በ2025 የዩክሬን ጦርነት ያከትም ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቭላድሚር ፑቲን በጎርጎሮሳውያኑ 2024 ማገባደጃ ባደረጉት ንግግር "በሁሉም የጦር ግንባር በየቀኑ እንቅስቃሴ አለ። ሁኔታው በፍጥነት እየተለወጠ ነው" ብለዋል።
በምሥራቅ ዩክሬን የሞስኮ ወታደሮች ወደ በዶምባስ የሚያደርጉትን ጉዞ ቀጥለዋል።
አንዳንድ ነዋሪዎች ጦርነቱ እነሱ መንደር ሳይደርስ ቀድመው እየሸሹ ነው። የተቀሩት ድብደባ ሲጀመር ጓዛቸውን ጠቅልለው ከአካባቢው ይወጣሉ።
ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከ2022 ወዲህ ብዙ ግዛቶች እየያዘች ነው። ዩክሬን ኃያሏን ሩሲያ ለመመከት ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ቀጥላለች።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሞቱበት፣ የተጎዱበትና የተፈናቀሉበት ጦርነት ሦስት ዓመታት አስቆጥሯል። ዩክሬን እየተሸነፈችም ይመስላል።
ዩክሬንንም ሆነ ፕሬዝዳንቱን የማይወዱት ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሀውስ ሊገቡ ነው።
በ2025 የዩክሬን ጦርነት ያከትም ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ድርድር አይታሰብም'
ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በ24 ሰዓታት ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ቢናገሩም ለመተግበር የሚከብድ ይሆናል። ንግግራቸው አሜሪካ በጦርነቱና በምታወጣው ወጪ ምን ያህል እንደተሰላቸች ማሳያ ነው።
"በየሜዳው የሞቱ ወታደሮች ቁጥር እየጨመረ ነው። እየሆነ ያለው ነገር እብደት ነው" ብለዋል ትራምፕ።
በካርንጊ ኢንዶውመንት ፎር ኢንተርናሽናል ፒስ የሚሠራው ማይክል ኮፍማን እንደሚለው የትራምፕ አስተዳደር ሁለት ፈተና ይገጥመዋል።
"አንደኛው በአሉታዊ መንገድ የሚታይ ጦርነትን ከቀደመው አስተዳደር መረከባቸው ነው። ጦርነቱን ለማቆም በቂም ጊዜ አይኖራቸውም። ሁለተኛው ፈተና ጦርነቱን የሚረከቡት መፍትሔ የመስጠት ዕድል ሳይኖር ነው" ይላል።
ትራምፕ እንዴት ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ከታይም መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጠቁመዋል።
ከባይደን አስተዳደር ጋር በጦርነቱ አካሄድ እንደማይስማሙ ገልጸው፣ ዩክሬን ረዥም ርቀት ሚሳዔል እንድትተኩስ አሜሪካ መፍቀድ አልነበረባትም ብለዋል።
"ጦርነቱን እያባባስን ነው" ብለዋል ትራምፕ።
ለዩክሬን ድጋፍ መስጠት ያቆሙ እንደሆነ በኤንቢሲ ተጠይቀው "ሊሆን ይችላል" ሲሉ መልሰዋል።
ዩክሬንን ችላ ሊሉ ይችላሉ የሚል ስጋት ቢኖርም "ጥሎ በመሄድ የሚመጣ መፍትሔ አይኖርም" ሲሉም ተደምጠዋል።
አቋማቸው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የዩክሬን ባለሥልጣኖች ንግግር እንዲደረግ የሚደርስባቸውን ጫና አልተቀበሉትም።
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ቢሮ "ድርድር አይታሰብም። ሩሲያ በጦርነቱ ዋጋ ስላልከፈለች ድርድር አይኖርም" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያ ጦር በምሥራቅ ዩክሬን መግፋቱን እስከቀጠለ ድረስ የሰላም ንግግር ሊኖር እንደማይችል ዩክሬን አስታውቃለች።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሲመረጡ ቀድመው የደስታ መልዕክት ከላኩ መካከል ናቸው። የትራምፕን ቡድን የሚያነጋግር ልዑክም ልከዋል።
በፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እገዛ ትራምፕና ዘለነስኪ ተገናኝተዋል።
የቀድሞው የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ፕሬዝዳንት ዘለነስኪ ጥሩ ስልት እየተከተሉ ነው። ከትራምፕ ጋር በገንቢ ሁኔታ ለመሥራት ዝግጁ መሆንን ያሳያል" ብለዋል።
ሩሲያ ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ከትራምፕ ጋር ለመገናኘት እየሞከረች ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።
በቻተም ሀውስ የዩክሬን ፎረም ኃላፊ ኦሪሲያ ሉትቪክ "ትራምፕ ምን እንደሚያደርጉ በግልጽ ስላልተናገሩ ዩክሬናውያን ሐሳብ እየሰጧቸው ነው። ሐሳቡን ትራምፕ የራሳቸውን አድርገው ያቀርባሉ" ይላሉ።
እንዴት ጦርነቱ ሊቋጭ ይችላል?
