ወላይታ ፡ በወላይታው አለመረጋጋት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 16 መድረሱ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Wolaita Zone chief Administrator FB
በወላይታ ዞን እሁድ ዕለት በዞኑ ውስጥ ያሉ ከተፍተኛ አስተዳዳሪዎችና ሌሎች ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አለመረጋጋት እስከ ትናንት ድረስ 16 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ።
ይህንንም በተመለከተ ከተለያዩ ሆስፒታሎች መረጃዎችን ማጠናቀራቸውን የሚናገሩት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል (ኦቶና ሆስፒታል) መምህርና የአጥንት ክፍል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መብራቱ ጪሻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዶ/ር መብራቱ መረጃዎቹን ከሚያስተምሩበትና ከሚሰሩበት ኦቶና ሆስፒታል፣ ከወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል፣ ቦዲቲ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ቦዲቲ ጤና ጣብያ እንዲሁም ከነዋሪዎች ማጠናቀራቸውን በመግለጽ፤ በዞኑ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 16 መድረሱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ዶ/ር መብራቱ ጪሻ እንደሚሉት በነበረው አለመረጋጋት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሕክምና ተቋማት የመጡት 49 ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰው በጥይት ተመትተው ነው ይላሉ።
ከእሁድ ማታ ጀምሮ በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታል ከመጡት መካከል ዘጠኝ ሰዎች ሞተዋል። በተጨማሪም 30 ሰዎች ሕክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ሦስቱ ደግሞ በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በጽኑ ሕክምና ክፍል መሆናቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በሆስፒታል ከሞቱት በተጨማሪም ወደ ሆስፒታል ሳይመጡ በውጭ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች እንዳሉም ዶክተሩ ያስረዳሉ።
ከእሁድ ማታ ጀምሮ በነበረው አለመረጋጋት ግጭቱ በበረታባት በቦዲቲ ከተማ የሞቱት ሰባት መሆናቸውን የገለፁት ዶ/ር መብራቱ፤ ወደ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በአጠቃላይ 21 ሰዎች ተጎድተው የመጡ ሲሆን ሆስፒታሉ እንደደረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሁለት መሆኑን ተናግረዋል።
በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በአሁኑ ሰዓት ሦስት ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል እንደሚገኙ የሚናገሩት ዶ/ር መብራቱ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ክፉኛ የተጎዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ጉዳት ደርሶባቸው ከመጡት መካከል 16 ሰዎች የተለያየ ሕክምና አግኝተው ወደቤታቸው መሄዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ወደ ኦቶና ሆስፒታል በግጭቱ ተጎድተው የገቡት አራት መሆናቸውን ዶ/ር መብራቱ ቢገልፁም ሁለት ሰዎች ብቻ እግራቸው ላይ በጥይት ቆስለው መምጣታቸውን የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጌታሁን ሞላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዞኑ በነበረው አለመረጋጋት ከሞቱት ሰዎች መካከል ሰባቱ ሆስፒታል አለመምጣታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር መብራቱ ከእነሱም ውስጥ ሦስቱ በተለምዶ ማዘጋጃ ሰፈር የሚባለው አካባቢ፣ ሁለት ማዕዶት ሰፈር፣ ኦቶና ሆስፒታል መሄጃ ላይ 21 ማዞሪያ በመባል የሚታወቀው ሰፈር ደግሞ ሁለቱ መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
የተቀሩት ደግሞ ሁለቱ ወደ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ለሕክምና እንደመጡ የሞቱ ሲሆን ሰባቱ ሰዎች ደግሞ በቦዲቲ ከተማ በደረሰባቸው ጉዳት ሳቢያ ወደ በሕክምና ተቋማት ከተወሰዱ በኋላ ህይወታቸው ያለፈ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር መብራቱ ገለፃ ከሆነ በግጭቱ የተጎዱ ሰዎች ወደ ኦቶና ሆስፒታል ያልሄዱበት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ ነው ቢሉም ዶ/ር ጌታሁን በበኩላቸው ሆስፒታሉ ከኮሮናቫይረስ መከላከል ጋር በተያያዘ እየሰራ የነበረው ሥራ በመኖሩ ተጎጂዎችን መቀበል አለመቻላቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር መብራቱ ኦቶና ሆስፒታል ተጎድተው ከመጡ አራት ሰዎች መካከል አንዱ የአስራ ሁለት ዓመት ልጅ መሆኑን በመጥቀስ እጁ ላይ በዱላ ተመትቶ ስብራት ደርሶበት መግባቱን ጨምረው አብራርተዋል።
