የእስራኤል የመረጃ ጠላፊዎች የኬንያ ፕሬዝዳንት ረዳቶችን ኢላማ አድርገው እንደነበር ተነገረ

ቴሌግራም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኬንያ ባለፈው ዓመት ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሁለት ረዳቶች የመልዕክት ልውውጥ በእስራኤላውያን ተጠልፎ እንደነበረ አንድ የምርመራ ውጤት አመለከተ።

የመልዕክት ልውውጥ መስመሮችን ኢላማ በማድረግ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የቅርብ ሰዎች ላይ የተደረገው የመረጃ ጠለፋ በምርጫው ውጤት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የተደረገ ሙከራ መሆኑ ተገልጿል።

የእስራኤሉ ሃሬትዝ እና የዩናይትድ ኪንግደሙ ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ በሌሎችም ጋዜጦች ላይ የታተመው ምርመራ የተደረገው በአንድ የጋዜጠኞች ስብስብ አማካይነት ነው።

በውጤቱም ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ የተደረገው ምርጫ ቀናት ሲቀሩት የመረጃ ጠላፊው ቡድን የዊሊያም ሩቶ “የፖለቲካ አማካሪዎችን የመልዕክት ልውውጥ መጥለፍ ስለሚቻልባቸው ዘዴዎችን ማብራሪያ ሰጥቷል” ሲል አጋልጧል።

መረጃ የመጥለፍ ድጋፍን የሚፈልጉ ግለሰቦች መስለው የቀረቡ ጋዜጠኞች፣ በጠላፊው አማካይነት በወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የነበሩት የዊሊያም ሩቶ የፖለቲካ አማካሪ ዴኒስ ኢቱንቢን እና የጽህፈት ቤት ኃላፊያቸው የነበሩትን ዴቪስ ቺርቺርን ጨምሮ አምስት ሰዎች ኢላማ ነበሩ።

በዚህም የአምስቱ ግለሰቦችን የቴሌግራም እና የኢሜል መልዕክቶችን እንዴት መጥለፍ እንደሚቻል ማብራሪያ መስጠታቸው ተገልጿል።

የምርመራው ውጤት የመልዕክት ጠላፋውን ያካሄዱት ‘ታል ሃናን’ በተባለ የደኅንነት ወኪል አማካይነት በሚመሩ የቀድሞ የእስራኤል ልዩ ኃይል አባላት እንደሆነ አመልክቷል።

ሃናን የተባለው ግለሰብ የባለሥልጣናቱን አካውንቶች በመጥለፍ “መረጃዎችን በመሰብሰብ ዊሊያም ሩቶ በፕሬዝዳንትነት ለመመረጥ እያደረጉት በነበረው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ መረጃ የማዛባት ዘመቻን” የሚያካሂድ ቡድንን እንደመራ መናገሩ ተጠቅሷል።

የምርጫው ቅስቀሳ ወደ መጠናቀቁ በተቃረበበት ጊዜ የሩቶ የፖለቲካ አማካሪ የነበሩት ዴኒስ ኢቱምቢ በቴሌግራም አካውንታቸው ላይ ያልተለመዱ ነገሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን በመገንዘባቸው፣ ለምንም አይነት ግንኙነት መጠቀም እንዳቆሙ አሳውቀው ነበር።

ነገር ግን ይፋ የተደረገው ምርመራ ጠለፋ ያካሄደው ቡድን ሥራውን እንዲያከናውን በማን እንደተቀጠረ ይፋ አላደረገም። ይህንንም በተመለከተ የኬንያ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎች ምንም አይነት አስተያየት አልሰጡም።

በዊሊያም ሩቶ የምርጫ ዘመቻ ወቅት መረጃዎችን በመጥለፍ ተደረጓል የተባለው ሙከራ ግን ፖለቲከኛውን በምርጫው አሸንፈው ሥልጣን ከመያዝ አላገዳቸውም።

የሩቶ ተፎካካሪ የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ራይላ ኦዲንጋ በምርጫው የመጨረሻ ውጤት ላይ ዊሊያም ሩቶን የሚደግፉ ማጭበርበሮች ነበሩ በሚል ክስ ቢያቀርቡም በቂ ማስረጃ አልተገኘም በሚል አቤቱታቸው ውድቅ መሆኑ ይታወሳል።