የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ግንኙነት መሻሻል በትግራይ ያለው ሁኔታ ወሳኝ ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነቱ ምክንያት የሻከረውን ግንኙነት የማሻሽለው “ቀስ በቀስ፤ ደረጃ በደረጃ” ነው አለ።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳዮች ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሻሽለው በጊዜ ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።
ቦሬል ይህን ያሉት ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በአሜሪካ እና ኅብረቱ መካከል ስላለው ግንኙነት ብራሰልስ ውስጥ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሮ ነበር ያሉ ቦሬል፤ እንደመታደል ሆኖ በአሁኑ ወቅት ችግሮች መፍትሄ እያገኙ ነው ብለዋል።
“በዓለማችን ካሉት አዎንታዊ ዜናዎች መካከል አንዱ ይህ ነው” ሲሉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለማስቆም የተወሰዱ አዎንታዊ እርምጃዎችን ገልጸዋል።
“የተጀመሩ ለውጦችን ለማስቀጠል የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ እጅ ለእጅ ሆነው አብረው መሥራታቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል” ብለዋል ቦሬል።
ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለትግራይ ያለን መልዕክት ግጭቱን ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በቅርበት እየተከታተልን መሆኑን እንዲረዱ ነው ያሉ ጆሴፍ ቦሬል፣ ኅብረቱ ከጦርነቱ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን ግንኙነት የሚያድረሰው “ቀስ በቀስ፤ ደረጃ በደረጃ ነው” ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ተዋጊ ወገኖች መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙት የመብት ጥሰቶች ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከሉ ናቸው ብሎ ነበር።
ይህን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር የነበራት ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል። ኅብረቱም ለኢትዮጵያ መንግሥት ይሰጥ የነበረውን የ90 ሚሊዮን ዩሮ የበጀት ድጋፍ እንዲቆም ማድረጉ ይታወሳል።
የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬልን ጨምሮ ሌሎችም የኅብረቱ ባለሥልጣናት በጦርነቱ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግሥትን አጥብቀው ሲተቹ ቆይተዋል።
ለመንግሥት ከሚሰጠው የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት በዓመት በአማካይ 214 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ድጋፍ ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ የኅብረቱ ድረ ገጽ ያመለክታል።
ሩሲያ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ
ጆሴፍ ቦሬል እና አንቶኒ ብሊንከን በብራሰልስ በነበራቸው ውይይት ላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሩሲያ እና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል።
ቦሬል “ፑቲን ዩክሬንን የማውደውም ተግባሩ ቀጥሏል ካሉ በኋላ የኒውክለር ጦር መሳሪያ በቤላሩስ መጥመዱ የአውሮፓን ደኅንነት አሳሳቢ አድርጎታል” ብለዋል።
ሩሲያ በቤላሩስ የኒውክለር ጦር መሳሪያ የተከለችው የቻይናው ፕሬዝዳንት የሞስኮ ጉብኝነት በኋላ መሆኑን ያስታወሱት ቦሬል፤ ከብሊንከን ጋር በነበራቸው ውይይት ቤይጂንግ ለሞስኮ ድጋፍ ማድረጓ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርን ስለመጣሷ ተነጋግረናል ብለዋል።
ቦሬል ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ጦርነት ቻይና ድጋፏን እንዳትሰጥ ጫና ለማድረግ እራሳቸውን ጨምሮ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን እና የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በቀጣይ ቀናት ወደ ቤይጂንግ እንደሚያመሩ ገልጸዋል።
ቦሬል ከብሊንከን ጋር በነበራቸው ውይይት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ደኅንነቷን ለማረጋገጥ በቅጠረኛው የሩሲያ ቡድን ዋግነር ላይ እንዳትመረኮዝ ዓለም አቀፍ ድጋፎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
የኅብረቱ ከፍተኛ ኃላፊ ዋግነር በተሰማራባቸው አገራት ችግር በመፈጠር ለቀጠናው የደኅንነት ስጋት ነው ብለዋል።












