አውሮፓ ውስጥ በትምህርቷ በመላቅ፣ በሞዴሊንግ ሙያ ታዋቂ ለመሆን የምትጥረው ሩታ

ሩታ የማነ

የፎቶው ባለመብት, ruta yemane

የምስሉ መግለጫ, ሩታ የማነ

የሞዴል እና የፋይናንስ ባለሙያ የሆነች ሩታ የማነ ለ‘ቶፕ ሞዴል ኢንተርናሽናል 2024’ የቁንጅና ወድድር ዕጩዎች ከሆኑት አንዷ ስትሆን፣ በውድድሩ ግማሽ ምዕራፍ ከአምስቱ ምርጦች አንደኛ ደረጃን ይዛለች።

ባለሁለት ሙያ የሆነችው ሩታ፣ ሞዴሊንግ እና ፋይናንስ የጥንካሬ እና የውበት ምልክቶችዋ እንደሆኑ ትናገራለች።

“ሕይወትን መምራት ከቻልን የምንፈልገውን ማድረግ እንደምንችል አምናለሁ” ትላለች።

የቶፕ ሞዴል ኢንተርናሽናል የቁንጅና ውድድር፣ የዓለም ምርጥ ተሰጥኦ ያላቸው ሞዴሎች ከፍተኛ ውድድር የሚያደርጉበት መድረክ ነው።

በዓለም ዙሪያ ከ500 በላይ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት የዘንድሮው ውድድር በአዘጋጆቹ መስፈርት የተመረጡ አምስት ምርጥ አሸናፊዎች ለግማሽ ፍፃሜ ደርሰዋል።

“እዚህ ደረጃ የደረስኩት በሕዝብ ድምፅ ነው። ምክንያቱም ለተወዳዳሪዎቹ ወደ ‘ግማሽ ፍፃሜው’ ለማለፍ የሕዝብ ድምፅ ወሳኙ ነበር። በተለይ የአገሬ ልጆች፣ የትግራይ ተወላጆች ተባብረውኛል። ለማመስገን ቃላት ያጥረኛል። ለመጪው ውድድር በጣም ጓጉቻለሁ። ወደ መጨረሻ ለመድረስ ከአሁን በኋላ ሁለት ውድድሮች ይቀሩኛል” ስትል ተናግራለች።

የቶፕ ሞዴል ኢንተርናሽናል የግማሽ ፍፃሜ ተወዳዳሪዎች እና የመጨረሻ ዕጩዎች ውጤት በመጪው ኅዳር ወር ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

“ውድድር ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድሎች እና ከታዋቂ ብራንድ ባለቤቶች የሚያገናኝ መድረክ ነው” ስትል ውድድሩ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ትገልጻለች።

ከፍተኛ የሕዝብ ድምጽ እና የቁንጅና ውድድር ልምድ ስላላት፣ የሚቀጥለውን የመጨረሻ ዙር ውድድር አሸንፋለሁ የሚል እምነት አላት።

ሩታ የማነ

የፎቶው ባለመብት, ruta yemane

የምስሉ መግለጫ, ሩታ የማነ

“በተማሩ ሴቶች በጣም እቀናለሁ”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁኑ ጊዜ የፋይናንሺያል ማዕከል በሆነችው በሉክሰምበርግ በንብረት እና የገንዘብ አስተዳደር ኩባንያ ውስጥ እየሰራች ያለችው ሩታ በሞዴሊንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ብቻ መወሰን አልመረጠችም።

ይልቁንም ከፖላንድ ወደ ሉክሰምበርግ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት፣ በፋይናንስ እና ኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪዋን እየተማረች ትገኛለች።

“የተማሩ ሴቶች ሳይ በጣም እቀና ነበር” ትላለች፤ እሷም የእነሱን ምሳሌነት በመከተል ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ትሰጣለች።

