞቱበት እንዳልቀሩ ሲነገር ቆይቷል።
የጥናት ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በተጠቀሰው ዓመት ውስጥ ከፍተኛ ሰብአዊ እልቂትን ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአንድ ዓመት ውስጥ ከ104 ሺህ በላይ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ቀዳሚው ነው ብሏል።
በመቀጠል ደግሞ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ያገኘው እና ባለፈው የካቲት ወር አንድ ዓመት የሞላው የዩክሬን ጦርነት ቢያንስ 82 ሺህ ሰዎች ለሞት እንደተዳረጉበት ሪፖርቱ አመልክቷል።
በእነዚህ ሁለት ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ምክንያትም አስካሁን በጥናቱ ከፍተኛ ሰው አልቆበታል ተብሎ ከተመዘገበው የአውሮፓውያኑ የ1994 የሩዋንዳው ዘር ጭፍጨፋ ወዲህ፣ ያለፈውን ዓመት በርካታ ሰዎች በጦርነት ያለቁበት ዓመት ነው ብሎታል ተቋሙ።
በዚህም ሳቢያ በትግራዩ ጦርነት እንዲሁም በዩክሬን እና በሩሲያ ጦርነት ሰበብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር የአውሮፓውያኑ 2022 ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ እንዲጨምር እንዳደረገው ጥናቱ ገልጿል።
በዚህ ሪፖርት ላይ የቀረበው በግጭቶች ሰበብ ያጋጠመው የሞት አሃዝ የስዊዲኑ አፕሳላ ዩኒቨርስቲ በሠራው ምርምር መሠረት ሲሆን፣ ይህም ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተደራጁ ግጭቶች 238 ሺህ ሰዎች ሕይወት በማለፉ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የሟቾች ቁጥር በ96 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል ብሏል።
በኢትዮጵያ እና በዩክሬን ውስጥ በተካሄዱት ጦርነቶች ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በዓለም ዙሪያ ባለፈው ዓመት በተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ ከፍተኛውን የሞት ቁጥር የሚሸፍኑ ናቸው።
በዚህም ሳቢያ ሁለቱ ጦርነቶች ከቀዝቃዘው ጦርነት ወዲህ መንግሥታት የተሳተፉባቸው ደም አፋሳሽ ጦርነቶች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል።
በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ሲካሄድ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ልክ በሁለት ዓመቱ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተደረሰ ግጭት የማቆም ስምምነት ተቋጭቷል።
በጦርነቱ ውስጥ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት ሠራዊት፣ የክልል ኃይሎች፣ የህወሓት ተዋጊዎች እና የኤርትራ ጦር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል አሰማርተው ተዋግተውበታል።
በዚህ የሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ምን ያህል ሰው እንዳለቀ በይፋ የሚታወቅ አሃዝ ባይኖርም፣ የተለያዩ ወገኖች ቁጥሩን ከግማሽ አስከ አንድ ሚሊዮን ያደርሱታል።












