ከጉግል ውጭ መጠቀም የምንችላቸው ‘የመረጃ ማሰሻዎች’ እንዳሉ ያውቃሉ?

መረጃ ማሰሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአንድ ቀን ስንት ጊዜ ‘ጉግል’ ያደርጋሉ? ጉግል በእያንዳንዱ ሰከንድ 63 ሺህ ጥያቄዎች እንደሚጠየቅ በገጹ ጽፏል። በቀን ውስጥ ወደ 5.6 ቢሊዮን ገደማ ጥያቄዎች ያስተናግዳል።

ብዙዎቻችን ከቃላት ትርጉም አንስቶ ስለማንኛውም ጉዳይ ‘አማካሪያችን’ ጉግል ከሆነ ቆይቷል።

የመረጃ ደኅንነት ባለሙያዎች ግን ጉግል መረጃ ሲሰጠን በምላሹ የእኛን መረጃ እየወሰደ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የእኛን ማንነት፣ ምን እንደምንወድ፣ ምን እንደምንጠላ፣ ምን ማድረግ እንደምንፈልግ፣ ምን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንደምንችል፣ የት መሄድ እንደምናዘወትር ወዘተ ይመዘግባል።

ስለእኛ የሚከማቸው የተደራጀ መረጃ ለማስታወቂያ ድርጅቶች ወይም የተለያየ ምርት ለሚሸጡ ተቋሞች ይሸጣል።

መረጃው የሚሰበሰበው የኢሜይል መገልገያውን ጂሜይልን እና ዩቲዩብን ጨምሮ ከሁሉም ከጉግል ጋር የተያያዙ ገጾች ነው።

ይህ መረጃ፣ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች በፍላጎታቸው፣ በዘራቸው፣ በዕድሜያቸው፣ በጾታቸው እንዲሁም በሌሎች የማንነት መገለጫዎቻቸው ልክ የተሰፋ ማስታወቂያ (targeted ad) ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል የሚለው አንደኛው ትችት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ የግል መረጃ ለሦስተኛ ወገን ከተላለፈ በኋላ ሰዎች የት እንዳሉ፣ ከማን ጋር ምን እንደተነጋገሩ፣ ምን እንደሸመቱ እና ሌሎችም መረጃዎች በምስጢር አለመያዛቸው ነው።

ትችቶቹ የሚሰነዘሩት ጉግል ላይ ብቻ አይደለም። ሌሎች መረጃ ማሰሻ (search engine) አቅራቢዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች ላይም ነው።

ጉግል ግንባር ቀደሙ እና በርካታ ተጠቃሚ ያለው መረጃ ማሰሻ ስለሆነ ነው በትችቱ በዋነኛነት የሚነሳው።

ጉግል ከግል መረጃ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘርበትን ወቀሳ ተከትሎ ‘የተሻለ አማራጭ አለን’ የሚሉ ሌሎች መረጃ ማሰሻ አቅራቢዎች ወደ ገበያው ገብተዋል። እነሱስ ምን ያህል ይታመናሉ? ሌላ ጥያቄ ነው።

ባለንበት ፈጣን የመረጃ ዘመን የግል መረጃን ምን ያህል ምስጢራዊ አድርጎ መቀጠል ይቻላል? የሚለው አጠያያቂ ነው። ቢያንስ ግን የግል መረጃችንን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በተሻለ ደረጃ የሚጠብቁ ከጉግል ውጭ ያሉ መረጃ ማሰሻዎችን በዚህ ዘገባ እንመለከታለን።

ስለ አማራጭ መረጃ ማሰሻዎች እንዲነግረን የጠየቅነው የአይኮግ ላብስ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ጌትነት አሰፋን ነው። ከ200 በላይ ፕሮግራመሮች ያለው ተቋሙ ላለፉት አሥር ዓመታት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እንዲሁም ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ይሠራል።

መረጃ ማሰሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጉግል ከእኛ ምን ይፈልጋል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በነገራችን ላይ ከጉግል በፊት ሌሎች የመረጃ ማሰሻዎች ነበሩ። ጉግል ሲመጣ ግን መረጃ ማሰሻዎቹን ጠቀለላቸው። አሁን በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ ያገኛል።

ለመሆኑ ጉግልን የሚደርስበት መረጃ ማሰሻ አለ?

