አውሮፕላን እያበረረ ከገዳይ እባብ ጋር የተፋጠጠው ፓይለት ብሔራዊ ጀግና ተባለ

የፎቶው ባለመብት, RUDOLPH ERASMUS
ደቡብ አፍሪካዊው ሩዶልፍ ኢራስመስ የተባለ አውሮፕላን አብራሪ እያበረረ ሳለ ከአደገኛ እባብ ጋር በመጋፈጡ አውሮፕላኑን ለማሳረፍ ተገደደ።
በ11ሺህ ጫማ እየተጓዘ የነበረውን አውሮፕላን ለማሳረፍ የተገደደው ካፒቴን ኢራስመስ ነገሩ እንግዳ እንደሆነበት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከማብረሪያ ክፍል መቀመጫ ሥር አንዳች ነገር እግሩን ሲዳብሰው እየተጎነጨው የነበረ የውሃ ላስቲክ መስሎት ነበር።
ቀስ እያለ ስሜቱ ወደ ታፋው ሲሰማውና የሆነ የሚንቀሳቀስ ነገር እንዳለ ሲያውቅ ግን ግራ ገባው።
“ምናልባት የፈሰሰ ዉሃ እየነካኝ ይሆን ብዬ አሰብኩ” ይላል ካፒቴን ኢራስመስ።
አንድ አፍታ ከሚያበረው አውሮፕላን ሰማይ ወደ መቀመጫው ጎንበስ ባለ ጊዜ ግን የተመለከተውን ማመን አቃተው። ግዙፍ እባብ መልሶ አፈጠጠበት።
ካፒቴኑ በዚያው ቅጽበት ሳይረበሽ አውሮፕላኑን ፕሪቶሪያ አየር ማረፊያ ለማሳረፍ ተገዷል።
ይህ የግል አውሮፕላን አራት ሰዎችን አሳፍሮ ነበር።
ኬፕ በሚል ቅጽል የሚጠራው እባብ አንዴ ከነደፈ ገዳይ ሲሆን አንድ ሰው በዚህ እባብ ተነድፎ በሕይወት ሊቆይ የሚችለው ለግማሽ ሰዓት ብቻ ነው።
ካፒቴን ኢራስመስ “ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ፤ ለተሳፋሪዎች ከተናገርኩ መረባበሽ ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርሃት ሰቅዞ ያዘኝ” ብሏል በወቅቱ ስለተሰማው ስሜት ለቢቢሲ ሲያጋራ።
በመጨረሻም በተረጋጋ ሁኔታ ‘ክቡራትና ክቡራን ተሳፋሪዎች፤ አንድ እባብ አብሮን ተሳፍሯል። እግሬ ሥር እየተርመሰመሰ ነው፤ ተረጋግተን አውሮፕላኑን እናሳርፈዋለን” ብሎ ተሳፋሪዎች ፍጹም ተረጋግተው እንዲቆዩ ተናገረ።
በዚህ ጊዜ በአራቱ ተሳፋሪዎች ዘንድ ድንጋጤው ወደ ፍጹም ዝምታና ጸሎት ተቀየረ።
“በዚያ ቅጽበት መርፌ ብትወድቅ ራሱ ይሰማል፤ ሁሉም ጸጥ ረጭ ብሎ ነበር” ይላል ኢራስመስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካፒቴን ኢራስመስ ለቢቢሲ የተሰማውን ስሜት ሲያስረዳ አንድ አውሮፕላን አብራሪ ብዙ ያልተጠበቁ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ብዙ ስልጠና ይሰጠዋል። እባብን ማብረሪያ ክፍል ውስጥ ስለመጋፈጥ ግን ሰልጥነን አናውቅም ሲል ነገሩ ፍጹም ያልተጠበቀ እንደሆነ አብራርቷል።
በዚያ ሰዓት እንደምንም ተረጋግቶ አውሮፕላኑን ማሳረፍ ባይችል ኖሮ የከፋ አደጋ ሊደርስ እንደሚቸል ተናግሯል።
አውሮፕላኑ በመጨረሻ ዌልኮም ከተማ አርፏል።
ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው ይህ አውሮፕላን ከመነሳቱ በፊት ሌሎች ሁለት በአውሮፕላን ጣቢያ የሚሰሩ ሰዎች አንዳች ተሳቢ ነገር ሲንቀሳቀስ አይተን ነበር፤ ነገር ግን ድንገት ተሰወረብን፤ አውሮፕላን ውስጥ መግባቱን አላወቅንም ብለዋል።
ካፒቴን ኢራስመስም አውሮፕላኑን ከመሳፈራቸው በፊት ውስጡን መፈተሻቸውንና ምንም እንዳላገኙ ተናግሯል።
የደቡብ አፍሪካ የሲቪል አቪየሽን ኮሚሽነር ካፒቴን ኢራስመስ “በተመለከተው አስፈሪ ነገር ሳይረበሽ አውሮፕላኑን በሰላም በማሳረፉ ብሔራዊ ጀግና ነው” ሲሉ አሞካሽተውታል።












