'ለባልሽ ስቃይ ተጠያቂዋ አንቺ ነሽ'፡ የምርኮኛ ቤተሰቦችን ለስለላ እና ጥቃት እንዲፈጽሙ የሚያስገድዱት የስልክ ጥሪዎች

ስቬትላና "ለአንድም ሰከንድ" አገሯን ለመክዳት አስባ እንደማታውቅ ተናግራለች።
"ባለቤቴ ፈጽሞ ይቅር አይለኝም ነበር" ስትል በዩክሬን መዲና ኪየቭ አቅራቢያ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ተናግራለች።
ባለቤቷ ዲማ በአገሩ ጦር ውስጥ የሕክምና ባለሙያ ነው። ከሁለት ዓመት በላይ በሩሲያ ተይዞ ከቆየ በኋላ በድንገት ስልክ ተደወለላት።
ዩክሬን ላይ ክህደት ከፈጸመች ዲማ በእስር ቤት የተሻለ እንክብካቤ ሊደረግለት አልፎ ተርፎም ከታሰበው ጊዜ ቀደም ብሎ ሊፈታ እንደሚችል በስልክ ተነገራት።
"የተደወለው በዩክሬን ቁጥር ነው። ስልኩን ሳነሳው ግለሰቡ ራሱን ዲሚትሪ ብሎ አስተዋወቀ። አነጋገሩ የሩስኪ (የሩሲያ ቋንቋ) ተጽዕኖ አለበት" ስትል ስቬትላና ገልጻለች።
"'የወታደራዊ ምዝገባ ቢሮን ማቃጠል፣ ወታደራዊ መኪና ማቃጠል ወይም ደግሞ የዩክሬንን የባቡር ኤሌክትሪክ ሳጥንን ማበላሸት ትችያለሽ' አለኝ።"
አንድ ሌላ አማራጭ ሰጣት። በዚህም በአቅራቢያዋ ያሉትን የአየር መከላከያ ተቋሟት አድራሻ እንድታሳውቅ ጠየቃት። እነዚህ የዩክሬንን ሰማይ ከሩሲያ ድሮኖች እና ሚሳዔሎች የሚጠብቁ ወሳኝ ወታደራዊ ንብረቶች ናቸው።
ዲሚትሪ ሃሳቡን ሲያቀርብላት ስቬትላና ደግሞ የሩሲያ ወኪሎችን በተመለከተ የዩክሬን ባለሥልጣናት ያሠራጩትን መመሪያዎች እያስታወሰች ነበር።
በመመሪያው መሠረት በተቻለ መጠን ለረዥም ጊዜ ለማውራት እንዲሞክሩ፣ ሁሉንም ነገር መቅረጽ እና ፎቶግራፍ በማንሳት ሪፖርት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል።
ስቬትላና ጉዳዩን ሪፖርት አደረገች። የአጭር መልዕክቶቹንም ለቢቢሲ አሳይታለች።