“ለምሳሌ ማይክሮሶፍት፣ ቢንግ ሞክረዋል። ነገር ግን ጉግል ላይ ሊደርስ የሚችል እስካሁን አልተገነባም። አሁንም ጉግል ትልቁን የገበያ ድርሻ ይወስዳል” ይላል ጌትነት።

ጉግል በተለያየ ጉዳይ ዘገባዎች፣ ጥናቶች፣ ማስፈንጠሪያዎች፣ ማብራሪያዎች ያከማቻል። ይህንን መረጃ ከእያንዳንዱ ገጽ እንፈልግ ብንል እጅግ ከባድ ነው።

ስለዚህ ጉግል እነዚህን በአጭር ቃላት በማስቀመጥ ወይም ‘ኢንዴክስ’ በማድረግ ለአጠቃቀም ምቹ አድረጎ ያቀርባል።

እኛም ስለ እያንዳንዱ ነገር ለማወቅ ወደተለያየ ገጽ እየሄድን ከመታከት ሁሉንም መረጃ ለማግኘት ወደ ጉግል እናመራለን።

ጉግል አዲስ ተጠቃሚ ሲመዘግብ ዘለግ ያለ የአጠቃቀም ደንብ እና መመሪያ ያቀርባል። ተርታው ሰው ዝርዝሩን ለማንበብ ጊዜ ወይም ፍላጎት በማጣት ‘እስማማለሁ’ ብሎ ይመዘገባል።

ብዙዎች የግል መረጃቸው ሊወሰድ እንደሚችል ሲነገራቸው ‘ምንም የምደብቀው የለኝም’ ብለው ሲመልሱ ይደመጣሉ።

ነገር ግን መረጃዎች የሚሰበሰቡበትን ጥልቀት እና ኋላ ላይ ተጠቃሚዎች ላይ ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ ጫና ለማሳደር የሚኬድበትን ርቀት ሲገነዘቡ ይደናገጣሉ።

ጉግል መረጃችንን የሚወስደው ፈቅደንለት ነው። ፍርድ ቤት ሄደን ብንከስ ‘እስማማለሁ’ ያልነውን ደንብና መመሪያ እንደ ማስረጃ ያጣቅሳል።

“ማንኛውም በነጻ አገልግሎት የሚሰጥ የቴክኖሎጂ ተቋም ትርፍ የሚያገኘው ከማስታወቂያ ነው። የሰዎችን የግል ዳታ (መረጃ) በብዛት ይሰበስባሉ። ይሄ ሮው ዳታ [መረጃው ሳይብላላ] ሆኖ ይሸጣል ወይም ለታርጌትድ አድ [ተጠቃሚ ላይ ያነጣጠረ ማስታወቂያ] ይውላል። ጉግል ይህን እንዲያደርግ ደግሞ ፈቅደንለታል” ሲል ጌትነት ያስረዳል።

የመረጃ ማሰሻ ተቋሞች ሥራ መረጃን ወደ ገንዘብ መለወጥ ነው። ያውም በቢሊዮን ዶላር ወደሚቆጠር ገንዘብ መቀየር።

አገልግሎታቸውን በነጻ ሲሰጡን ‘ደግ’ ሆነው ሳይሆን ከእኛ የሚገኘው መረጃ በብዙ እጥፍ ስለሚያተርፍ ነው።

“ጉግል ዳታችንን እንዴት እንደሚጠቀም ቀድሞ ይገልጻል። ረዥም ጽሑፍ ነው። ብዙ ጊዜ አናነበውም። በፖሊሲው ያልተስማማ ሰው እንዲገባ አይፈቀድለትም” ይላል ጌትነት።

ተጠቃሚዎች መረጃቸውን ከጉግል መጠበቅ ይችላሉ? ስንል ለባለሙያው ጥያቄ ሰንዝረናል።

የኢንተርኔት መረጃ መፈለጊያ ቦታ መፈለጊያ

ከጉግል ሌላ ምን አማራጭ አለን?

ጌትነት እንደሚለው፣ ጉግል የግል መረጃችንን እንዳያገኝ መደበቅ እንችላል። ያ ማለት ግን ጉግል የሚሰጠን መረጃ መጠን ይገደባል ማለት ነው።

ለምሳሌ ክሮም ላይ ስማችንን እና ኢሜል አድራሻችንን ጠቅሰን [ሳይን ኢን አድርገን] የምናገኘው መረጃ እና ሳንጠቅስ የሚመጣው መረጃ የተለያየ ነው።

ማንነታችንን ስንጠቅስ ቀድሞ ካደረግነው የመረጃ አሰሳ በመነሳት ጉግል ተዛማጅ መረጃዎችን ያመጣል። ይህም የምናገኘውን መረጃ ለእኛ ‘ተስማሚ’ ያደርገዋል። አለበለዚያ ግን ያልተመረጠ መረጃ ስብስብ ይቀርብልናል።

ጉግል ባለው መረጃ ብዛት ተመራጭ ሲሆን፣ የግል መረጃችን መሰብሰብ ጉዳይ ደግሞ ያሰጋናል።

ስለዚህ ምስጢራዊነታችንን ለመጠበቅ ሌሎች መረጃ ማሰሻዎች ብንጠቀምስ?