ዘለንስኪ 'የድል ዕቀድ' ብለው እንዴት ጦርነቱን ማሸነፍ እንደሚችሉ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ከሩሲያ ጋር ጦርነቱ ሲያልቅ በአውሮፓ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮችን በጦርነት የተፈተኑ የዩክሬን ወታደሮች እንደሚተኳቸው ገልጸዋል።
ዩራንየም፣ ግራፋይት፣ ሊትየምን ጨምሮ ሌሎችም የዩክሬን ማዕድኖችን በጋራ ለማልማት ጥያቄ አቅርበዋል።
ሌላው የዕቅዳቸው አካል ዩክሬንን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አባል ማድረግ ነው።
"ሁሉን አቀፍ ከኒውክሌር ውጭ የሆነ ትስስር" የሚለው ሐሳባቸው በዩክሬን ደጋፊዎች የተወደሰ ሐሳብ ነው።
ዩክሬን ከሩሲያ በቀጣይም ስጋት ውስጥ እንዳትገባ ማድረግ ይሻሉ።
ዩክሬን "የዩሮ አትላንቲክ ጥምረት አባል ለመሆን የማይቀለበስ ውሳኔ ላይ ደርሳለች" የተባለ ቢሆንም አሜሪካ እና ጀርመን ገና ድጋፋቸውን አልሰጡም።
ዩክሬን አባልነቷ የሚረጋገጠው በዓለም አቀፍ መድረክ ዕውቅና በተሰጣቸው ድንበሮቿ እንደሆነ ዘለንስኪ ተናግረዋል።
ይህም ጦርነቱን ሊያስቆም እንደሚችል ለስካይ ኒውስ ተናግረዋል።
የዩክሬንን ድንበር በዲፕሎማሲያዊ ሒደት የማስመር አካሄድን በተመለከተ የቀረበላቸው ጥያቄ እንደሌለ ገልጸዋል።
ትራምፕ መር የሰላም ንግግር ወይም የኔቶ አባልነት ጥያቄ ውጥስ ከገቡ ቀጣዩ አካሄድ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው አጠያያቂ ነው።
የዩክሬን መገናኛ ብዙኃን ኃላፊ አንድሪ የርማክ "ጠንካራና ሊተገበር የሚችል ሕጋዊ አካሄድ ያስፈልጋል" ይላል።
"ከዚህ ቀደም ተገብተው የነበሩ ቃሎች ደኅንነታችንን ማረጋገጥ አልቻሉም" ሲልም ያክላል።
በኔቶ መመሥረቻ ስምምነት አንቀጽ 5 ላይ ያለው የጋራ መከላከል የማይተገበር ከሆነ ሩሲያ ሌላ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል ስጋት እንዳላቸው ተንታኞች ይናገራሉ።
በቻተም ሀውስ የዩክሬን ፎረም ኃላፊ ኦሪሲያ ሉትቪክ "ዘለንስኪ ባዶ የተኩስ አቁም ሊኖር እንደማይችል ያውቃሉ" ይላሉ።
ዩክሬን እንዴት ትጠበቃለች የሚለው ምላሽ ሳያገኝ የተኩስ አቁም ማድረግ ውጤት እንደማይኖረው ያስረዳል።
የአውሮፓ አገራት እንዴት ኃላፊነቱን መከፋፈል ይችላሉ የሚለው ላይ ውይይቶች ተደርገዋል።
በዩክሬን የሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት ከቀረቡት ሐሳቦች አንዱ ነው። ከስምነት አገራት የተውጣጡና በእንግሊዝ የሚመሩ ልዩ ኃይሎች ማሰማራት ሌላው የቀረበው አማራጭ ነው።
ተንታኙ ግን በዚህ አይስማሙም።
"የቀረው አማራጭ ምንድን ነው ስንል የቀን አማራጭ አይኖርም" ይላሉ።
