ብርቱካን ሚደቅሳ ከምርጫ ቦርድ ኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው እንደሚለቁ አሳወቁ

ብርቱካን ሚደቅሳ

የፎቶው ባለመብት, nebe/fb

የምስሉ መግለጫ, ብርቱካን ሚደቅሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በራሳቸው ፈቃድ ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁ አሳወቁ።

ብርቱካን ሚደቅሳ በተረጋገጠው የግል የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ይፋ እንዳደረጉት ከነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ሰብሳቢነት ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ሰኔ 05/2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ምክር ቤት አፈጉባኤ አሳውቀዋል።

በታኅሣሥ 2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በመሆን ሥራውን የተረከቡት ብርቱካን፣ ከአራት ዓመታት በላይ በኃላፊነቱ ላይ ቆይተው በቦርዱ ውስጥ ለውጦች እንዲካሄዱ አድርገዋል።

ብርቱካን ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን በተመለከተ ይፋ ባደረጉበት መልዕክታቸው ላይ በሰብሳቢነታቸው ዘመን ሦስት ሕዝበ ውሳኔዎችን እና አገራዊ ምርጫን ማካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።

“የተሰጡኝን ኃላፊነቶች ሕጋዊነት፣ ፍትሃዊነት እና ቅንነትን በተከተለ ሁኔታ ለማከናወን ስጥር ቆይቻለሁ” በማለት ጤናቸውን በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት ስለሚያስፈልጋቸው ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ብርቱካን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢነታቸውን ከነሐሴ መጀመሪያ አንስቶ ለመልቀቅ በመወሰናቸው በሚቀጥሉት አርባ ቀናት “ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን የማጠናቀቅ እና አስተዳደራዊ ሽግግር የመፈፀም ኃላፊነቶችን የምወጣበት ይሆናል” ብለዋል።

ጨምረውም ብርሔራዊ ምርጫ ቦርድን በሰብሳቢነት ለመምራት በዕጩነት ያቀረቧቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን እና ኃላፊነቱን ለሰጣቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የቀድሞዋ ዳኛ እና ፖለቲከኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ወደ ኢትጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢነት ኃላፊነት የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በወሰዷቸው የለውጥ እርምጃዎች አማካይነት ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በምርጫ ቦርድ የኃላፊነት ዘመናቸው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አንድ ዓመት የዘገየውን ብሔራዊ ምርጫን እንዲሁም የደቡብ ክልልን ወደ ሦስት ክልልነት የከፈሉትን ሦስት ሕዝበ ውሳኔዎችን በመምራት አካሂደዋል።

እንዲዘገይ በተደረገው ምርጫ ሰበብ በገዢው ፓርቲ እና በህወሓት መካከል ከባድ ውዝግብ ተከስቶ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት አንድ ምክንያት የሆነ የተናጠል ምርጫ በትግራይ ክልል ውስጥ መካሄዱ ይታወሳል።

ጦርነቱን ተከትሎም በአመጽ ተግባር ላይ ተሳትፏል የተባለው ህወሓት ከሕጋዊ ፓርቲነት በምርጫ ቦርድ የተሰረዘ ሲሆን፣ የሰላም ስምምነት ከተደረሰም በኋላ ህወሓት ዕውቅናው እንዲመለስለት ያቀረበው ጥያቄ በቦርዱ ተቀባይነት አላገኘም።

ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊ አስተዳደር ስር በምትገኘው ትግራይ ውስጥ አስቸኳይ ምርጫ ለማካሄድ አመቺ ሁኔታ እንደሌለ ገልጸዋል።

የጤና ጉዳይን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነታቸውን ለመልቀቅ ምክንያት እንደሆናቸው ያመለከቱት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በዳኝነት ዘመናቸው የቀድሞው የህወሓት ባለሥልጣን የነበሩትን አቶ ስዬ አብረሃን በተመለከተ ያሳለፉት የፍርድ ውሳኔ ዝናን እንዳስገኘላቸው ይታወሳል።

ብርቱካን ሚደቅሳ በአወዛጋቢው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባል የነበሩ ሲሆን፣ በፓርቲው ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ነበሩ።

የምርጫውን ውዝግብ ተከትሎ መንግሥት የተቃዋሚ አመራሮችን እና ጋዜጠኞችን ለእስር በዳረገበት ጊዜ ብርቱካንም በእስር ላይ ቆይተው ነበር።

ቅንጅት ከፈረሰ በኋላም አንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የተሰኘ ፓርቲን ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመመሥረት በፖለቲካው ውስጥ ለመቆየት የሞከሩ ቢሆንም ብዙም ሳይቆዩ ድጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።

ብርቱካን በአገሪቱ ውስጥ የነበረው የተቃውሞ ፖለቲካ መድረክ እየጠበበ በመምጣቱ፣ በገዢው የኢህአዴግ መንግሥት በገጠማቸው ጫና እና እስር ወደ አሜሪካ በስደት ሄደው በትምህርት ላይ ለዓመታት ከቆዩ በኋላ ነበር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ የተሾሙት።