በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተከሰተው ችግር በቀኖና እና በሥርዓት መሠረት መፈታቱ ተገለጸ

ጳጳሳት

የፎቶው ባለመብት, EBC

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ተከስቶ የነበረው ችግር በቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና እና ሥርዓት መሠረት እንደተፈታ አስታወቀች።

በዚህም መሠረት የቤተክርስቲያኗን ሥርዓት እና ሕግ ጥሰዋል ተብለው በቅዱስ ሲኖዶሱ ተወግዘው ተለይተው የነበሩት አባቶችም ወደ ቤተክርስቲያኗ መመለሳቸው ተገልጿል።

ሶስቱ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ኤዎስጣቴዎስና አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ቀደመ ሃገረ ስብከታቸውና ማዕረጋቸው እንዲመለሱና ተሿሚዎቹ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመታቸው የጵጵስና ሹመታቸው ተሽሮ ወደነበሩበት የክህነት ማዕረግ እንዲመለሱ ተወስኗል።

ከተሾሙት መካከል በቤተ ክርስቲያን ስርዓት ተመዝነው የሚያሟሉት በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲሾሙ ይደረጋል ተብሏል።

ቤተ ክርስቲያኗ ሕገወጥ ነው ካለችው ጵጵስና ሹመት ጋር ተያይዞ ባለፉት ሳምንታት በአገሪቱ ስጋት ፈጥሮ የነበረው ውዝግብ በቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና እና ሥርዓት መሠረት መፈታቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።

ችግሩ መፍትሔ ማግኘቱን በተመለከተ መግለጫ በተሰጠበት ጊዜ የቤተክርስቲያኗ ሥራ አስኪያጅ አቡነ አብረሃም “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሦስቱ አባቶች መመለስ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች” ብለዋል።

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ ከመፍታት ባሻገር በቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና ሥርዓት መሠረት እንዲፈታ ታላቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ተገልጿል።

“አሁን ችግሩ ተፈትቷል፣ ወደፊትም የቤተ ክርስቲያኗ ሉዓላዊነት እና አንድነት ተጠብቆ ክርስቶስ እስከሚመጣ በአንድነቷ እና በሉዓላዊነቷ ትኖራለች” ማለታቸው በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

ችግሩም እልባት እንዲያገኝ በቤተ ክርስቲያኗ በኩል አቡነ ናትናኤል፣ አቡነ ኤርምያስ፣ አቡነ ሩፋኤል እና የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ስለመደረጉ እና ችግሩንም ለመፍታት መቻሉ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተገኙበትም ቤተ ክርስቲያኗን የወከሉ አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ባሉበት ውይይት ተደርጎ የተደረሰበትን ስምምነት ሲኖዶሱ ተቀብሎታል ብሏል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት በቤተክርስቲያኗ አካታችነት እና የቋንቋ አጠቃቀም ላይ ያነሳናቸው ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም በማለት 26 ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾም ውዝግቡ መጀመሩ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሃይማኖታዊ ቀኖና እና ሥርዓት ውጪ ነው በማለት የጵጵስና ሹመቱን የሰጡት እና ተሿሚዎችን የቤተክርስቲያኗን ሕግ እንዲሁም ሥርዓት ጥሰዋል በማለት አውግዞ እንዲለዩ መወሰኑ ይታወሳል።

ነገር ግን አባቶቹ ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ የሚጠይቁ ከሆነ ቤተክርስቲያኗ መልሳ እንደምትቀበላቸው ገልጻ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ እና ሌሎች ጳጳሳት፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተወገዙት ሦስት አባቶች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ባለፈው ሳምንት አርብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስለተፈጠረው ክስተት መወያየታቸውን እና የቤተ ክርስቲያኗንም ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መንግሥት መቀበሉን ማሳወቋ ይታወሳል።

ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ሃይማኖታዊ ቀኖና እና አስተዳደራዊ ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ጉዳዩን እልባት እንድትሰጥ መንግሥት መስማማቱንም አሳውቃለች።

በተያያዘ ዜና ቤተ ክርስቲያኗ ሕገወጥ ሹመት ሰጥተዋል ባለቻቸው ጳጳሳት እና ተሿሚዎች ላይ የተወሰነው ጊዜያዊ እግድ እስከ የካቲት 17 እንዲጸና ተወስኗል።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ቤተ ክርስቲያኗ የእግድ አቤቱታ ያቀረበችባቸው ሦስት ጳጳሳት እና ተሿሚዎች ወደ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይገቡ የተላለፈው ጊዜያዊ እግድ እስከ ቀጣይ ቀጠሮ ድረስ እንዲቆይ ብያኔ መተላለፉን ጠበቃ አቶ አያሌው ቢታኔ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕግ ባለሙያዎች ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት ትዕዛዙ የተላለፈላቸው የመንግሥት ተቋማትም እንዲያስፈጽሙም ወስኗል ብለዋል።

እግዱ በአመልካች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ በሆኑ አብያተ ክርስቲያናት በምንም አይነት መልኩ እንዳይገቡ እና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የተሰጠ እግድ መሆኑንም አሰረድተዋል።

ሆኖም ከዚህ ቀደም አባቶቹ በነቀምት እና በጊምቢ የያዙት አገረ ስብከት እና አብያተ ክርስቲያናትን እንደማይጨምር፣ ከዚያ ውጪ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ላይ እግድ ተጥሎባቸዋል ብለዋል።

በዛሬው ችሎት በተጨማሪም እነ አባ ሳዊሮስን በወከሉትና ቤተ ክርስቲያኗ በከሰቻቸው 29ኛ ተከሳሽ የአቶ ኃይለሚካኤል ታደሰን ጉዳይ እንደተመለከተ ጠበቃዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃ እና የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ኃይለሚካኤል በጠበቃ ደረጃ ወይስ በግለሰብ ደረጃ ነው የሚከሰሱት፣ እንዲሁም ሌሎቹንስ ወክለው ክሱ ላይ መቅረብ ይችላሉ የሚለውም ተነስቷል።

ዳኞቹ ሁለት ለአንድ በሆነ ድምጽ አቶ ኃይለ ሚካኤል ራሳቸውን ጨምሮ በጥብቅና ውክልና ሌሎች ተከሳሾችንም ጨምሮ እንዲወክሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ቤተ ክርስቲያኗ ባቀረበችው የአቤቱታ እግድ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የካቲት 17/2015 ዓ.ም. ለማስተላለፍ ቀጠሮ ይዟል።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ግድያዎች፣ እስሮች፣ መዋከቦች እና እንግልቶች መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመናል ያሉ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን መያዛቸውን የተቃወሙ ምዕመናን ላይ የመንግሥት የፀጥታ አባላት እና ተባባሪዎቻቸው ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል መጠቀማቸው ተገልጿል።

በዚህም በጥይት እና በድብደባ ስምንት ሰዎች ሻሸመኔ ውስጥ መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ያለ ነው ብላለች።

በተለያዩ ቦታዎችም አዲሱን “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል ያሉትን ጳጳሳት በተቃወሙ ምዕመናን እና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጪ እስራት ተፈጽሟል ብሏል።