የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, PM Office
ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ኦጃይ ባንጋ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያዩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የዓለም ባንክ የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት በማሳደግ ረገድ ሚና ይጫወታል በማለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሐምሌ 24/ 2015 ዓ.ም አስፍረዋል።
የዓለም ባንክ የአጋርነቱን ሚና በማስፋት፣ ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፋይናንሲንግ እና የዓገር አገፍ በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳውን በመደገፍም የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት በማሳደግ ረገድም አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ ለሁለት ቀናት በሚያደርጉት ቆይታ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ከፋይናንስ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እንዲሁም ከብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምሕረቱ ጋር እንደሚገናኙ ዓለም አቀፉ ተቋም አስታውቋል።
በቅርቡ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አጃይ ባንጋ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የዓለም ባንክ የአዲስ-ጂቡቲ የትራንስፖርት ኮሪዶርን የሚያሻሽል ገንዘብ መለቀቁን ይፋ ካደረገ ከቀናት በኋላ ነው።
ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር የተገኘው 730 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰትን እያስተናገደ የመጣው እና ለትራፊክ ምቹ ያልሆነውን የአዲስ አበባ - ጂቡቲ መንገድን ለማሻሻል ጥቅም ላይ እንደሚውል ባንኩ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር የዓለም ባንክ አንድ አካል ሲሆን፣ በድሃ አገራት ውስጥ የሚካሄዱ የድህነት ቅነሳ ተግባራትን በዝቅተኛ ወይም ካለወለድ በሚሰጥ ብድር የሚደግፍ ነው።
ይህ የፋይናንስ ድጋፍ ከሚኤሶ - ድሬዳዋ ያለውን የመንገዱን ክፍል ወደ ባለ አራት የመስመር የፍጥነት መንገድ ከፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህም ጉዞው የሚፈጀውን ሰዓት ከማሳጠሩ በላይ ነዳጅ ይቆጥባል፣ እንዲሁም ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ ፍሰትን ይፈጥራል ይላል የዓለም ባንክ።
ባሕር በር አልባ ለሆነችው እና ከ95 በመቶ በላይ የወጪ እና የገቢ ምርቶቿን የምታንቀሳቅስበት መንገዷ እንዲሻሻል መደረግ አገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴዋን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ብለዋል የፋይናንስ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ።
ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የ400 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት መፈራረማቸውን የፋይናንስ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።
ሚኒስቴሩ ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ ለሰው ሀብት ልማት አገልግሎት የሚውል የ350 ሚሊዮን ዶላር የልማት ድጋፍ እና የ50 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ብድር መፈራረማቸውን አስታውቋል፡፡
ይህ የ400 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ የትምህርት ጥራትን እና ውጤታማነትን ለማሻሻል እንዲሁም የሥርዓተ ምግብን አገልግሎት ለማጎልበት እንደሚውል እና ከአገልግሎቱም በመላ አገሪቱ የሚገኙ ልጃገረዶች እና ታዳጊ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ የኢትዮጵያ ጉብኝት ትኩረት ለወጣቶች እና ለሴቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕድል ይሆናል የተባለ ሲሆን፤ ዛሬ በሚጀምረው የሁለት ቀናት ጉብኝታቸው የጨርቃ ጨርቅ እና ጫማ ማምረቻ ተቋማትን እንደሚጎበኙ እንዱሁም በአስተኛ ንግድ ባለቤት ከሆኑ ሴቶች ጋር እንደሚገናኙ ተቋሙ የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከአገሪቱ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት ጋር ተገናኝተው የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ኅብረት ትብብራቸውን በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ።