እአአ በ1994 በተፈረመው የቡዳፔስት ሜሞራንደም ከሶቭየት ኅብረት መፍረስ በኋላ ያለው ድንበር ተወስኗል። የ2014 የሚንስክ ስምምነት የዶምባስን ጦርነት አስቁሟል።
እነዚህ ስምምነቶች በቀጣይ የሚመጣ ወታደራዊ እንቅስቃሴን በተመለከተ ማረጋገጫ ካልሰጡ ውጤት እንደማይኖራቸው ተንታኙ ይናገራሉ።
"ሩሲያ ጥቃት ብትፈጽም ተመጣጣኝ ምላሽ እንደሚኖር ማወቅ አለባት" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የምዕራባውያን ሚና
የዩክሬን እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ላይ ስምምነት ባይኖርም የዩክሬን አጋር አገራት የተቻላቸውን እያደረጉ ነው።
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩቴ "ሁሉም አማራጭ" ከግምት ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህም ዩክሬንን ከሩሲያ የሚሳዔልና ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ የአየር መከላከለያ መላክን ይጨምራል።
ዩክሬን የወታደር እጥረትም ገጥሟታል። የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ጸሐፊ ጆን ሄሊ የእንግሊዝ ወታደሮች በዩክሬን ሥልጠና እንዲሰጡ ለመላክ ስምምነት እንዳለ ተናግረዋረዋል።
የባይደን አስተዳደር ከሥልጣን ሳይወርድ በፊት በኮንግረስ የተፈቀደውን ያህል ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠትና ዩክሬንን ለመደገፍ ሠርቷል።
ትራምፕ ለዩክሬን እርዳታ መስጠትት ሊቀጥሉበት እንደሚችሉ፣ ሆኖም ግን የኔቶ አባላት ለመከላከያ የሚመድቡትን በጀት ከፍ እንዲያደርጉ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
የዩክሬን አጋር አገራት ሩሲያ ላይ ማዕቀብ እየጣሉም ነው።
የሩሲያን ምጣኔ ሃብት በማዳከም ለዩክሬን ድጋፍ መስጠት ነው ዕቅዳቸው።
ለአሜሪካ ኮንግረስ ቅርብ የሆኑ አስተያየት ሰጪ "ማዕቀቦች የሩሲያን ምጣኔ ሃብት እንደታሰበው አለማዳከማቸው ብስጭት አስከትሏል" ብለዋል።
15 ምዕራባውያን አገራት ማዕቀብ ቢጥሉም ውጤታማነቱ ግን ጥያቄ አጭሯል።
ሆኖም ግን የሩሲያ የኑሮ ውድነት 23% ደርሷል። በ2025 የምጣኔ ሃብት መዳከም ሊኖር እንደሚችል ተገምቷል።
"ማዕቀቦቹ ጫና ቢኖራቸውም ቁልፍ ጉዳይ አይደሉም" ብለዋል ፑቲን።
ምዕራባውያን እንደሚሉት ሩሲያ በየቀኑ በአማካይ 1,500 ወታደሮች በሞት ወይም በጉዳት እያጣች ነው።
ዩክሬን እንዲህ ያለ ቁጥር ላይ እስከምትደርስ ድረስ ምን ያህል ግዛቷ ይያዛል? የሚለው አጠያያቂ ነው።












