ዩናይትድ ከሊጉ መጀመር በፊት ግሪንውድን የተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል

ሜሰን ግሪንውድ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ሜሰን ግሪንውድ

ማንቸስተር ዩናይትድ አዲሱ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት ሜሰን ግሪንውድን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ያሳልፋል ተባለ።

ወጣቱ የክንፍ አጥቂ ተጫዋች ግሪንውድ የአስገድዶ መድፈር ሙከራ እና አካላዊ ጥቃት የሚሉ ክሶች ከቀረቡበት በኋላ ከክለቡ ተገልሎ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ጥር 2015 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ የዓይን ምስክር ተብለው በዐቃቤ ሕግ የተያዙ ምስክሮች እራሳቸውን ከክሱ ማራቃቸውን ተከትሎ እንዲሁም ክሱን የተመለከተ አዲስ ማስረጃ ተገኝቷል በሚል ቀርበውበት የነበሩት ክሶች በሙሉ ውድቅ እንዲሆኑ መደረጋቸው ይታወሳል።

ግሪንውድ ላይ ክስ ያቀረበው ዐቃቤ ሕግ ይህ ማለት ተጫዋቹ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የመገኘቱ ዕድል በጣም አነስተኛ ነው ብሏል።

ግሪንውድ የቀረቡበት ክሶች በሙሉ እንዲወድቁ መደረጋቸው ይፋ ከሆነ በኋላ “እረፍት ተሰምቶኛል” ብሎ ነበር።

የሊጉ 2023/24 የውድድር ዘመን ከአንድ ሳምንታት በኋላ ነሐሴ 5/2015 ዓ.ም. ይጀምራል።

ዐቃቤ የያዘው ክስ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ማንችስተር ዩናይትድ የራሱን የውስጥ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል።

አሁን ላይ ክለቡ በአዲሱ የ2023/24 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታውን ከዎልቭስ ጋር ነሐሴ 8 ከመጫወቱ በፊት በ21 ዓመቱ ተጫዋቹ ዙሪያ የመጨረሻ ውሳኔውን ይሰጣል።

ከቀያይ ሴጣኖቹ ጋር እስከ 2025 የሚዘልቅ ውል ያለው ግሪንውድ ቀደ ጣሊያኑ ክለብ ሊያመራ ይችላል የሚል ጭምጭምታ ሲሰማ ነበር።

ግሪንውድ ክሶቹ ከቀረቡበት በኋላ ከቡድኑ ከመገለሉም በላይ እስካሁን ድረስ በዩናይትድ ልምምድ ቦታ ዝግጅት አላደረገም።

አዲሱ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት ክለቡ ለወዳጅነተ ጨዋታዎች ወደ አሜሪካ ከመጓዙ በፊት ተጫዋቹን በተመለከተ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ሲጠየቁ በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን አመለካከት ማጋራታቸውን እና የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጡት በክለቡ ያሉ ሌሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ግሪንውድን በተመለከተ ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድ ከመጨረሻ ውሳኔ መድረሱን ከምንጮቹ የተረዳ ሲሆን ውሳኔውም ከዎልቭስ ጨዋታ በፊት ይፋ እንደሚደርግ ይጠበቃል።