ፈረንሳዊቷ 'ብራድ ፒት ነኝ' ብሎ በቀረባት ግለሰብ 850 ሺህ ዶላር ተጭበረበረች

ብራድ ፒት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፈረንሳዊቷ ግለሰብ ብራድ ፒት ብለው ለቀረቧት አጭበርባሪዎች 850 ሺህ ዶላር መስጠቷ አነጋጋሪ ሆኗል።

ስለግለሰቧ የቴሌቪዥን ስርጭት ያሰናዳው ቲኤፍ1 የተባለው ጣቢያ የተጭበረበረችው ግለሰብ ብዙ ትችት ማስተናገዷን ተከትሎ ፕሮግራሙን ሰርዞታል።

ፕሮግራሙ የተሰራጨው ባለፈው እሑድ ሲሆን በመላው ፈረንሳይ መነጋገሪያ ሊሆን በቅቷል።

የ53 ዓመቷ አን ለአንድ ዓመት ተኩል ከዝነኛው የሆሊውድ ተዋናይ ብራድ ፒት ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳላት ነበር የምታስበው።

መጭበርበሯ ካወቀች በኋላ ለአንድ ታዋቂ የፈረንሳይ የዩቲዩብ ቻናል በሰጠችው ቃል "እብድ አሊያም ሞኝ አይደለሁም" ብላለች።

"እንደተጨበረበርኩ አምናለሁ። ለዚህ ነው ወጥቼ የማወራው። ምክንያቱም እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ።"

የብራድ ፒት ተወካይ ኢንተርቴይንመንት ዊክሊ ለተባለ የአሜሪካ መዝናኛ ጣቢያ በሰጡት ምላሽ "አጭበርባሪዎች አድናቂዎች ከታዋቂ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት መበዝበዛቸው ያሳዝናል" ብለዋል።

ተወካዩ አክለው በተለይ ማኅበራዊ ሚድያ የማይጠቀሙ ታዋቂ ሰዎችን መስለው የሚመጡ አጭበርባሪዎች ልብ እንዲሏቸው መክረዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎች ግለሰቧን እየወረፏት ይገኛሉ።

በሕይወት ዘመኗ ያጠራቀመችን ገንዘብ ሙሉ በመሉ ያጣችው አን መጭበርበሯ ይፋ ከሆነ በኋላ ሶስት ጊዜ ራሷን ልታጠፋ እንደሞከረች ተነግሯል።

የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ድርጅቶችም ግለሰቧ ላይ ሲቀልዱ ተስተውለዋል።

ቱሉዝ የተባለው የእግር ኳስ ክለብ "ብራድ ፒት ረቡዕ ስታድየም መጥቶ ጨዋታ ይታደማል። አንቺስ አን?" ሲል ለጥፎ ቆየት ብሎ አጥፍቶታል። ክለቡ ለድርጊቱ ይቅርታ ጠይቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቲኤፍ1 ግለሰቧ ከደረሰባት "ብዝበዛ" በኋላ ፕሮግራሙን ማቋረጡን አስታውቋል። ቢሆንም የተሰራጨው ፕሮግራም አሁንም በይነ መረብ ላይ ይገኛል።

አን እንደምትለው ይሁ ሁሉ ነገር የጀመረው በአውሮፓውያኑ የካቲት 2023 ኢንስታግራም አውርዳ መጠቀም በጀመረች ወቅት ነው። በወቅቱ ከአንድ ሀብታም ግለሰብ ጋር በትዳር ትኖር ነበር።

አንዲት ጄን ኤታ የተባለች ግለሰብ የብራድ ፒት እናት ነኝ በማለት ቀርባት "ልጄ እንዳንቺ አይነት ሴት ነው የሚያስፈልገው" ትላታለች።

በሚቀጥለው ቀን ብራድ ፒት ነኝ የሚል ሰው ይቀርባታል። "እየሆነ ያለውን ነገር አላውቅም" ትላለች አን ሁኔታውን በማስታወስ።

በአንድ ወቅት ብራድ ፒት ነኝ ያለው ሰው ቅንጡ ስጦታዎች ሊልክላት ፈልጎ ነገር ግን ከተዋናይት አንጀሊና ጆሊ ጋር ባለው የፍቺ ሒደት ምክንያት የባንክ አካውንቱ እንደተዘጋ ይነግራታል። አን 9000 ዶላር ትልክለታለች።

"ልክ እንደ ሞኝ ሰው፤ ከፈልኩለት። ጥርጣሬ በገባኝ ቁጥር ጥርጣሬዬን የሚያጠፋ አንዳች ነገር ያደርጋል" ትላለች።

በሌላ ጊዜ ደግሞ የኩላሊት ካንሰር እንዳጋጠመው በመናገር በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሠሩ ምስሎች ይልክልታላል።

በዚህ መሐል አን ከባሏ ጋር ትፋታለች። ከፍቺው ያገኘችው 775 ሺህ ዶላር በሙሉ ተጭበርብሯል።

የ22 ዓመቷ የአን ልጅ እናቷ "ምክንያታዊ እንድትሆን ከአንድ ዓመት በላይ" መሞከሯን ትናገራለች።

አን መጭበርበሯ የገባት ትክክለኛው ብራድ ፒት ኢነስ ደ ራሞን የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መሆናቸውን ይፋ ሲያደርጉ ነው።

አጭበርባሪዎቹ "የኤፍቢአይ መኮንን ጆን ስሚዝ" በመምሰል ተጨማሪ ገንዘብ ሊወስዱባት ሲሞክሩ በስተመጨረሻ አን ሁኔታውን ለፖሊስ ጠቁማለች።

አን በአሁኑ ወቅት ከጓደኛዋ ጋር እየኖረች እንደሆነ ተናግራለች።