በአሜሪካ እንጀራን በፋብሪካ ማምረት የጀመሩት ኢትዮጵያውያን መንትያ ወንድማማቾች

በአሜሪካ የሚኖሩት ኤፍሬም እና ወንድሙ ፍፁም ዩሴፍ

የፎቶው ባለመብት, Ephrem

የምስሉ መግለጫ, ኤፍሬም ዩሴፍ እና ወንድሙ ፍፁም ዩሴፍ

በአሜሪካ የሚኖሩት ኤፍሬም እና ወንድሙ ፍፁም ዩሴፍ ተወልደው ያደጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

እነዚህ ወንድማማቾች የኮሌጅ ትምህርታቸውን ኢኮኖሚክስ አጥንተው ሲያጠናቅቁ እና ቤተሰቦቻቸው ምግብ ቤት ሲከፍቱ ተገጣጠመ።

እነ ኤፍሬም በክብ እንጀራ ዙሪያ፣ ክብ ሰርቶ ተሰባስቦ ማዕድ መቋደስን ያደጉበት ነው።

ሠፌዱም፣ ምጣዱም፣ መሶቡም ክብ የሆነን እንጀራ ግን የወደፊት መተዳደሪያቸው ይሆናል ብለው አላሰቡም።

አዲስ ተመራቂዎቹ ወንድማማቾች በአሜሪካ የሥራ ገበያ ላይ ወጥተው ቀጣሪ ከመፈለጋቸው በፊት ቤተሰቦቻቸው የከፈቱትን አዲሱን ምግብ ቤት ለማስለመድ፣ በዚያውም ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ወሰኑ።

“ከቤተሰቦቻችን ጋር ሆነን ሥንሰራ ያየነው” ይላል ኤፍሬም “እዚህ አገር በተለይ የሠራተኛ ችግር መኖሩን ነው።”

ከአገር በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የራስን ባህል በአሜሪካዋ ሳንሆዜ፣ ካሊፎርኒያ ላይ ለመትከል መታገል ድካሙ ቀላል አይደለም።

የዚህን ጥረት መቅኒ የሚያፈሰው የሠራተኛ አለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ ቀኑን ሙሉ እንጀራ ለመጋገር የሚጠፋው ጊዜ እና ጉልበት ጭምር ነው።

ኤፍሬም እና ወንድሙ ከእናታቸው ማጀት እንደልብ እጥፍ አድርገው፣ በትኩስ ወጥ እያጠቀሱ ይጎርሱት የነበረው እንጀራ አሁን ድካም አንዳለው ተረዱ።

“ሙሉ ቀን እንጀራ መጋገር የተደጋገመ እና ከባድ መሆኑን ተመለከትን” ይላል ኤፍሬም።

በእርግጥ ለእነ ኤፍሬም ቤተሰብ የእንጀራ ንግድ አዲስ አይደለም። ሚኒሶታ ውስጥ በእንጀራ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዘመዶች አሏቸው።

‘ሸጋ እንጀራ’ አሽሞንሙነው የጋገሩትን እንጀራ የሚሸጡበት ስም ነው።

ይህም ቢሆን ግን በሰው ጉልበት፣ በእጅ እየተጋገረ የሚሸጥ ነው።

ይህ በእነ ኤፍሬም አእምሮ እጅግ በጣም አድካሚ እና አሰልቺ ሆነ።

ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ወስነው ሥራ የጀመሩት ኤፍሬም እና ወንድሙ እንጀራ መጋገር ተለማመዱ።

“ፍፁም በተለይ በጣም ጎበዝ ነው፤ እኔም ግን ለክፉ አልሰጥም” ይላል ከመጋገር ይልቅ እንዴት በቀላሉ እንጀራ ማምረት ይቻላል የሚለውን ማሰብ የሚቀለው ኤፍሬም።

እንጀራ መጋገርን ቤተሰብ ለመርዳት ብለው የሞከሩት ኤፍሬም እና መንትያ ወንድሙ አድካሚ ነው ብለው ብቻ አልተዉትም።

የአውቶ ምጣድ ጥንስስ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ጉልህ ቦታ ካላቸው ምግቦች መካከል እንጀራ አንዱ ነው።

እንጀራን ከዚህ ቀደም እንደሚመለከቱት እነርሱን እና ትውፊታቸውን የሚያገናኝ፣ የማንነታቸው አሻራ የታተመበት፣ ወይንም ደግሞ ሆድ የሚሞላ ብቻ ሆኖ አልታያቸውም።

