በድሬዳዋ 34 ጅቦችን ‘ታግሎ የጣለው’ ወጣት

የፎቶው ባለመብት, yonas belihu
በድሬዳዋ ዙሪያ ጅቦች በርከት ብለው ይገኛሉ። ለዓመታት ‘ሰላማዊ’ ኑሮ ሲገፉ ቆየተዋል። ሰው ላይ አይደርሱም፣ ሰውም አይደርስባቸውም።
በከተማዋ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን ከተማ ውስጥም ጅቦች ይኖራሉ። የድሬዳዋን ግማሽ ሸፍኗል በሚባለው የምድር ባቡር ጊቢ ውስጥ እና ከግቢው በቅርብ ርቀት በሚገኘው ሰባተኛ ካምፕ ባለው ጫካ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ጅቦች በብዛት ይገኛሉ።
በምድር ባቡር ጊቢ ውስጥ አስታዋሽ ያጡት የባቡር ፉርጎወች፣ ብረታ ብረት እና የፍሳሽ ማሰወገጃዎች ውስጥ ጅቦቹ ይኖራሉ። ይራባሉ።
ለፋብሪካ ግንባታ ተብሎ በከተማው አቅራቢያ ጫካዎች ሲመነጠሩ ጅቦቹ በመሸሽ ወደ ምድር ባቡር ጊቢ ውስጥ እንደገቡ ይታመናል።
እዚሁ ጊቢ ውስጥ ሰዎችም ይኖራሉ። ቀድሞ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የሚመላለሱት የባቡር ፉርጎዎች ውስጥ ዛሬ ኑሮ መስርተው ልጆች ወልደው የሚኖሩ ሰዎች አሉ።
በዚህ መሃል ጅብና ሰው የመገናኘት ዕድላቸው እንደጊቢው ሰፊ ነው። ይህ በመሆኑ ጅቦቹ እንደሁኔታው ጥቃትም ለማድረስ አይቦዝኑም።
የ33 ዓመቱ ዮናስ በልሁ በድሬዳዋ ዲፖ ሰፈር ነዋሪ ነው። ዋናኛ መተዳሪያው ብረታ ብረት ብይዳ እና ግንበኝነት ነው።
በድሬዳዋ ዝነኛ የሆነው ግን ጅብ በማጥመድ ነው። ‘ጅብ ማጥመድ?!’ ግር ያሳኛል! ዮናስ ከ34 ጅቦች ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ አሸንፏል።
በጅብ ‘የተበላው’ የሦስት ዓመት ህጻን
በድሬዳዋ ጅብ ሰው ላይ ጉዳት አደረሰ የሚል ዜና እምብዛም የተለመደ አልነበረም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ይህ እየተቀየረ ነው።
የጅቦች ጥቃት እየጨመረ ቢመጣም ትኩረት የተነፈገው ነው ይላል ዮናስ።
አንድ ቀን የሆነው ግን ድሬዳዋን አሰደነገጣት። ነዋሪዎቿ አዘኑ።
ከሁለት ዓመታት በፊት ምድር ባቡር ጊቢ አካባቢ አባት እና የሦስት ዓመት ልጅ ይጫወታሉ። በግምት ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ “አባት ለሽንት” ዞር ይላል። የአባቱን እግር ተከትሎም ልጅ ይወጣል።
ዮናስ ሁኔታውን ያስታውሳል “[የ3 ዓመቱ ልጅ] ሰብ’ሰብ ብለው ወደ ነበሩ ልጆች ለመጫወት ይሄዳል። ጅብ መጥቶ ወደ ልጆቹ ሲጠጋ ሌሎቹ ሸሽተው ሲሄዱ እሱ ማመምለጥ አልቻለም። ቁጭ አለ። በጠራራ ፀሐይ [ጅቡ] አንገቱን ያዘው. . . አባቱ ብቅ ሲል ይዞበት ሲሄድ ነው ያየው።”
ልጁን ለማተረፍ ቢሞከርም “የተወሰነ አካሉን” ከማግኘት ውጪ ምንም ማድረግ አልተቻለም።
ማምሻውን ዮናስ እና ጓደኞቹ ለቅሶ ለመድረስ ወደ ቤቱ አመሩ።
ሰዎች ለለቅሶ ተስብስበው በነበረበት በዚያ ምሽትም የጀቦቹ ጩኸት ይሰማ እንደነበር የሚያስታውሰው ዮናስ፣ ከመደንገጥ እና ከማዘን ይልቅ በጅቦች የሚጠፋውን የሰው ሕይወት ለመታድግ ቆረጠ።
ሀሳብ አወጣ አወረደ። የብረታ ብረት ብየዳ ሙያውን በመጠቀም ጅቦቹን የሚያጠምድበት መንገድ አሰበ።
“የጅብ ወጥመድ”

የፎቶው ባለመብት, yonas
