“የተስማማንባቸውን ነጥቦች ያለመሸራረፍ ለመፈጸም ተስማምተናል” አቡነ ሳዊሮስ

አቡነ ኤውስጣቴዮስ፣ አቡነ ሳዊሮስ እና አቡነ ጴጥሮስ

የፎቶው ባለመብት, eotc/facebook

የምስሉ መግለጫ, አቡነ ኤውስጣቴዮስ፣ አቡነ ሳዊሮስ እና አቡነ ጴጥሮስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በአገር ሽማግሌዎች እና በመንግሥት ባለሥልጣናት አማካይነት የተደረሰውን ስምምነት እንደሚያክብሩ አቡነ ሳዊሮስ አረጋገጡ።

የቤተክርስቲያኗ የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሦስት ሳምንታት በላይ የዘለቀውን ያለመግባባት በቤተክርስቲያኗ ቀኖና እና ሥርዓት መሠረት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተገኙበት ከስምምነት መደረሱ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ነገር ግን ከስምምነቱ ከሁለት ቀናት በኋላ ከቤተክርስቲያኗ ተለይተው የነበሩት አባቶች በተናጠል በሰጡት መግለጫ የስምምነቱን ነጥቦች ጥሰዋል በሚል የቤተከርስቲያኗ መሪዎች መግለጫ በመስጠት በስምምነቱ የተሳተፉ የሚመለከታቸው አካላት “ሁኔውን ሊመለከቱ እና በቃ ሊሉ ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርበው ነበር።

ይህንን ተከትሎ ቅዳሜ የካቲት 11/2015 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ እንደተገለጸው ደግሞ አቡነ ሳዊሮስ እና አብረዋቸው ያሉ አባቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ጽህፈት ቤት ተገኝተው ስምምነቱን “ሳይሸራረፍ እንደሚቀበሉ እና ተግባራዊ እንደሚያደርጉ” መስማማታቸውን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም በቀጣይ የሚኖሩ ተግባራትን በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት ለማከናወን መስማማታቸውን አቡነ ሳዊሮስ እና አቡነ ኤውስጣቴዮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አቡነ ጴጥሮስ ባሉበት በአማርኛ እና በኦሮምኛ በንባብ ባቀረቡት ቃል ገልጸዋል።

“የተደረሰው ስምምነት ተጥሷል”

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተው ችግር መፈታቱ ከተነገረ ከሁለት ቀናት በኋላ ስምምነቱ በአንደኛው ወገን በድጋሚ መጣሱን የቤተክርስቲያኗ አባቶች ቀደም ብለው ገልጸው ነበር።

የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃም እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ አርብ የካቲት 10/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ላይ፣ በስምምነቱ ወደ ቤተክርስቲያኗ እንዲመለሱ የተወሰነላቸው አባቶች በድጋሚ ጥሰት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

የቤተክርስቲያኗ መሪዎች እንዳሉት ቀደም ሲል ከቤተክርስቲያኗ እንዲለዩ ተወስኖባቸው የነበሩት አባቶች የሰጡትን ሹመት በተመለከተ እና ምላሽ በጋኙ ጉዳዮች ዙሪያ በድጋሚ ቀኖናውን እና የተደረሰውን ስምምነት መጣሳቸውን ገልጸዋል።

በመግለጫው ላይ አቡነ አብርሃም እንዳሉት ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በነበሩት ሁለት ቀናት በስምምነት እንዲመለሱ ከተወሰነላቸው አባቶች በኩል “የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍሉ፣ አባቶችን ከልጆች እና ልጆችን ከአባቶች የሚያሻክሩ ነገሮችን ናቸው” ብለዋል።

ውግዘታቸው እንዲነሳ የተወሰነላቸው ሦስቱ አባቶች ቦታው የት እንደሆነ ካልተገለጸ ስፍራ ላይ ሹመት የሰጧቸው አባቶች በተገኙበት በተሰጠ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተላለፈ መግለጫቸው፣ ቀደም ሲል ከተደረሰው ስምምነት ጋር የሚቃረን ሃሳብ ተንጸባርቀዋል።