ይሄንን አማራጭ የሚያበረታቱ ባለሙያዎች አሉ። በሌላ በኩል መረጃ ማሰሻዎች ቀዳሚ ገቢያቸው ማስታወቂያ እስከሆነ ድረስ ‘የግል መረጃችሁን አንወስድም፣ አናከማችምም’ ብለው ቢምሉ ቢገዘቱም ማመን ይቸግራል ብለው የሚከራከሩ አሉ።

ደክደክጎ (DuckDuckGo)፣ ሴርኤክስ (searX)፣ ስታርትፔጅ (Startpage)፣ ሜታጊር (MetaGer)፣ ኩዋንት (Qwant) እና ሌሎችም የመረጃ ማሰሻ አማራጮችን መጠቀም የሚመክሩ አሉ።

እነዚህ መረጃ ማሰሻዎች ቃል የሚገቡት፣ የግል መረጃ ላለማከማቸት ወይም የሚሰበሰብ መረጃን በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ለመደምሰስ፣ ተጠቃሚዎች ያሉበትን ቦታ ላለመከታተል፣ ተጠቃሚዎች ያሰሱትን መረጃ ላለመሰብሰ ወይም ላለማጋራት ነው።

አንዳንድ መረጃ ማሰሻዎች የሚሠሩት በተወሰኑ አገራት ተገድበው ነው። ለምሳሌ አምና ሥራ የጀመረው ኒቫ (Neeva) አገልግሎት የሚሰጠው በዩናይትድ ኪንግደም፣ በፈረንሳይ እና በጀርመን ነው።

መሥራቹ የቀድሞ የጉግል ማስታወቂያ ክፍል አለቃ ሲሆን፣ ያስተዋወቀው መረጃ ማሰሻ ‘ከማስታወቂያ ነጻ፣ ተጠቃሚዎችን የማይከታተል’ እንደሆነ ገልጿል።

መረጃ ማሰሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የግላዊ መረጃችን ደኅንነት ጉዳይስ?

ጌትነት እንደሚለው፣ ቢንግ [Bing]፣ ያሁ [Yahoo!]፣ ባይዱ [Baidu]፣ አዎል [AOL]፣ አስክዶትኮም [Ask.com]፣ ኤክሳይት [Excite] ወደ ገበያው የገቡት መረጃችሁን አናስቀምጠውም፣ መረጃችሁን እንጠብቅላችኋለን፣ መረጃችሁ የእኛ አይደለም፣ ከስድስት ወር በኋላ ግላዊ መረጃችሁ ይሰረዛል ወዘተ ብለው ነው።

“. . .ዳታዬ ተጠብቋል ወይ? ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። ተጠቃሚዎች ምን ያህል የግል መረጃቸው እንዲጠበቅ ይፈልጋሉ? ምን ያህልስ ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ይፈልጋሉ? የሚለውን አመዛዝነው [የሚሆናቸውን መረጃ ማሰሻ] መምረጥ ይኖርባቸዋል” ሲል ያስረዳል።

የግል መረጃችንን እንደሚጠብቁ ቃል የሚገቡት ገጾች ምን ያህል የይዘት ክምችት አላቸው? የሚለው ላይ ጌትነት ጥያቄ ያነሳል።

ስለዚህ ተጠቃሚዎች የማገኘው መረጃ ቢበዛ ይሻላል? ወይስ የግል መረጃዬ ተጠብቆ ቢቆይ? በሚሉ ምርጫዎች መካከል ይወድቃሉ።

አሁን አሁን በተለያዩ ገጾችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች የምናደርገው እንቅስቃሴ በአጠቃላይ እየተመዘገበ ነው። ለምሳሌ ቴሌግራም፣ ዋትስአፕ፣ ጉግል፣ ኢሜል ስንጠቀም መረጃችን ወደ አንድ ቋት መጓዙ እንደማይቀር ጌትነት ይናገራል።

የቴክኖሎጂ ተቋሞች ኃያል እየሆኑ የመጡትም በዚህ የመረጃ ክምችት ነው። ለዚህ ነው ባለሙያው ሌሎች መረጃ ማሰሻዎችን “እንደ አማራጭ ቢወሰዱም የየራሳቸው ክፍተት አላቸው” ሲል ነው የሚመክረው።

ብዙዎች ከጉግል እንደተሻለ አማራጭ የሚጠቀሙት መረጃ ማሰሻ ደክደክጎ ወደ 80 ሚሊዮን ተጠቃሚ አፍርቷል።

ባለሙያው ይህ መረጃ ማሰሻ በቀጥታ መረጃ ባይወስድም በሌሎች እንደ ኩኪ ዳታ (cookie data) ያሉ መንገዶች እንቅስቃሴያችንን ማወቁ እንደማይቀር ያስረዳል።

ሆኖም ግን ተጠቃሚዎች “እንደ አማራጭ ሊወስዱት ይችላሉ” ይላል።