በኢየሩሳሌም ሙስሊሞች እና አይሁዶች ይገባናል በሚሉት ቅዱስ ስፍራ ግጭት ተቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ስፍራ የእስራኤል ፖሊስ ከበርካታ ፍልስጤማውያን ምዕመናን ጋር መጋጨቱ ተገለጸ።
ፖሊስ እንዳለው ግጭቱ የተቀሰቀሰው ‘ችግር ፈጣሪ’ ያላቸውና ርችት፣ ዱላ እና ድንጋይ የያዙ ሰዎች አል አቅሳ መስጊድ ውስጥ ገብተው መዝጋታቸውን ተከትሎ ወዲያውኑ ከበባ ካደረገ በኋላ ነው።
ፍልስጤማውያኑ በበኩላቸው ፖሊስ ቡድኑን ለማስወጣት አስለቃሽ ጭስ እና የጎማ ጥይቶችን ከተጠቀመ በኋላ 14 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
ከዚያም ቢያንስ ዘጠኝ ሮኬቶች ከጋዛ ወደ እስራኤል የተተኮሱ ሲሆን፣ በሲድሮት አቅራቢያ የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ሳይረን [ደወል] ሲጮህ ተሰምቷል።
ከተተኮሱት ሮኬቶች አምስቱ የከሸፉ ሲሆን፣ ሌሎች አራቱ ደግሞ ሰው በሌለበት ባዶ ስፍራ መውደቃቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
ለዚህ ጥቃት እስካሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን ባይኖርም በታጣቂ ቡድኑ ሃማስ ሮኬቶቹ እንደተተኮሱ ይታመናል።
የታጣቂ ቡድኑ ሃማስ ምክትል ኃላፊ ሳሌህ አል አሮሪ፣ እስላማዊ ተቋማት ላይ ጥቃት መሰንዘር ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። የቆሙበትን [ እስራኤላውያኑ] ምድር እናጠፋዋለን” ሲሉም ዝተዋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የጦር አውሮፕላኖቹ የታጣቂ ቡድኑን መንቀሳቀሻ ሥፍራ ኢላማ ማድረጋቸውን ገልጿል።
በእስራኤል ቁጥጥር ሥር በምትገኘው ምሥራቅ እየሩሳሌም የተቀሰቀሰው ግጭት የጀመረው በርካታ ፍልስጤማውያን አማኞች ከረመዳን የጸሎት ሥነ ሥርዓት በኋላ መስጊዱ ውስጥ ገብተው ከዘጉ በኋላ ነው።
ከመስጊዱ ውስጥ የተቀረጹ ቪዲዮዎች በተቃዋሚዎቹ ርችት ሲተኮስ አሳይተዋል። የእስራኤል ፖሊስም ድንጋይ ሲወረወርባቸው እንደነበርና በዚህም አንድ የፖሊስ አባል መጎዳቱን ገልጿል።
በሌላ ቪዲዮም የእስራኤል ፖሊስ ፍልስጤማውያኑን በዱላ ሲደበድብ ታይቷል።
የፍልስጤም ቀይ ጨረቃም የሕክምና ቡድኑ ወደ መስጊዱ ውስጥ እንዳይገባ በእስራኤል ኃይል መከልከሉን ገልጿል።
የፍልስጤም ታጣቂዎች ቀደም ብሎ ረቡዕ ዕለት በሚጀምረው የፋሲካ በዓል የአይሁድ እምነት ተከታዮች በመስጊዱ ውስጥ ፍየል በማረድ መስዋዕት ማድረግ እንደሚፈልጉ የሚገልጹ ሪፖርቶች መኖራቸውን በመግለጽ ሙስሊሞች መስጊዱ ውስጥ ገብተው እንዲዘጉ ጥሪ አቅርበው ነበር።
በእየሩሳሌም ላይ ያለው ተራራ በአይሁድ እምነት በጣም ጥብቅ ሃይማኖታዊ ሥፍራ ሲሆን፣ በእስልምናም ሦስተኛው ቅዱስ ስፍራ ነው።
በአይሁዶች ዘንድ ‘የተራራው ቤተ መቅደስ’ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሥፍራው ሁለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቤተ መቅደሶች አሉት። በሙስሊሞች ደግሞ ሃራም አል ሸሪፍ የሚባል ሲሆን ነብዩ መሐመድ ወደ ጀነት የወጡበት ሥፍራ እንደሆነ ይታመናል።
ሙሉ ግቢው በሙስሊሞች ዘንድ አል አቅሳ መስጊድ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ አሁን ላይ የተከሰተው ግጭትም የተቀሰቀሰው በዚሁ መስጊድ ውስጥ ነው።
አይሁዶች እና የእስልምና እምነት ተከታይ ያልሆኑ ግለሰቦች ገብተው መጸለይ ባይችሉም ወደ ግቢው መግባት ይፈቀድላቸዋል።
ይሁን እንጅ ፍልስጤማውያን በአይሁዶች የሚደረግ ጉብኝት አሁን ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ ይመለከቱታል።