የመጀመሪያ ዲግሪዋን በፖላንድ ውስጥ በኢንተርናሽናል ቢዝነስ አጠናቃለች።

ወደ ሉክሰምበርግ ከመምጣቷ በፊት ፖላንድ ለስድስት ዓመታት የኖረች ሲሆን፣ በፋይናንስ ባለሙያነት በምትሰራበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ ከጀመረችው የሞዴሊንግ ኢንዱስትሪ ጋር እንድትገናኝ ዕድል ሰጥቷታል።

“ትምህርቴን ስጨርስ፣ ከዋና ሥራዬ ጎን ለጎን ሞዴሊንግ እየሰራሁ ነበር” ትላለች።

ለመሆኑ ከሞዴሊንግን እንዴት ነበር የተዋወቀችው?

ሩታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሞዴሊንግ እና ከቁንጅና ውድድር ጋር የተዋወቀችው እ.ኤ.አ. በ2013 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ወቅት ለትምህርት ዕድል ወደ አውሮፓ ከመምጣቷ በፊት ነበር።

በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ሳለች በጓደኞቿ ግፊት በሚስ ዩንቨርስቲዎች ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር ተሳትፋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቶፕ ሞዴል ተሸላሚ ሆናለች።

በልጅነቷ ብዙ ሰዎች ሊያ ከበደን (ኢንተርናሽናል ቶፕ ሞዴል) እንደምትመስል እና ስታድግ ሞዴል እንደምትሆን ይነግሯት እንደነበር ታስታውሳለች።

"ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሞዴሊንግ ለእኔ የሚሆን ሥራ እንደሆነ እየተሰማኝ መጣ” ስትል ወደ የሞዴሊንግ እና ፋሽን የገባችበት አጋጣሚ ትናገራለች።

እንደዋዛ የበገባችበት ውድድር የአዲስ ኣበባ ዩኒቨርሲቲ ቶፕ ሞዴል በመሆኗ ነበር ወደ ሞዴሊንግ ኢንደስትሪ መንገዱን ‘ሀ’ ብላ ጀምረችው።

የዚያ ጊዜው ስኬት ከንግድ ሞዴል ኩባንያዎች ጋር እንድትሰራ ዕድል ሰጥቷታል። እንዲሁም በአቢሲኒያ የሞዴሊንግ እና አርት ትምህርት ቤት እንድትማር አነሳሳት።

“ኢትዮጵያ ውስጥ የመማር ተስፋን ተውኩ”

ሩታ ለመማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት፤ ነገር ግን በግል ችግር ምክንያት የሁለት ዓመት ትምህርቷን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ አልቀጠለችም።

ከሞዴሊንግ ሥራዋ ጎን ለጎን በባዮ ሜዲካል ኮሌጅ ነርሲንግ መማር ጀመረች።

ነገር ግን መንግሥት ‘ኮሌጁ ፍቃድ አልተሰጠውም’ በሚል ኮሌጁን የዘጋው ሲሆን፣ ሩታ የምትወደውን የትምህርት ዓይነት ለሁለተኛ ጊዜ ለማቋረጥ ተገድዳለች።

ለአራት ዓመታት ትምህርቷ መቋረጥ ከባድ ብስጭት ፈጥሮባታል።

“በጣም ተበሳጭቼ ነበር። ዩንቨርስቲውን ለቅቄ ስወጣ በአቅም ማነስ ሳይሆን በግል ችግሮች ምክንያት ነበር። ነርሲንግ ጀመርኩ እና ለሁለት ዓመት ተምሬያለሁ፤ እሱም ተቋረጠ። ይህ በሆነ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመማር ተስፋ ቆርጬ ነበር። ከአገር ለመውጣትም ወሰንኩ። ቢያንስ የመማር አቅም እንዳለኝ ለራሴ ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር” ትላለች።

ሩታ የማነ

የፎቶው ባለመብት, ruta yemane

የምስሉ መግለጫ, ሩታ የማነ

“በያዝኩት ነገር ሁሉ ስኬታማ መሆን እፈልጋለሁ”

