የግብፅ እና የሱዳን ባሕር ኃይሎች የጋራ የጦር ልምምድ አደረጉ

የግብጽ ባሕር ኃይል መርከብ በስዊዝ ካናል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግብጽ ባሕር ኃይል መርከብ በስዊዝ ካናል

የግብፅ እና የሱዳን ባሕር ኃይሎች በቀይ ባሕር ላይ የጋራ የጦር ልምምድ ማድረጋቸውን የግብፅ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሁለቱ አገራት ለበርካታ ቀናት የቆየውን የጦር ልምምዱን ያካሄዱት በሱዳን ወደብ ባለ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

የሱዳን እና የግብፅ የጦር ልምምድ በዋናነት የባሕር ላይ ደኅንነትን ለመጠበቅ እና የጋራ ጠላት የሚደቅንባቸውን የደኅንነት ስጋትን ለመመከት ያለመ መሆኑን በመግለጫው ተመልክቷል።

የጋራ የጦር ልምምድ የተደረገው “የግብፅ ጦር በተለያዩ ዘርፎች ከወንድም እና ወዳጅ አገራት ጋር ወታደራዊ ትብብርን ለማሳደግ ባዘጋጀው የሥልጣና ዕቅድ ማዕቀፍ አማካይነት ነው” ተብሏል።

የሁለቱ አገራት የጦር ልምምድ በቀይ ባሕር ላይ የባሕር ኃይል ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ ሕገ ወጥ ስደተኞች እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር፣ ፀረ ሽብር እና የጋራ ጠላትን ለመመለከት ያለመ ስለመሆኑ የግብፅ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሰሜን ምሥራቃዊ የአፍሪካ ክፍል ውስጥ ቀይ ባሕርን ተጋርተው የሚገኙት ጎረቤታሞቹ ግብፅ እና ሱዳን ወታደራዊ ትብብር በማድረግ ለዓመታት የቆየ ወዳጅነት አላቸው።

በተለይም ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ያለው ኢትዮጵያ በምትገናባው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ውዝግብ መከሰቱን ተከትሎ ግብፅ እና ሱዳን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወታደራዊ ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን አድርገዋል።

አብዛኛው ውሃው ከኢትዮጵያ በሚመነጨው እና በዋናነት ግብፅ እና ሱዳን በሚጠቀሙት የአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ባለው ግዙፍ ግድብ ምክንያት ሦስቱ አገራት ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።

ግንባታው ከአስር ዓመታት በላይ በወሰደው እና ሊጠናቀቅ የተቃረበው ግድብ ከአባይ ወንዝ የሚያገኙትን የውሃ መጠን ይቀንስብናል በማለት ግብፅ እና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ የግድቡን የውሃ ሙሌት መጀመሯን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ወታደራዊ ልምምዶችን ሱዳን ውስጥ ማካሄዳቸው ተዘግቦ ነበር።

የአሁኑ የጦር ልምምድ በባሕር ኃይሎቻቸው አማካይነት ቀይ ባሕር ላይ የተደረገ ሲሆን፣ አላማውም የጋር ደኅንነት ስጋትን በጋራ መከላከል መሆኑ ተገልጿል።