የዩክሬን የደኅንነት አገልግሎት (ኤስቢዩ) ጉዳዩን እስኪመረምር ድረስ የተባበረች መስላ እንድትታይ ነገራት። በአካባቢው ያለውን የባቡር መስመር በቦምብ ለማፈንዳት የተስማማች መሆኗን በሐሰት ነገረቻቸው።
የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ አሁንም አሁንም በሚሰማበት የመኖሪያ ቤቷ ሆና በቴሌግራም በኩል ከዲሚትሪ የደረሷትን ሁለት የድምጽ ጥሪዎች ታጫውት ጀመር። ሞሎቶቭ ኮክቴል እንዴት እንደሚዘጋጅ እና እንደሚጠመድ መመሪያ የሚሰጥ ትዕዛዝ ነበር።
"በአንድ ሊትር የከሰል ማቀጣጠያ ፈሳሽ ውስጥ ትንሽ ቤንዚን ጨምሪ። ወደ አንድ የባቡር ጣቢያ ሂጂ። ምንም አይነት የደኅንነት ካሜራዎች አለመኖራቸውን አረጋግጪ። ኮፍያ ብታደርጊም ጥሩ ነው" ሲል ድሚትሪ መመሪያ እያስተላለፈላት ነበር።
ስቬትላና ከዒላማዋ 2 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ስትደርስ ስልኳን ወደ 'ኤሮፕሌን ሞድ' ላይ እንዴት እንደምትቀይረው አስተምሯታል። ይህን የምታደርገው የስልኳን ሲግናል ተጠቅመው መርማሪዎች እንዳይደርሱባት መሆኑን ነግሯታል።
ሥራውን መጠናቀቁን የሚያሳይ ማረጋገጫ እንዲቀርብ በመጠየቅ "የማስተላለፊያ ሳጥን ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ፎቶ አንሺ። ይህ የቃጠሎሽ ዒላማ መሆን አለበት" ሲል ዲሚትሪ ገልጿል።
"የዛሬን ቀን በወረቀት ላይ ጻፊ። ወረቀቱን እና ቦታውን አንድ ላይ ፎቶ አንሺ።"
በምላሹ ደግሞ ከባለቤቷ ጋር በስልክ እንድትገናኝ ወይም መልዕክት እንዲደርሰው ማድረግ እንደሚትችል ዲሚትሪ ነግሯታል።
የምታናግረው ሰው ሩሲያ ውስጥ እንደሚገኝ የዩክሬን የስለላ ድርጅት አሳወቃት። በኋላ ላይ ግንኙነቷን ማቋረጥ እንዳለባትም ተነገራት። ስቬትላና ሃሳቧን እንደቀየረች ለዲሚትሪ ነገረችው።
"ዛቻዎቹ የጀመሩት በዚህ ጊዜ ነው" ስትል ስቬትላና ገልጻለች።
"ባለቤቴን እንደሚገድሉት እና ከዚያ በኋላ እንደማላየው ነገሩኝ" ብላላች።
ለቀናት እየደወለ "ባልሽ እየተሰቃየ ነው። ጥፋቱ ደግሞ ያንቺ ነው" ይለኝ ነበር።
ዲማ ሊጎዳ እንደሚችል ምን ያህል ተጨንቀሽ ነበር? ተብላ ስቬትላና ስተጠየቅ አይኖቿ በእንባ ተሞሉ። "ልቤ በጣም አዘነ። እናም 'አምላክ ሆይ፣ እባክህ ይህ እንዳይሆን አድርግ' እያልኩ መጸለይ ብቻ ሆነ ሥራዬ።"
"በአንድ በኩል 'ይህ ሰው ከእስረኞች ጋር ምንም ግንኙነት የለውም' እላለሁ። አንዳንዴ ደግሞ 'በእርግጥ ይህን ማድረግ ቢችልስ? ከራሴ ጋር እንዴት እኖራለሁ?' ብዬ እጠይቃለሁ።"

የፎቶው ባለመብት, Ukrainian Police Service
ከሩሲያ ወኪሎች ጋር መተባበር "የእስረኛውን ችግር በምንም መልኩ አያቃልልም በተቃራኒው የእስረኛ ልውውጥ ዕድሉን በእጅጉ ያወሳስበዋል" ሲል የዩክሬን የደኅንነት ተቋም ለቢቢሲ ገልጿል።
የሩሲያ ወኪሎች ሊያገኟቸው የሞከሩ ዩክሬናውያን ቤተሰቦች በፍጥነት ሪፖርት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ሪፖርት የሚያደርጉ ሰዎች "ጥበቃ ይደረግላቸዋል" እንደ ተጠቂም ይቆጠራሉ።
ለጥቃት ወይም የስለላ ተግባር ለመፈጸም ከተስማሙ ግን "ይህ እንደ አገር ክህደት ሊቆጠር ይችላል። እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ሊቀጡ ይችላሉ" ብሏል ኤስቢዩ።
የእሳት ቃጠሎ ፈጽመዋል ወይም ወታደራዊ ቦታዎችን ለሩሲያ ጠቁመዋል ያሏቸውን ዩክሬናውያን መያዛቸውን ባለሥልጣናት በየጊዜው ይፋ ያደርጋሉ።
የክሬምሊን ደጋፊ መገናኛ ብዙኃን ዩክሬናውያን የጦር ተሽከርካሪዎችን ወይም የባቡር መስመሮችን ሲያቃጥሉ ያሳያሉ በሚሏቸው ቪዲዮዎች ተሞልተዋል።
አንዳንድ ወንጀለኞች ከሩሲያ ወኪሎች ለሚያገኙት ገንዘብ ሲሉ ያደርጉታል። ተስፋ በቆረጡ ዘመዶች የተፈጸሙ ጥቃቶች እንዳሉም ግን ይታሰባል።