ሲኖዶስ ተብለው በተጠቀሱበት በዚህ መግለጫቸው ላይም በሦስቱ አባቶች የተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳትን ሹመት በቤተክርስቲያን ሕግ እና ቀኖና መሠረት የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሹመቱ የሚነሳ ሳይሆን ባለበት እንዲቆይ እና ምክክር እንዲደረግበት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ይህንን በተመለከተ ብፁዕ አቡነ አብረሃም እንደተናገሩት “አዲሱ ሲኖዶስ በሚል እስካሁን ከሚጠቀሙበት ለየት ባለ አዲስ ስም” መግለጫ መሰጠቱን ጠቅሰው “የኤጲስ ቆጶሳቱ ሹመት በስምምነቱም በጋራ የጠፋ ወይም የተሻረ የተደመሰሰ መሆኑን እያወቁም ጥሰት ፈጽመዋል” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጨምረውም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት “የስምምነቱ አካል ሆነው ስምምነቱን ያነበቡት ሳይቀሩ፣ በአንድ ላይ ሆነው ስምምነቱን ጥሰውታል፣ ቀኖናውን እና የሃይማኖቱንም ሕግ እንደገና ደግመው ጥሰውታል” በማለት ሁኔታው “ከሃይማኖታዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘትን ተጎናጽፏል” ሲሉ ተናግረዋል።

ለውዝግቡ ምክንያት የሆነውን ሹመት የሰጡት አባቶች ለ25 ኤጲስ ቆጶሳት የሰጡት ሹመተ ክህነት አለመነሳቱን እና ተቀባይነት ማግኘቱን በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰው፣ ቀደም ሲል የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች የሚለውን መጠሪያ አዲሱ ሲኖዶስ በማለት መጠቀማቸው ተዘግቧል።

ይህም “አስተሳሰባቸው እና አነጋገራቸው ሁሉ በእኩል ደረጃ እንደሆኑ ከመግለጻቸው በተጨማሪ፣ 25ቱ የትናንት ካህናት እና አገልጋዮች አሁንም ኤጲስ ቆጶሳት እንደሆኑ ተደርጎ ተንጸባርቋል” በማለት የቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ አብረሃም ተናግረዋል።

ይህ የአባቶቹ መግለጫ የተደረሰውን ስምምነት የጣሰ ነው በማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተክርስቲያን በአቡነ አብረሃም እና በአቡነ ጴጥሮስ በኩል መግለጫ እንድትሰጥ እስገድጓታል።

በመግለጫው ላይም የቤተክርስቲያኗ ሥርዓት እና ሕግ መጣሱን እንዲሁም ችግሩን ለመፍታት በሽማግሌዎች እና በመንግሥት ባለሥልጣንት ፊት የተደረሰው ስምምነትን እንዲፈርስ መደረጉን በማመልከት የሚመለከተው አካል ሁኔታውን “ሊመለከተውና አሁንም በቃ ሊለው ይገባል” ብለዋል።

ከአራት ሳምንት በፊት ሦስት ጳጳሳት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም በማለት ከቤተክርስቲያኗ እውቅና እና ሕግ ውጪ ለ26 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት መስጠታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ቀውስ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ፣ የቤተክርስቲያኗ ቀኖና፣ ዶግማ እና ሥርዓት ተጥሷል በማለት ሹመት የሰጡት እና ሹመት የተቀበሉት አባቶች በይቅርታ አስኪመለሱ ድረስ በውግዘት ከቤተክርስቲያኗ እንዲለዩ ወስኖ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የአገር ሽማግሌዎች በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ባደረጉት ጥረት ማድረጋቸው ተነግሯል።

በዚህም ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ በመደረሱ ችግሩ በቤተክርስቲያኗ ቀኖና እና ሥርዓት መሠረት እንደተፈታ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም ተገልጿል።

በስምምነቱም ቅዱስ ሲኖዶሱ ሹመት በሰጡት በሦስቱ ጳጳሳት ላይ እና ሹመት በተቀበሉት ላይ ጥሎት የነበረውን ውግዘት እና እገዳ እንደሚያነሳ እና ወደ ቀደመ መንፈሳዊ ማዕረጋቸው እና ኃላፊነታቸው እንደሚመለሱ ተገልጾ ነበር።