ታሊባን አፍጋኒስታናውያን ሴቶችን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥራ አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አፍጋኒስታንን የሚያስተዳድረው ታሊባን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚሠሩ የአገሩ ሴቶችን ከሥራ ማገዱን ድርጅቱ አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው ከሆነ ታሊባን ውሳኔውን በጽሑፍ ሳይሆን በቃል ነው ያስተላለፈው።
ከታሊባን ጋር በሚደረጉ ስብሰባዎች በጉዳዩ ላይ ግልጽ መረጃ እስኪገኝ ለ48 ሰዓታት ወደ ሥራ እንዳይገቡ ድርጅቱ ለአፍጋኒስታናውያን ሴት ሠራተኞቹ መረጃ አስተላልፏል።
ታሊባን ሥልጣኑን እአአ በ2021 መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ በሴቶች ነፃነት ላይ እየደረሰ ያለው ጭቆና እየበረታ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እርምጃውን “ተቀባይነት የሌለው እና በፍፁም የማይታሰብ ነው” ብሎታል።
የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ “ይህ ውሳኔ የእርዳታ ድርጅቶች የተቸገሩትን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት የሚጎዳ እና አሳሳቢ አዝማሚያ ነው” ብለዋል። አክለውም “ያለ ሴት ሠራተኞች የሕይወት አድን ድጋፍ እርዳታን ማድረስ አይቻልም” ብለዋል።
ሴት ሠራተኞች ለእርዳታ ሥራዎች በተለይም የተቸገሩ ሌሎች ሴቶችን በመለየት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በከፋ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው አፍጋኒስታን ለ23 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ሲሠራ ቆይቷል።
የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው የድርጅቱ ሴት ሠራተኞችን እገዳው አይመለከታቸውም።
ይህ የአሁኑ ውሳኔ ተግባራዊ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ግን አፍጋኒስታን ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ሥራዎችን እና በድርጅቱ እና በታሊባን መንግሥት መካከል ላለው ግንኙነት ፈተና ይሆናል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው የታሊባን ባለሥልጣናት በምሥራቅ ናንጋርሃር ግዛት የአፍጋኒስታን ሴቶች ማክሰኞ ዕለት ለድርጅቱ ተቋማት እንዳይሠሩ ከለከሏቸዋል።
የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትዊተር ገፃቸው “የአፍጋኒስታን ሴት ባልደረቦቻችን በናንጋርሃር ግዛት እንዳይሠሩ መከልከሉን አጥብቄ አወግዛለሁ። ይህ እርምጃ ካልተቀየረ የሕይወት አድን እርዳታን ለሚፈልጉ ሰዎች የመድረስ አቅማችን መጉዳቱ አይቀሬ ነው” ብለዋል።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር መንግሥታዊ ላልሆኑ የጤና ድርጅቶች እና ለተመድ ከሚሠሩ ውጭ ሴቶች እንዳይሠሩ ታሊባን ይፋዊ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።
አሁን ይህ ውሳኔ የተቀለበሰ ይመስላል፤ በጤና ተቋማት የሚሠሩ ሴቶች ፈቃድ የሚያገኙት በቀጥታ ከጤና ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ከሆነ ብቻ ነው።
ታሊባን ወደ ሥልጣን ከተመለሰ በኋላ ታዳጊዎች እና ሴቶች ከትምህርት ቤት እና ከኮሌጅ ታግደዋል። ሴቶች ዐይናቸውን ብቻ በሚያሳይ መልኩ እንዲለብሱ እና ከ 72 ኪ.ሜ በላይ የሚጓዙ ከሆነም ከወንድ ዘመድ ጋር አብረው መሆን ይኖርባቸዋል።
ባለፈው ኅዳር ወርም ሴቶች ከፓርኮች፣ ከጂሞች እና ከመዋኛ ስፍራዎች ታግደው ነበር።
ታሊባን የሴቶች ትምህርት ተሟጋቾች ላይም እርምጃ ወስዷል። የአፍጋኒስታን የሴቶች እንዲማሩ የሚያበረታታው ማቲዩላህ ዌሳ ባልታወቀ ምክንያት ታስሯል።
የታሊባን መንግሥት በሴቶች ላይ የጣለውን የትምህርት እገዳ የተቃወሙት ፕሮፌሰር እስማኤል ማሻል በየካቲት ወር ካቡል ውስጥ መጽሐፍትን በነፃ ሲያድሉተይዘዋል።