ፔትሮ ያሴንኮ የዩክሬን የጦር እስረኞች አያያዝ ዋና መሥሪያ ቤት ባልደረባ ሲሆን፣ 50 በመቶ የሚሆኑት የምርኮኛ ቤተሰቦች ከሩሲያ ወኪሎች ጋር መገናኘታቸውን ተናግሯል።
"በከፍተኛ ሁኔታ ለጥቃት የተጋለጡ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ናቸው። ነገር ግን [በምርኮ ላይ የሚገኙትን] እንደማይረዳቸው ለማስተማር እየሞከርን ነው" ይላል ፔትሮ።
ወታደራዊ ተሽከርካሪን ማቃጠልን የመሰለ ድርጊት ለዩክሬን ጦር እንደ ትልቅ ቁሳዊ ኪሳራ አይቆጠርም ሲል ፔትሮ ተናግሯል።
"ዋናው ችግር ግን የዩክሬን ማኅበረሰብ አንድነትን ሊያናጋ መቻሉ ነው።"
"እርግጥ ነው አንድ ሰው ለምሳሌ የአየር መከላከያ መሣሪያዎችን የሚገኙባቸው ቦታዎችን የሚያጋራ ከሆነ ለእኛም ትልቅ ችግር ነው" ሲል አምኗል።
በጦርነት የተያዙትን የዩክሬናውያንን ቁጥር ባለሥልጣናት አያሳውቁም። ቁጥሩ ከስምንት ሺህ በላይ እንደሚሆን ግን ይታሰባል።
ዘመዶቻቸው ከሩሲያ ጋር ለመሥራት የተስማሙት ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የዩክሬን የስለላ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሩሲያ መንግሥት የእስረኞችን ቤተሰቦች እንደ መሣሪያ ይጠቀማል የሚባለውን ውንጀላ "መሰረተ ቢስ ነው" ሲል ለቢቢሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ሩሲያ "የዩክሬን ተዋጊዎችን በሰብአዊነት ከመያዝ ባለፈ የጄኔቫ ስምምነትን ታከብራለች" ብሏል።
ዩክሬንን ተመሳሳይ ዘዴዎችን ትጠቀማለች በማለትም በመግለጫው ከሷል።
"የዩክሬን ወኪሎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን እና የሲቪል ተቋማትን ዒላማ እንዲያደርጉ እና የእሳት ቃጠሎ እንዲፈጽሙ የሩሲያ ነዋሪዎችን ለማስገደድ እየሞከሩ ነው" ብሏል።

የሲቬትላና ባለቤት ዲማ ከታሰረበት ከሦስት ወራት በፊት ተለቋል።
ጥንዶቹ አሁን በደስታ አብረው መኖር ጀምረዋል። ከአራት ዓመት ልጃቸው ቮቫ ጋር ጊዜያቸውን ማሳለፍ ያስደስታቸዋል።
ባሏ ነፃ ሲወጣ ስቬትላና ምን ተሰምቷት ይሆን?
"ከዚህ በፊት አልቅሼ የማላውቀው የደስታ እንባ ነበር። ፍቅሬን ከሞት መንጋጋ የነጠቅኩ ያህል ነው የተሰማኝ" ትላለች።
ሩሲያውያን ሚስቱ ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆኗ እሱን ለመቅጣት ቢዝቱም እርምጃ እንዳልወሰዱበት ዲማ ነግሯታል።
ስቬትላና ስለስልክ ጥሪዎቹ ስትነግረው ደነገጠ።
"እንዴት እንዳገኙኝ ጠየቀኝ?" መልሷም "ለማንኛውም ሁሌም እንደምለው፣ እኔ የመኮንኑ ሚስት ነኝ" ስትል በቀልድ መልክ መልሳለች።















