ጤፍን አቀነባብሮ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ወደ አገሩ የተመለሰው ‘ኢንቨስትመንት ባንከር’

የፎቶው ባለመብት, Lovegrass
ዮናስ አለሙ በአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ምህንድስና እና ፋይናንስ አጥንቷል። በሙናያው ልቆ እውቅ በሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ‘ኢንቨስትመንት ባንከር’ ለመሆን ችሏል።
ከአርሶ አደር ወላጆች የተገኘው ዮናስ፤ በተማረበት እና በወደደው ሙያ አንቱታን ያተረፉ ቀጠሪዎች ጋር ሥራ ቢጀምርም፤ የጤፍ ነገር እረፍት ቢነሳው ሥራውን እርግፍ አድርጎ ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።

ዮናስ አስተዳደጉን ሲገልጽ፤ “የገጠር ልጅ ነኝ፤ ቤተሰቦቼ ገበሬዎች ናቸው። እያረስኩ ነው ያደኩት ማለት ይቻላል” ይላል።
ዮናስ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በውጭ አገር የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ ቡልጋሪያ አቀና። ከዚያም በሌላ ‘ስኮላርሺፕ’ ወደ እንግሊዝ አገር ተጓዘ።
ከአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያ ዲግሪውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፤ ሁለተኛውንም ዲግሪ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢያገኝም፣ ሁልጊዜም ፍላጎቱ የፋይናንስ ዘርፉን መቀላቀል እንደነበረ ዮናስ ይናገራል።
“ፋይናንስ ውስጥ መግባት በጣም እፈልግ ስለነበረ በዘርፉ ትምህርቴን ተከታተልኩ” የሚለው ዮናስ፤ ግሎባል አሶሲዬሽን ኦፍ ሪስክ ፕሮፌሽናልስ ከተባለ ተቋም የዘርፉን እውቅና (ሰርተፊኬሽን) ከወሰደ በኋላ ወደ ፋይናንስ ኢንዱስትሪው መቀላቀሉን ያስታውሳል።
ዮናስ በወደደው የሙያ ዘርፍ አንቱታን ባተረፉ የፋይናንስ ተቋማት ተቀጥሮ መስራት ቻለ።
“በጣም ጥቂት ሰዎች ነበሩ ይህ ሰርተፊኬሽን የነበራቸው። ይህም ዕደል ፈጥሮልኝ በፈረንሳዩ ቢኤንፒ ፓሬባ ሥራ ጀመርኩ። ከዚያ ጄፒ ሞርጋን፣ ክሬዲት ሱዌዝ እያልኩ የኢንቨስትመንት ባንከር ሥራን ቀጠልኩ” ይላል።
ከአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቆ በመረጠው የሥራ መስክ በስመ ጥር ተቋማት ሥራውን ቢጀምርም፤ በኢትዮጵያ ጤፍ የውጭ ኩባንያዎች ከአገሬው በላይ ተጠቃሚ ሆነው መመልከቱ እንዳሳሰበው ዮናስ ይናገራል።
በአገር ደረጃ ጤፍን በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊ ወደሆነ ሸቀጥ መቀየር ባለመቻላችን የውጭ ኩባንያ ጤፍን ለዓለም ገበያ አቅርቦ ከትርፉ ተጋሪ ለመሆን ፍቃድ አሳልፈን ሰጥተናል ይላል ዮናስ።
“ይህ ለእኔ በተለይ እንደ ገበሬ ልጅ የሚያሳዝን ነው። በአገር ደረጃ ይህ አቅም አለመኖሩ ያሳዝናል። የትኛውንም አይነት ፈተና ተጋፍጬ ወደ አገር ቤት ተመልሼ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት የሚል እምነት ነበረኝ።”
ዮናስ ጤፍ የኢትዮጵያዊነቱን መልክ ሳይቀይር፤ ለዓለም ገበያ በሚሆን መልኩ አቀነባብሮ ለገበያ ለማቅረብ መኖሪያው ከነበረው እንግሊዝ አገር ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።
“ሂድ የሚል መካሪ አልነበረም። ለእኔ ብለው ሰዎች ‘ተው አትሂድ፤ ይቅርብህ’ እያሉ እየመከሩኝ የማንንም ምክር ሳልሰማ ዐይኔን ጨፍኜ ሥራዬን ለቅቄ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ።”
ሥራ ለመጀመር የነበረው ፈተና
ዮናስ ወደ አገር የተመለሰው በኢትዮጵያ የራሳችንን ጥሬ ግብዓት ተጠቅመን፤ በራሳችን የንግድ ዓርማ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚል ራዕይ ይዞ ነው።
ዮናስ ይህን ራዕይ ይዞ ከአውሮፓ ቢመለስም ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነው አልጠበቁትም። ውጥኑ ብዙ ፈተና ገጥሞታል።
“ከመጣሁ በኋላ የገጠሙኝ ፈተናዎች ብዙ ነበሩ። የገጠሙኝ ችግሮች መንቀሳቀስ እንኳ የሚያስችሉ አልነበሩም” ይላል ወደ ንግድ ሥራ ለመግባት ሲያደርግ ገጥመውት የነበሩትን ፈተናዎች ሲያስብ።
“ቦታ ማግኘት ብዙ ጊዜ ፈጀብኝ። የመጣሁበትም ወቅት የፖለቲካ ለውጥ የነበረበት ስለነበረ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። ቦታ ለማግኘት ብቻ አንድ ዓመት ተኩል ነው የፈጀብኝ።”
ዮናስ ሥራውን የሚያከናውንበት ቦታን ካገኘ በኋላ እንኳ የግንባታ እና ሌሎች ፍቃዶችን ለማግኘት ብዙ መድከሙን ያስታውሳል።
ከሱሉልታ ማሳ - ወደ ዩኬ ሱፐር ማርኬቶች