ዮናስ ጅቦቹን ሊይዝ የሚችል አንድ ሜትር በአንድ ሜትር የሆነ ከእንጨት እና ከሽቦ ወጥመድ አዘጋጀ። ወጥመዱ አገልገሎቱን ከጨረሰ የ‘ባጃጅ’ ሽቦ “ሸምቀቆ” ተዘጋጀቶለታል። ቀሪው ሥራ ደግሞ በጦር ያከናውናል። ወጥመዱን አዘጋጀቶ በውስጥ ሥጋ አስቀምጦ ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ አስቀመጠው።
ወጥመዱ አንድ ጅብ መያዝ ቢችልም አመለጠ። የመጀመሪያው ሙከራ አልተሳካም።
ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሁለተኛ ሙከራው በተለይም ለአካቢው ነዋሪ ሰቀቀን ከሆኑት ጀቦች አንዱን መያዝ ቻለ።
ይህንን የማድረግ ልምዱ ያልነበረው ዮናስ ከጅቡ ጋር ከንጋቱ 11 ሰዓእ እስከ ጠዋት 1 ሰዓት “ሲታገል” ቆይቷል።
ዮናስ በዚህ ድርጊቱ ምስጋና አላገኘም። ተቀራኒውን እንጂ። ከነዋሪዎች ወቀሳና “አስጨረሰከን” የሚል ትች ገጠመው።
“የእኛ ማኅብረሰብ ጅብ ተበቃይ ነው የሚል ፍራቻ አለው። ‘እኔን ባይበቀለኝ ወይ ልጄን ወይ የቅርቤን ሰው ይበቀላል’ የሚል አስተሳሰብ አለው። [ስለዚህ] ጅቡ ምንም ነገር ቢፈጽም ተጨማሪ አደጋ እንዳይፈጥር ምንም ለማድረግ አይሞከርም” ይላል ዮናስ።
የጅቡን ጥቃት ለመቀነስ ነዋሪዎች የሚወስዱት ከፍተኛው እርምጃ ያሉበትን ጫካ መመንጠር ነው። ዮናስ ግን ‘ጅብ ሲጠጉት ያፈዛል’ን ጨምሮ ስለጅብ ያለውን ‘አሉባልታ’ አይቀበልም። “ጅብ እንደማንኛውም እንስሳ ነው” ይላል።
“[የህጻኑ] ሕይወቱ ያለፈው ቀኑ ስለሆነ ነው፣ ፈጣሪ አላለም ብለው ጅቡ የሚደርገውን ነገር እስከመቀበል ደረስው” ነበር ሲሉም አክሏል።
በዚህም ሳቢያ ያድርጊት በእኛና ቤተሰቦቻችን ላይ ችግር ይፈጥራል በሚል ወቀሳቸውን አበረቱበት።
“የሚያስወግዳቸው” ጅቦች ቁጥር ሲጨምር ሰዎች ተቃውሞን ከመቀነስ አልፎ ይተባበሩት ጀመር።
“ያስወገድኩት ጅብ ስድስት ሲደር ከስወገድኩ በኋላ ስለምቀብር ከእኔ ጋር ቆፍረው መቅበር ጀመሩ። ሰባት እያለ ሲጨምር እየለመዱት ሄዱ ምንም የተለየ ነገር እንደሌለው አወቁ።”
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ድፍን ድሬዳዋን ያስደነገጠ ሌላ የጀብ ጥቃት ተሰማ።
የሦስት ዓመቱ ልጅ በጥቃቱ ሕይወቱ ካለፈ ከ37 ቀናት በኋላ ከምሽቱ 12 ሰዓት አከባቢ ቁጠባ በሚባል ሰፈር በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ “ከእናቷ ጋር የአንድ ሜትር ርቀት ያልነበራትን” ሌላ የ3 ዓመት ህጻን “እናቷ ወደ እቃ ቤት ዞር” ባለችብት ቅጽበት ጅብ ይዟት ሄደ።
ይህንን ተከትሎም የአከባቢው ነዋሪ ተሰባስቦ ብዙ ጥረት ቢያደርግም የህጻኗን ሕይወት ማትረፍ አልተቻለም።
በአካባቢው ያለው አንድ ጅብ ነው። ይህ ጅብ ህጻናት ላይ ጥቃት ማደረሱ ልጅ ላለው ሁሉ እንቅልፍ የሚሰጥ አልሆንም።
ይሄኔ ነው ከጅቦች ጋር በመታገል ስሙ ለናኘው ዮናስ የደወሉት።
ዮናስ በአካቢው አምሽተው ከሚሰሩ የባጃጅ ሹፌሮች እና ጥበቃዎች ስለጅቡ እንቅስቃሴ መረጃ ጠየቀ።
መረጃው በቂ ሆኖ ስላላገኘው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከጥበቃዎች ጋር በማደር በሦሰት አካቢዎች የጅቡን መውጪያ እና መግቢያ አጠና።
ጅቡ ወደ ሌላ ቦታ የማይሄድ፣ ከመሰሎቹ ጋር የማይቀላቀል፣ ግዙፍ እና ጥቁር እንደሆነ ተረዳ።