ቢቢሲ በዞኑ ስለተከሰተው አለመረጋጋትና ጉዳት ስለደረሰባቸው ሰዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ቢያደርግም ምላሽ ለማግኘት አልቻልም።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ እርስቱ ይርዳው በወላይታ ዞን ስለተከሰተው አለመረጋጋት ለደቡብ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉንና የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረው ለሞቱት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።
በሶዶ አሁንም የሰዎች እንቅስቃሴ የተገደበ መሆኑን የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ንግድ ቤቶች፣ ባንክ ቤቶች፣ የመንግሥት ቢሮዎች ዝግ መሆናቸውንና የትራንስፖርት እንቅስቃሴም አለመኖሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚወስዱ የከተማዋ መንገዶችም ዝግ መሆናቸውን ለቢቢሲ ጨምረው አረጋግጠዋል።
በቦዲቲ አሁንም ውጥረት መኖሩን የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ልክ እንደ ሶዶ ሁሉ ከተማዋ እንቅስቃሴ አልባ መሆኗን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለት በወረዳና በዞን ደረጃ ያሉ አስተዳዳሪዎች ሕዝቡን እንዲያረጋጉ ከክልልና ከፌደራል የመጡ አመራሮች ጋር ጥያቄ የቀረበበት ስብሰባ መካሄዱን የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ማቴዎስ ባልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሆኖም በዋነኝነት የዞኑ አመራሮች፣ የሕግ ባለሙያዎችና ከሃያ በላይ ሰዎች በታሰሩበትና መንግሥት ያላግባብ ኃይል በመጠቀም የብዙዎች ህይወት በጠፋበት ሁኔታ ስብሰባውን ማካሄድ አንችልም በሚል ያለውጤት መበተኑን አንድ ተሳታፊን ዋቢ አድርገው አቶ ማቴዎስ ይናገራሉ።
"አመራሮቹ ሕግን ባልተከተለ መንገድ ተከበው በወከባ ነው የታሰሩት፤ የሚያስጠይቅ ነገር ቢኖር እንኳን ሕግን በተከተለ ሁኔታ መሆን ነበረበት። ለምንስ የዚህን ያህል ሰው ህይወት ጠፋ? ትዕዛዝ የሰጠው አካልስ ማነው?" የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸውን አቶ ማቴዎስ ያስረዳሉ።
የታሰሩ አመራሮች ከተፈቱና እንዲሁም በፀጥታ ኃይል የተገደሉ ሰዎችን በተመለከተ ነፃና ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ትዕዛዝ ስለሰጠው አካልና ኃላፊነት የሚወስድ አካል መታወቅ ለመግባባቱና ለስብሰባውም እንደ ቅድመ ሁኔታዎች መቀመጣቸውን አቶ ማቴዎስ ያስረዳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የታሰሩ አመራሮች ከህወሓትና ኦነግ ሸኔ ጋር ይዶልቱ ነበር ብለው የክልሉ ፖሊስ መናገራቸው አግባብነት የሌለው ነው በማለት ብዙዎች በስብሰባው ላይ ሃሳባቸውን አንፀባርቀዋል ብለዋል። በዚህም መሰረት ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲካሄድ በሚልም በቀጠሮ ተለያይተዋል።
በትናንትናው ዕለት ከታሰሩት ውስጥ የአገር ሽማግሌዎችን የወከሉት አቶ ሰይፉ ለታና አቶ ዳንኤል ደሳለኝ የተፈቱ ሲሆን ሌሎች እስረኞችንም የሐይማኖት አባቶች መጎብኘታቸውንም አቶ ማቴዎስ ይናገራሉ።
እስረኞቹ በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ለሐይማኖት አባቶቹ የገለፁላቸው ሲሆን ምግብና ውሃም ቀርቦላቸዋል፤ በሩቅም ሆነው ጎብኚዎችን ማየት እንደቻሉም እስረኞቹ መናገራቸውን አንድ አባት ለአቶ ማቴዎስ ነግረዋቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ እስረኞቹ በአሁኑ ወቅት ፍርድ ቤት መቅረባቸውንም አቶ ማቴዎስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሶዶም ሆነ በቦዲቲ አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም የንግድም ሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች በአሁኑ ውስጥ ቀጥ እንዳሉ ናቸው።
በትናንትናው ዕለት በተለያዩ ወረዳዎች እንዲሁም በዛሬው ዕለት ደግሞ ኪንዶ ኮይሻ በምትባል ወረዳ እስረኞች ይፈቱ፣ ለተገደሉ ሰዎች ኃላፊነት የሚወስድ አካል እንዲጠየቅና ሌሎችም ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች መደረጋቸውንም አቶ ማቴዎስ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ወላይታ ዞን ውስጥ ስለተከሰተው አለመረጋጋትና የጸጥታ ኃይሎች ስለወሰዱት እርምጃ መግለጫ አውጥቶ ነበር።
በዚህም በዞን አንዳንድ ከተሞች የፀጥታ ኃይሎች ተቃውሞ ባሰሙ ሰዎች ላይ የወሰዱት እርምጃ "ተመጣጣኝነት አጠያያቂ" መሆኑን ገልጾ "የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፈኞችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይገባል" ብሏል።















