'ለረዥም ጊዜ ስንጠብቀው ነበር' - ፍልስጤማውያን ለተኩስ አቁም ስምምነቱ የሰጡት ምላሽ

ፍልስጤማዊያን ደስታቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ይህንን ለረዥም ጊዜ ስንጠባበቅ ቆይተናል። በመጨረሻም ምንም ሳልጨነቅ እተኛለሁ" ትላለች የ17 ዓመቷ ሳናቤል።

አሜሪካ እና አሸማጋይዋ ኳታር ከ15 ወራት ጦርነት በኋላ ተደርሷል ያሉትን የእስራኤል እና የሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነት በደስታ ከተቀበሉ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን አንዷ ናት።

ከሦስት ቀናት በኋላ ተግባራዊ በሚሆነው በመጀመሪያው የስምምነቱ ክፍል የእስራኤል ወታደሮች ህዝብ ከሚበዛባቸው የጋዛ አካባቢዎች እንዲወጡ ተደርጎ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያስችል ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ መኪናዎች በየቀኑ ወደ ግዛቲቱ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል።

በጋዛ ያሉ ነዋሪዎች ደስታቸው እና እፎይታቸውን ቢገልጹም ግን በህይወት ያጧቸውን እና ከአንድ ዓመት በላይ የወደመችውን ግዛት እንደገና መገንባት ስለመጀመራቸው ሲያስቡ ሃዘን እና ጭንቀት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።

ጋዛ የምትገኘው ሳናቤል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዜና ከተሰማ በኋላ "በመጨረሻም የምንፈልገውን አግኝተናል! ሁላችንም አሁን ደስ ብሎናል" ስትል ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ተናግራለች።

ቤተሰቦቿ በአባቷ ባስጠገኑት መኪናቸው "በእኩለ ሌሊት" ወደ ቤት ለመመለስ ማቀዳቸውን ትገልፃለች።

ካለፉት ሳምንታት ድርድር በኋላ ኳታር እና ዩናይትድ ስቴትስ የተኩስ አቁም መደረሱን እና ታጋቾች እንደሚፈቱ በማረጋገጣቸው በጋዛም ሆነ በእስራኤል በሚገኙ በታጋቾች ቤተሰቦች ዘንድ ትልቅ ደስታ ፈጥሯል።

የአስታራቂዎችን ረቂቅ ስምምነት ማጽደቁን የሐማስ ባለስልጣን ቀደም ብለው አስታውቀዋል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በበኩሉ "በርካታ ያልተፈቱ አንቀጾች" እንዳሉ ቢገልጽም፤ ዝርዝር ጉዳዮች ረቡዕ ምሽት ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ ተስፋውን ገልጿል።

ስምምነቱ በእስራኤል ካቢኔ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ከእሑድ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

"በጣም ጥሩ ስሜት ይሰማኛል። ከዚህ በፊት እንደዚህ ደስተኛ ሆኜ አላውቅም። በዙሪያዬ የሚሆነውን ነገር ማመን አልቻልኩም። እያለምኩ ነው?" ስትል የ19 ዓመቷ ዲማ ሹራብ ከካን ዩኒስ ለቢቢሲ በዋትስአፕ ባስተላለፈችው መልዕክት ተናግራለች

"በጋዛ ደስተኞች ብንሆንም ግን እንፈራለን። ስምምነቱ ሥራ ላይ ሲውል ፍርሃቱ ይጠፋል።"

ዲማ ሹራብ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቤተሰቦቿ ለበርካታ ጊዜ ከተፈናቀሉ በኋላ በከፊል በወደመ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር። ዳቦ፣ ለውዝ፣ አተር፣ ባቄላ እና አንዳንድ በጣም ውድ በሆኑ አትክልቶች ህይወታቸውን አቆይተዋል። ውሃ ለመቅዳት እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ድረስ ትጓዛለች። ጋዝ ስላልነበራትም በእንጨት ታበስላለች።