ሩታ በኢትዮጵያ የአራት ዓመት ትምህርቷን ማባከን አልመረጠችም።

እ.ኤ.አ. በ2017 የትምህርት ዕድል ፍለጋ ወደ ፖላንድ ተጉዛ ከዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ንግድ የመጀመሪያ ዲግሪ አገኘች። የፋይናንስ ባለሙያ ሆና በፖላንድ መሥራት ጀመረች።

ሆኖም በፖላንድ የሞዴሊንግ እና የቁንጅና ውድድር ሥራዋን እንደምትቀጥል ምንም አላሰበችም።

“እ.ኤ.አ. 2017 ክረምት ነበር። ከጓደኞቼ ጋር በአንድ ካፌ ውስጥ ተቀምጬ ነበር፤ ድንገት አንድ ሰው አፍጥጦ ያየኝ ጀመር። ምቾት እስኪነሳኝ ድረስ ያየኛል። ከዚያም ለእነዚህ ጓደኞቼ ‘ይህ ሰውዬ ትኩር ብሎ እያየኝ ነው፣ በጣም ቀፈፈኝ’ አልኳቸው። ሲያዩትም ደንግጠው ‘አታውቂውም እንዴ?’ አሏት።

ጓደኞቿ ስለዚህ ግለሰብ ማንነት ነገሯት። ግለሰቡ የራሱ ታዋቂ የሜክአፕ ብራንድ ያለው እና በፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በጣም ታዋቂ እንደሆነ የሚነገረው ሃቢ ጀፈርሰን ነበር።

“በኋላ መጥቶ ራሱ አናገረን። ‘ይቅርታ! እንደረበሽኳችሁ ተረድቻለሁ፣ ግን እኛ የምንፈልገው አንቺን ነው። ነገ ለመፅሄት ፎቶግራፍ ‘ፎቶ ሾት’ አለን፤ አንድ ሰው እየፈለግን ነበር፤ ‘ነፃ ከሆንሽ መምጣት ትችለሽ’ ብሎ ቢዝነስ ካርዱን ሰጠኝ።”

ወዲያው ሩታ ለዲዛይን ፈንድ መጽሔት እንደ ሜክአፕ ሞዴል ታየች እና በሞዴሊንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ የነበራት ዕድሎች ተከፈቱ።

እንደ ልብስ፣ ጫማ፣ ሜክአፕ፣ ቦርሳ፣ ባንኮች እና ሌሎች የንግድ ሞዴሎች ባሉ የቁንጅና ውድድሮች ላይ መሥራት እና መወዳደር ችላለች።

ሩታ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያጠናቀቀችው እ.ኤ.አ በ2019 ነበር።

ከመደበኛ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ሥራ እና ከሥራ እስከ ሞዴልነት ድረስ በሁሉም ነገር ተሳትፋለች፣ ነገር ግን 2020 ለእሷ በጣም አስቸጋሪው ጊዜ ነበር።

የመጀመሪያ ትምህርቷን አጠናቃ በዳታ ሳይንስ ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የጀመረችበት ጊዜ ነበር።

“ደም አፈሳሹ ጦርነት በትግራይ ተጀመረ። ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። ከእንቅልፌ ነቅቼ የማየው ጨለማ ነው። ምንም ተስፋ የሌለበት የጨለማ ጊዜ ነበር። የምሰማው ዜና ሰዎች እየተገደሉ ነው የሚል ብቻ ሆነ፤ መብራት የለም፤ ባንክ የለም፤ ውሃ የለም . . የሚል ብቻ ነው”።

“በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፣ በጣም ተበሳጨሁ፣ ትኩረቴን መሰብሰብ አልቻልኩም፣ ወዲያው ትምህርቴን ማቋረጥ ነበረብኝ” ትላለች።

ሩታ የማነ በምትሳተፍበት ዓውድ ሁሉ ስኬታማ ለመሆን ጠንካራ አቋም አላት።

ለወደፊት ትግራይን “በፋይናነስና በሞዴሊነግ ሙያዋ እና በምትችለው ሁሉ” ለመርዳት ትሻለች።