በእንጀራ ፍቅር ከጎረቤት ኬንያ እስከ አሜሪካ ባሉ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶች የሚመገቡ የውጭ አገር ዜጎች መውደቃቸውን እነ ኤፍሬም አስተውለዋል።

የቤተሰቦቻቸውን ምግብ ቤት የሚያዘወትሩ የሌላ አገር ዜጎች እንጀራን እያሽሞነሞኑ ቆርሰው በፍቅር ሲጎርሱ አይተዋል።

ይህ ደግሞ በሳንሆዜ ብቻ ሳይሆን በሚኒሶታ፣ በዋሺንግተን እና ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶችም ተመሳሳይ ነው።

ስለዚህ እንጀራን በፋብሪካ ደረጃ ቢጋግሩ ጓዙን ጠቅልሎ፣ ቀልቡን እና ልቡን አገሩን ጥሎ ለሄደው ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ለባዕዳንም እንደሚተርፉ ገብቷቸዋል።

የእንጀራውን ስሪት ትኩር ብለው ሲያዩት፣ አሰፋፉን ሲመለከቱ ደግሞ ምህንድስና፣ ሳይንስ፣ ጥበብ ታያቸው።

ኤፍሬም “ይህ እኮ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ጉዳይ ነው” ማለታቸውን ያስታውሳል።

ሊጡን ማዞር የሚችል ማሽን ካለ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ችግሩ ተቃለለ ማለት ነው ያሉት እነ ኤፍሬም ሥራውን ማቀላጠፍ እና በቶሎ መሥራት እንደሚቻል አሰሉ።

በእርግጥ ኤፍሬም እና ወንድሙ እንጀራ በክብ እያዞሩ መጋገር የሜካኒካል እንጂነሪንግ ጉዳይ ነው ይበሉ እንጂ ምህንድስና አላጠኑም። የእነርሱ ሙያ ኢኮኖሚክስ ነው።

ከምጣኔ ሀብት አንጻር ሲየዩት እንጀራ መጋገርን ጊዜ እና ጉልበትን የሚቆጥብ ማድረግ ከተቻለ፣ ፍላጎትን ማሳደግ ይቻላል።

ያ ደግሞ በብዛት ወደማምረት፣ ከዚያም በዝቅተኛ ዋጋ መሸጥ፣ ድካምን ማቅለል ያስችላል ሲሉ አሰቡ።

“ይህ የሆነው እኤአ በ2013 ነው” የሚለው ኤፍሬም ሀሳቡን ሚኒሶታ ለሚገኙት የሸጋ እንጀራ ባለቤቶች አማከሩ።

ሁሉም በሀሳቡ ተስማምተዋል።

ስለዚህ የምህንድስና ባለሙያዎችን ቀጥሮ ለማሠራት ማሰብ ነበረባቸው።

የመንትያዎቹ ወንድማማቾች እናት እና አባት

የፎቶው ባለመብት, Ephrem

የምስሉ መግለጫ, የመንትያዎቹ ወንድማማቾች እናት እና አባት

የመንትያዎቹ ወንድማማቾች ሀሳብ ሚኒሶታም ሆነ፣ ቤተሰቦቻቸው ምግብ ቤት ይህ ነገር ተግባራዊ ቢደረግ ገበያ ያገኛል፣ ሥራ ያቀላጥፋል፣ ድካም ያቀላል ሲሉ ወሰኑ።

“ጥራት ያለው እንጀራ እየጋገሩ ለሕብረተሰቡ ማቅረብ እና እናቶቻችንን ከድካም ማሳረፍ” የሚል ዓላማ ይዘው ተነሱ።

እንጀራን ግን በክብ የማዞር ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ የገባቸው፣ ከባለሙያዎች ጋር ተገናኝተው ጉዳዩን ማስረዳት ሲጀምሩ ነው።

“እንጀራ ማስፋት ከሜካኒካል ኢንጂነሪንግ በላይ ነው” ይላል ኤፍሬም።

እንጀራ በቅድሚያ መቦካት፣ ኩፍ እንዲል ለቀናት መቀመጥ፣ አብሲት ተጥሎ የሚሰራ መሆኑ ከሌሎች የዳቦ ዓይነቶች ለየት እንደሚል አስተዋሉ።