በአልጄሪያ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝታ የነበረ ቢሆንም ግን ጦርነቱ የተጀመረው ቪዛ ለማግኘት ፓስፖርቷን ካስገባች ከሁለት ቀናት በኋላ ነው። በራፋህ በኩል ለመውጣት ለደላላ ወደ 5 ሺህ ዶላር የመክፈል አቅም ያልነበራት ሲሆን ግንቦት ወር ላይም የነበረው ብቸኛው የራፋህ አማራጭ ተዘግቷል።

"የወደፊት ህይወቴ፣ ህልሞቼ የተጨናገፉ እንደሆነ ነው የተሰማኝ" ትላለች።

የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱ ግን ሐኪም የመሆን ፍላጎቷን መልሶታል።

ለስድስት ሳምንታት በሚቆየው በመጀመሪያው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት በሐማስ ከተያዙት 100 ከሚሆኑት ታጋቾች ውስጥ 33ቱ ተለቀው በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውን እስረኞች ጋር ልውውጥ ይደረጋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር የተኩስ አቁሙ በተጀመረ በ16ኛው ቀን ይጀመራል። በዚህም ቀሪዎቹ ታጋቾች እንዲፈቱ፣ የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና "ዘላቂ መረጋጋት" ማምጣትን ያካትታል።

ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ ዓመታትን ሊወስድ የሚችለውን ጋዛን መልሶ የመገንባት ሥራን እና የቀሩ የታጋቾች አስከሬኖችን መመለስን ያካትታል።

"በደስታ እና በሃዘን መካከል መዋለል"

ከሰሜን ጋዛ የተፈናቀለችው መምህርት ፋሪዳ እናቷን፣ አባቷን እና ወንድሞቿን ካየች ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናት ተናግራለች።

"በአሁኑ ጊዜ የመጠበቅ፣ የፍርሃት እና የጭንቀት ሁኔታ ውስት ነን" ስትል በማዕከላዊ ጋዛ ከምትገኘው ከዳር አል ባላህ ለቢቢሲ አረብኛ ጋዛ ላይፍላይን ተናግራለች።

"በጉጉት ስሜት ውስጥ ነን…የተከለከልነውን ነፃነት ለመተንፈስ እየሞከርን ነው።"

"የቱንም ያህል ብናገር የከበደኝን የተደበላለቀ ስሜት እና አሁን ወደ ቤቴ በመመለሴ የተሰማኝን ደስታ መግለጽ አልችልም።"

ሪም የተባለች እና ቤቷ ወድሞባት ከሰሜን የተፈናቀለች እናት በበኩሏ "ፈጣሪ ይመስገን ያልጠበቅነውን ጊዜ እየኖርን ነው" ብላለች።

"አሁን እየተሰማኝ ያለው ስሜት በደስታ እና በሃዘን መካከል ይዋልላል።"

ሃሺም አደል አቡ ኢያላ ደግሞ "የዓለም ላይ ታላቁ ስሜት" እንደተሰማው ከዃሃን ዩኒስ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ስቃይ፣ ሞት፣ ውድመት፣ ግድያ እና ረሃብ ውስጥ ሆነን ከአንድ ዓመት ከሦስት ወር በላይ እየጠበቅን ነው።"

"እኛ በትዕግሥት ቆይተናል። ከዚህ በፊት በዓለምም ሆነ በአረብ አገራት ያልታየ ጽናትን አሳይተናል።"

በድንኳን ውስጥ ለ15 ወራት እንደኖረ እና ወደ ቤቱ ሲመለስ "ተንበርክኮ ፈጣሪን እንደሚያመሰግን" አሳውቋል። "ይህ ደስታ በበጥሩ መልኩ እንዲያበቃ እንመኛለን" ብሏል።

ሐማስ መስከረም 26 በደቡብ እስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት በመፈጸም ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎች ከገደለ እና 251 የሚሆኑትን ማገቱን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ቡድኑን ለማትፋት ዘመቻ ከፍቷል።

ከዚያን ወዲህ በጋዛ ከ46 ሺህ 700 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ሲል በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከ2.3 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከፍተኛ ውድመት ከመድረሱም ባለፈ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት በሚደረገው ትግል ከፍተኛ የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድኃኒትና የመጠለያ እጥረት ተከስቷል።