በተጨማሪም በዚህ ጥናቱ ዮናስ በአንድ ነገር እርግጠኛ ሆነ - የጅቡ እንቅስቃሴ በሙሉ ህጻኗ “ወደተበላችበት” አካባቢ እንደሆነ።
ወጥመዱን ከሌላው ጊዜ በተለየ አጠናከረው። እርግጠኛ በሆበት መውጫው በኩል አስቀመጠው። ጅቡ በለመደው ሰዓት ወጥቶ በዮናስ ወጥመድ ውስጥ ተገኘ።”
“አንዳንዴ ጥቃት የሚያደርሰውን ጅብ መያዜ እውነት ስለማይመስላቸው [የሞተውን] ጅቡን ለአካባቢው ነዋሪዎች እና ለህጻናት” አሳያቸዋል የሚለው ዮናስ “ጅቡን ስለሚያውቁት” ያንን ሲያዩ እርግጠኛ እንደሚሆኑ ጠቅሷል።
ከዚህ ክስተት በኋላ በአከባቢው የጀብ ጥቃት እንደቆመ እና የአከባቢው ነዋሪዎችም እፎይታን እንደገኙ ይገልጻል።
በእንዲህ መልኩ በሁለት ዓመታት ውስጥ እስካሁን በድሬዳዋ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪው ላይ ጥቃት ያደረሱ እና ስጋት የሆኑ 34 ጅቦችን ‘ታግሎ’ እንዳሰወገድ ይገልጻል።
ዮናስ በዚህ ሥራው ሕይወቱን አደጋ ላይ የጣሉ ክስተቶች አጋጥሞታል።
ከጅብ እግር ስር ወደቆ እንዲሁም በሌላ ጊዜ ከአንድ ጀብ ጋር ሲታገል ሌላ ጀብ ደርሶበት ‘በተአምር’ ሕይወቱ ተርፏል።

የፎቶው ባለመብት, Yonas Belihu
ነዋሪዎችን ከጅብ ጥቃት የመከላከል ክፍያ
ዮናስ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ለሚፈጽመው ተግባር ከነዋሪዎች ከምስጋና የዘለለ ክፍያ አግኝቶ አያወቅም።
ሥራውን የሚያውቁ ከልባቸው ይመርቁታል፣ ህጻናት እንደ ጀግና ይቆጥሩታል።
“ህጸናት ሲያዩኝ ጨዋታቸውን አቁመው ይጨፍራሉ። ደስታቸው የሆነ የሚስብ ነገር አለው” ሲል ይገልጻል።
“እናቶች ሁልጊዜ ነው ይመርቁኛል፣ ህጻናት ሲያዩኝ ደስተኛ ናቸው። በተለይ ስጋት የሆነባቸውን ጅብ ስይዝ በተለየ ሁኔታ ነው የሚያዩኝ። የእነሱ ደስታ ለእኔ ሁልጊዜም ደስታ ይሰጠኛል” ይላል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው ዮናስ በሚሰራው ሥራ ደስተኛ ቢሆንም አንዳንዴ “የሰው ልጅ ነኝ እና ፍርሃት ሲመጣ፣ ሁሉንም ነገር የሚያጠፋልኝ ቁጠባ አካባቢ በጅብ የተበላችወን ልጅ ፎቶ ሳይ ነው። ምንም ለማድረግ ወደኋላ አልልም” ሲል ይናገራል።
ዮናስ የሚፈጽመው ይህ ተግባር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በቪዲዮ ጨምር አሳይቶ በአንድ ወቅት ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር “የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ” ተደርጎለት እንደነበር ገልጿል።
ይህ ድጋፍ ቢቀጥል እና አሁን ካለው ወጥመድ የተሻለ እና ከቦታ ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስ የሚችሉ ሌሎች ወጥመዶችን ማዘጋጀት ይፈልጋል።
ድሬዳዋ ላይ ጅቦች ለህጻናት እና ለደከሙ ሰዎች ስጋት እንዳልሆኑ ከረጋገጠ በኋላ በአዲስ አበባ ዙሪያም ይሁን በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ጥቃት አድራሽ ጅቦችን ‘ማስታገስ’ ምኞቱ ነው።
“ህጻንም ሆነ ትልቅ ሰው [በጅብ] ተበላ የሚለው ነገር የመጨረሻ ነው የሚረብሸኝ። በተላይ ህጸናት ጅቡን የሚታገሉበት ምንም አይነት አቅም የላቸውም። ያ ነገር በጣም ስለሚረብሸኝ [ጅቦች የሚያስቸግሩበት ቦታ] ብደርስ ደስ ይለኛል” ብሏል።