ከዚህ ሁሉ ባሻገር ደግሞ የሊጡ ውፍረት ራሱ የተለየ በመሆኑ ለማሽን ማቅረቡን ከባድ አደረገው። ስለዚህ ይህ ጉዳይ ተጨማሪ ሳይንሶች አሉት ወደሚል ተጨማሪ ማብራሪያ ገቡ።

የተቦካ ሊጥ ለማሽን ለማቅረብ የሊጡ ውፍረት ወጥ [ቋሚ] መሆን ቢኖርበትም፣ እነ ኤፍሬምን ግን የተቦካው ሊጥ በቆየ ቁጥር ውፍረቱ እየተቀያየረ አስቸገራቸው።

“እንጀራን ካሰብነው በላይ ውስብስብ ሆኖ አግኝተነዋል” ይላል ኤፍሬም።

እንጀራን በማሽን መጋገር ከዚህ ቀደም ተሰርቶ የሚታወቅ ባለመሆኑ ከቀጠሯቸው የምህንድስና ባለሙያዎች ጋር የሚሞክሩት ሁሉ በተደጋጋሚ እየከሸፈባቸው ተደጋጋሚ ውድቀት እንዳጋጠማቸው ኤፍሬም ያስታውሳል።

“ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት፣ በራሳችን ገንዘብ ስለሆነ እየሠራን የነበረው፣ ስንሞክር ስንወድቅ ነው የቆየነው።”

ተስፋ ሲያደርጉ፣ ተስፋ ሲቆርጡ የቆዩባቸው ዓመታት ረዥም መሆናቸውንም ያስታውሳል።

እኤአ በ2013 “አውቶ ምጣድ” ተብሎ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በርካታ ውድቀቶችን ካለፈ በኋላ ውጤት ማሳየት የጀመረው በቅርቡ ነው።

በሀሳብ ደረጃ 2013 ተጠንስሶ የመጀመሪያውን የእንጀራ መጋገሪያ ማሽን (ፕሮቶ ታይፕ) በ2014 መሞኮራቸውን ይናገራል።

ይህ ሙከራቸው ግን ለቀጣይ ሥራ መደላድል ቢሆንላቸውም “አስደንጋጭ ነበር” ይላል ኤፍሬም።

ከምርምር ሥራው ፈታኝ የነበረው ልክ እንደ እጅ እየተሽከረከረ፣ ሊጡን ምጣዱ ላይ መጥኖ የሚያሰፋውን እነርሱ ‘ዲፖዚተር’ የሚሉትን በአግባቡ ማሠራት ነበር።

ይህ ሊጡን የሚያሰፋ የማሽኑ ክፍል የእጅን እንቅስቃሴ በመኮረጅ፣ በአግባቡ ምጣዱ ላይ የሚያሰፋ መሆኑን ኤፍሬም ያብራራል።

አውቶ ምጣድ እንዴት ይሠራል?

የማሽኑ ትልቅ ኃላፊነት ዝግጁ የሆነን ሊጥ ወስዶ መጋገር ነው።

አሜሪካ አንድ ሰው በሰዓት ከ60 እስከ 70 እንጀራ መጋገር ይችላል የሚለው ኤፍሬም፣ በዚህ ማሽን ግን እስከ 1000 እንጀራ መጋገር ይቻላል።

አውቶ ምጣድ የተሳካ ሙከራ አድርጎ ዐይን ያለው እንጀራ ጋግሮ ያሳየው እኤአ በ2019 ነው።

ከዚያ በኋላ በየጊዜው እየተጠና፣ እየተስተካከለ እንደሄደ እና አሁን የደረሰበት ላይ መገኘቱን ይናገራል።

አሁን በተሳካ ሁኔታ እንጀራ የሚጋግረው ይህ ማሽን በሚኒሶታ በሰዓት 1000 እንጀራ በመጋገር ሥራውን ጀምሯል።

በቅርቡ ሳንሆዜ እንዲሁም ሲያትል ሥራዎችን ለመጀመር አጋሮች ማግኘታቸውንም ይገልጻል።

በተለይ በሲያትል ለመሥራት ከፓይረስ ኢንቨስትመንት ባለቤት ነቢል መሐመድ ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ኤፍሬም ለቢቢሲ ገልጿል።