ከረዥም ጥረት በኋላ ግን ዮናስ በሱልልታ ማሳ የተመረተውን ጤፍን አቀነባብሮ ‘ላቭ ግራስ ኢትዮጵያ’ በሚል የንግድ ስም ምርቶቹን ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ቻለ።
“ላቭ ግራስ የጤፍ ሌላኛው መጠሪያ ነው። ‘ላቭ ግራስ ኢትዮጵያ’ የሚል ስያሜ የሰጠነው ጤፍ የኢትዮጵያ ነው ለማት ነው” የሚለው ዮናስ፤ ብዙዎች ጤፍን በእንጀራ መልክ ብቻ ቢያውቁትም ከጤፍ ብዙ ነገር ሊሰራ እንደሚችል ይገልጻል።
ላቭ ግራስ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከጤፍ ዱቄት በተጨማሪ፤ የጤፍ ፓስታ፣ ለቁርስ የሚሆን የጤፍ ኮርንፍሌክስ፣ ግራኖል፣ ተበጥብጦ የሚጠጣ ብርታት ሰጪ ሼክ፣ ፓን ኬክ ሚክስ ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በኢትዮጵያ እያመረተ ለውጭ ገበያ ያቀርባል።
“የምግብ ገበያው ላይ ኢትዮጵያ ጥሩ ስም የላትም። በችግር እና በረሃብ ነው የምትታወቀው። እኛ ይህን ለመቀየር ነው ቆርጠን የተነሳው” የሚለው ዮናስ፤ ጤፍ በአሁን ወቅት በዓለም ደረጃ እውቅና እያገኛ ያለ የግብርና ምርት እንደመሆኑ ስሙን ከአትዮጵያ ጋር ማስተሳሰር ይኖርብናል ይላል።
“ለንግድ ምልክቱ ትልቅ ቦታ መሰጠት አለበት። አሁን ብዙ አገራት የጤፍ አምራች ሆነዋል። አሁን ቶሎ ብለን ኢትዮጵያ ከጤፍ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር ይኖርብናል። አለበለዚያ ልክ እንደ ቡና ‘ቡና እኮ በኢትዮጵያ ነው የተገኘው’ ከማለት ውጪ ብዙ መጠቀም አንችልም” ይላል።
በኢትዮጵያ አምርተን በዓለም ገበያ ተፎካካሪ መሆን ቀላል እንደማይሆን እንረዳለን የሚለው ዮናስ፤ ጤፍ ለበርካታ ሰዎች ጤና ተስማሚ ያልሆነው ግሉተን የተባለው ንጥረ ነገር የሌለው በመሆኑ እና ከፍተኛ ፋይበር ስላለው ተፈላጊ ምግብ መሆኑን ይጠቅሳል።
በተጨማሪም ጥንታዊነቱ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የእንስሳት ተዋጽኦን የማይጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመር መሆኑ ተመራጭ የመሆን ዕድሉ እየሰፋ ነው። ስለዚህም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በትንሽ ቀዳዳ ወደ ዓለም ገበያ ለመግባት እያጣr ነው።
የላቭ ግራስ ኢትዮጵያ ምርቶች አሁን ላይ እንደ ሰልፍሪጅስ እና ፕላኔትኦርጋኒክ ባሉ ግዙፍ የዩናይትድ ኪንግደም መደብሮች ውስጥ ይገኛሉ።
“ሱልልታ ላይ አምርተን ሰልፍሪጅስ መግባታችን ለእኔ ትልቅ ኩራት ነው። ይህ ‘መወዳደር እንችላለን’ የሚለው ሃሳባችን ትክክል መሆኑን አረጋግጦልናል" የሚለው ዮናስ፤ ምርቶቹም ከዩናይትድ ኪንደም እና ፈረንሳይ ጨምሮ 11 ሽልማቶችን ማሸነፋቸውን ይገልጻል።
በተገኘውን ስኬት ላይ ወደፊት ለኢትዮጵያ ገበያ ጨምር ምርቶችን የማቅረብ እቅድ እንዳለው የሚገልጸው ዮናስ፤ የአገሪቱን የንግድ ጉድለት ለመቀነስ መንግሥት ለሌሎች ንግድ ሥራ ፈጣሪዎች ማበረታቻ ማድረግ አለበት ይላል።
“የውጭ ንግድ ጉድለትን ለመቀየር ጥሬ ዕቃ መላክ የለብንም። እሴት ጨምረንበት መላክ አለብን። ይህ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው። መንግሥት ማበረታቻ ይዞ መቅረብ አለበት። አለዚያ የንግድ ጉድለታችን ሊስተካከል አይችልም” በማለት የኢትዮጵያ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ መበረታታት እንዳለባቸው አጽንኦት ይሰጣል።












