ጎረቤቶችን እንቅልፍ በመንሳት የተከሰሰው አውራ ዶሮ እንዲታረድ የናይጄሪያ ፍርድ ቤት ወሰነ

 አውራ ዶሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ናይጄሪያ ውስጥ ጉዳዩ ፍርድ ቤት የደረሰው ጩኸቱ ጎረቤቶችን ሰላም የነሳው አውራ ዶሮ በድምጽ ብክለት ምክንያት እንዲታረድ ተፈረደበት።

በአንድ አውራ ዶሮ ምክንያት እንቅልፍ አጣን ያሉት ናይጄሪያውያን ለፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ነው ባለቤቱ አውራ ዶሮውን እስከ መጪው አርብ ድረስ እንዲያርደው መወሰኑን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡት።

በሰሜናዊ ናይጄሪያ ካኖ ግዛት ውስጥ የሚገኘው ፍርድ ቤት ሁለት ሰዎች የአውራ ዶሮው የማይቋረጥ ጩኽት ሰላም አሳጣን፣ እንቅልፍ ነሳን በማለት ነበር የቀረበለትን ክስ ተከትሎ ነው ብይን የሰጠው።

በዶሮው እና በባለቤቱ ላይ ክስ ካቀረቡት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ግለሰብ ዩሱፍ ሙሐመድ፣ የአውራ ዶሮው ጩኽት በቤቱ ውስጥ የሰላም እንቅልፍ የማግኘት እና የማረፍ መብቱን እንደጣሰበት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

የአውራ ዶሮው ባለቤት ኢሲያኩ ሹይቡ የቀረበውን ክስ ተከትሎ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ዶሮውን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነገ አርብ ለሚከበረው የስቅለት በዓል ለቤተሰቦቹ እንደገዛው እና ብዙ ጊዜ አለመቆየቱን ተናግሯል።

የአውራ ዶሮው ጩኽት ሰላም አሳጣን ያሉት ጎረቤቶቹም ዶሮው ለበዓሉ አርብ ዕለት የሚታረድ በመሆኑ ጥቂት ቀናት ብቻ እንዲታገሱት ጠይቋል።

የነዋሪዎቹን አቤቱታ የተመለከቱት ሃሊማ ዋሊም ማከሰኞ ዕለት በዋለው ችሎት የዶሮውን ባለቤት ጥያቄ ተቀብለው፣ ዶሮው እስኪታረድ ድረስ የነዋሪዎቹን ሰላም በሚነሳ ሁኔታ በአካባቢው እንዳይለቀቅ እና በአንድ ቦታ እንዲወሰን አዝዘዋል።

በተጨማሪም ዳኛዋ የአውራ ዶሮው ባለቤት በገባው ቃል መሠረት ዶሮውን አርብ ዕለት በማረድ ለጎረቤቶቹ አቤቱታ ምላሽ እንዲሰጥ አዘዋል።

ነገር ግን ይህንን ባይፈጽም ቅጣት እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀውታል።

በአውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ አገራት ከትንሳኤ በዓል በፊት የሚታሰበው የስቅለት በዓል ነገ አርብ መጋቢት 29 የሚከበር ይሆናል።

በናይጄሪያም ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለት ዕለት ዕለቱን በአብያተ ክርስቲያናት በመሰብሰብ አስበው የሚውሉ ሲሆን፣ ወደ ቤታቸውም ሲመለሱ በአቅማቸው የተለያዩ ምግቦችን አዘጋጅተው በጋራ ይመገባሉ።