ነቢል የእንጀራ ፋብሪካውን በሲያተል ለመክፈት ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ቁልፍ ከተሞች ተጨማሪ ፋብሪካዎችን ለመገንባትም ከመንትዮቹ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል።

ክቡን እንጀራ ለመጋገር ዘመናት ከተኬደው የክብ ሩጫ ወጥተው ወደ ኢንዱስትሪ የማሻገር ህልም ይዘው እየሠሩ መሆኑንም ጨምረው ይናገራሉ።

ኤፍሬም፣ አሁንም ግን ተጨማሪ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ጥናት ማድረጋቸውን እንደቀጠሉ መሆናቸውን ያስረዳል።

አውቶ ምጣድን ከመንትያዎቹ ወንድማማቾች ጋር በመሆን በገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት የሸጋ እንጀራ ባለቤቶች ከ ፍሰሀ እሸቱ (ዶ/ር) ጋር

የፎቶው ባለመብት, Ephrem

ኤፍሬም እና መንትያ ወንድሙ ትልቁ ችግር ሆኖ ያገኙት መጋገር ቢሆንም ማቡካት፣ መጥኖ አብሲት መጣል፣ የተጋገረውን ያለ እጅ ንክኪ አውጥቶ ማሸግ ቀጣይ የፕሮጀክቱ አካላት ናቸው።

ማሽኑ በአብዛኛው ከሰው ንክኪ ነጻ ሆኖ ቢሠራም፣ አሁንም ግን የተጋገረውን እንጀራ ከምጣዱ ላይ ለማውጣት ሰው ያስፈልገዋል።

ኤፍሬም በቀጣይ ይህንን ለመቅረፍ እንደሚሠሩ ይናገራል።

የተጋገረውን እንጀራ ለማውጣት ቀለል እንዲያደርገው በሚል ወደፊት በአራት መአዘን ቅርጽ ምጣዱን በማድረግ በጋዝ የሚሰራ ምጣድ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ነው።

ክብ እንጀራ የሚጋግረው የአሁኑ ምጣድ፣ በኤሌትሪክ የሚሰራ ሲሆን ኃይል ቆጣቢ መሆኑንም ይናገራሉ። በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ምጣዶች አንጻር ምን ያህል የኤሌትሪክ ፍጆታ ቆጣቢ መሆናቸውን እያስጠኑ ነው።

ነገር ግን አሁን ባላቸው መረጃ የእነርሱ ዘመናዊ ምጣድ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሺህ እንጀራ ለመጋገር ከሚፈጀው የኤሌትሪክ ኃይል በሁለት ሦስተኛ ያነሰ እንደሚወስድ ይናገራል።

የነበሩ ፈተናዎች

ኤፍሬም እና ወንድሙ ከ2009 (እአአ) ጀምሮ የለፉበት ይህ እንጀራን በብዛት ለማምረት የሚያስችል ዘመናዊ ማሽን ተሠርቶ ሲጠናቀቅ የኮቪድ ወረርሽኝ በመከሰቱ ምግብ ቤቶች ተዘጉ።

ይህም የእንጀራ ገበያውን አስቆመው።

ጉልበት፣ ጊዜን እና የነበረውን ጫና ተደማምሮ ከፍተኛ ኪሳራ ማስተናገዳቸውን የሚናገረው ኤፍሬም፣ ሁላችንም በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፍን በእልህ ስንሠራ ስለነበረ ነው እዚህ የደረስነው ይላል።

“ቤታችንን አስይዘን እየተበደርን ጭምር ነው ለፕሮጀክቱ ማሳኪያ ገንዘብ ስናመጣ የነበረው” የሚለው ኤፍሬም መጨረሻው አምሮ በማየቱ ደስተኛ ነው።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንጀራ በላተኛ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

የእንጀራ ዋጋ ውድ በመሆኑ የተነሳ ኑሮን በመላ ለመወጣት፣ በኩርማን እንጀራ ጎመን ጠቅልሎ ለመጉረስ ተቸገሩ በርካቶች ናቸው።

እነ ኤፍሬም እንጀራን በኢንዱስትሪ ደረጃ በአገር ውስጥ መጋገር ቢቻል፣ የበርካቶችን ጉሮሮ በርካሽ ዋጋ መድፈን፣ የበርካታ እናቶችን ድካምም ማቅለል ያስችላል።

ለዚህ ግን ከግል ባለሀብቱም ሆነ ከመንግሥት ጋር ትብብር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።