ወላይታ ከሌሎች ዞኖች እና ወረዳዎች ጋር በክልል እንዲደራጅ የሚያስችል ድምጽ ተሰጠ

የፎቶው ባለመብት, NEBE
የወላይታ ዞንን ጨምሮ ሌሎች 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች በጋራ በአንድ ክልል ለመመሥረት የቀረበው ሕዝበ ውሳኔ ሕዝባዊ ይሁታን አገኘ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ ሰኔ 20/2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው እና የተረጋገጠ ነው ባለው የሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት ኢትዮጵያ አንድ አዲስ ተጨማሪ ክልል ይኖራታል።
በዚህም መሠረት ኮንሶ፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ እና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ እና ዲራሼ ወረዳዎች በአንድ ክልል መደራጀትን በመደገፍ በሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ተሰጥቷል።
በዚህ በወላይታ ዞን በተሰጠው ድምጽ 752 ሺህ 44 ሰዎች የስድስቱ ዞኖች (ኮንሶ፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዲኦ፣ ጎፋ) እና የአምስቱ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) በአንድ የጋራ ክልል መደራጀትን ደግፈዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 41 ሺህ 531 ሰዎች ደግሞ የ6ቱ ዞኖች የ5ቱ ወረዳዎችን በአንድ የጋራ ክልል መደራጀትን አልደግፍም ብለው ድምጽ ሰጥተዋል።
ይህ ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ የተደረገው በወላይታ ዞን ለሁለተኛ ጊዜ ሕዝበ ውሳኔ ከተካሄደ በኋላ ነው።
ቀደም ብሎ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ በሂደቱ ባጋጠመ “የሕግ ጥሰት” ምክንያት ድምጽ መስጠቱ በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።
ለዚህም ምርጫ ቦርድ “የተመዘገቡ ድምጽ ሰጪዎች ቁጥር ተዓማኒነት የጎደለው ” መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን፣ “የሕግ ጥሰቶቹ ከመፈፀማቸው በፊት ሕጋዊ እርምጃ ባለመወሰዱ ድጋሚ ድምጽ መስጠት ማካሄድ ማስፈለጉን” ገልጾ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄያቸውን በይፋ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
በዚህ ጥያቄ መሠረትም ምላሽ ያገኙት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለብቻቸው በክልልነት መደራጀት ችለዋል።
ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለብቻቸው በክልልነት ከተዋቀሩ በኋላም የቀሩትን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ልዩ ዞኖች እና ወረዳዎችን መልሶ ለማዋቀር እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር።
የወላይታ ዞንም ከዚህ ቀደም በተናጠል የክልልነት ጥያቄ ካቀረቡ የደቡብ ክልል ዞኖች አንዱ ነው።
ይህንን ጥያቄ ሲመሩ የነበሩ ከፍተኛ የዞኑ አስተዳዳሪዎች እና ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።
በዞኑ ውስጥ ከተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ ከ16 ሰዎች በላይ መሞታቸው ይታወሳል።
በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ በዞኑ ምክር ቤት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ለክልል ምክር ቤት፣ ከዚያም ለፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄው ቀርቦ ነበር።
በመጨረሻም ዞኑ በክላስተር ከሌሎች ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ጋር ተሰባስቦ እንዲደራጅ በፌደሬሽን ምክር ቤት ተወስኖ ነበር። ይህንንም ለማስፈፀም ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ተግባራትን ሲያካሂድ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ አካባቢዎች በክልልነት መደራጀታቸው “ራስን በራስ የማስተዳዳር ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው” ይህም ልማትን ለማፋጠን እና ማኅበረሰቡን በቅርበት ለማገልገል ወሳኝ ነው ሲሉ የሚደግፉት ቢኖሩም፣ ሌሎች ግን አገሪቷን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ እና የሚበታትን ነው ሲሉ ይተቹታል።












