ግዙፎቹ ፊኛዎች እና በራሪ አካላት አሜሪካ እና ቻይናን እያወዛገቡ ያሉት ለምንድን ነው?

የቻይና 'የስለላ ፊኛ' ስብርባሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና 'የስለላ ፊኛ' ስብርባሪ

ከቀናት በፊት ጥርት ባለው የሞንታና ሰማይ ግዛት ነዋሪዎች አንድ ቀልባቸውን የሳበ ነገርን አንጋጠው ሲመለከቱ ነበር፤ የክብ ቅርጽ ያለው ግዙፍ ነጭ ነገር።

ይህ ግዙፍ ክብ ነጭ ነገር የቻይና ሰላይ ፊኛ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

ይህ ፊኛ ከታየ ከጥቂት ቀናት በኋላ የአሜሪካ ጄቶች በሚሳኤል መትተው አጋዩት። በቀጣይ ቀናትም ሦስት ምንነታቸው ያልተገለጹ ፊኛዎች በሰሜን አሜሪካ ሰማይ ላይ ተመትተው ተጣሉ።

የቻይና ሰላይ ፊኛ ሳትሆን አትቀርም ተብላ ስለተጠረጠረችውም ሆነ ቀጥሎ ተመትተው ስለወደቁት በራሪ አካላት ምንነት ጥርት ያለ ተጨባጭ መረጃ አልተሰጠም።

ይህ ታዲያ ሁሉም የመሰለውን አስተያየት እንዲሰጥ ዕድል ከፍቷል። ለስለላ የተላኩ ናቸው ከሚለው አስተያየት እስከ በራሪ አካላቱ ከሌላ ዓለም የመጡ (ዩፎ) ናቸው የሚሉም አልጠፉም።

ዩናይትድ ስቴትስ የሰሜን አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ግሌን ቫንሄርክ የሰጡት አስተያየት ደግሞ በራሪ አካላቱ ከሌላ ዓለም የመጡ ናቸው ተብሎ የተሰጠውን መላ ምት ያጠናከረ መስሏል።

ጄኔራሉ በራሪ አካላቶቹ ‘ዩፉዎች’ ናቸው ወይ? ተብለው ሲጠየቁ፤ “አሁን ላይ ይሄ ነገር አይደለም ማለት አልችልም” ብለዋል።

አሜሪካ መትታ የጣለቻቸው ምንድናቸው?

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጎረቤት አገር ካናዳ አቅራቢያ ተመትተው የወደቁ በራሪ አካላት ስብርባሪዎችን ገና እያፈላለጉ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ስለበራሪ አካላቱ መነሻ እና ስለአገልግሎታቸው ምንነት ያሉት ነገር የለም።

የዋይት ሐውስ የደኅንነት ጉዳዮች ቃል አቀባይ ከጥቂት ቀናት በፊት የታዩት ሦስቱ በራሪ አካላት የቻይና የስለላ ፊኛ ሳትሆን አትቀርም ከተባለችው በራሪ አካል ጋር ሲነጻጸሩ በመጠን ያነሱ መሆናችውን ገልጸው ነበር።

አሜሪካ ከሁለት ሳምንት በፊት መትታ የጣለችው ግዙፍ ፊኛ መነሻው ቻይና መሆኑን እና በአሜሪካ ውስጥ ቁልፍ ቦታዎች ሲሰልል መቆየቱን ተናግረዋል።

ቻይና ፊኛው የራሷ መሆኑን ባትክድም ዓላማው ግን የአየር ንብረት ሁኔታን የሚከታተል መሆኑን እና በነፋስ ግፊት ወደ አሜሪካ የአየር ክልል መሄዱን ገልጻለች።

ሰላይ ነበረች ከተባለችው ፊኛ በኋላ ተመትተው የወደቁት ሦስት በራሪ አካላትም አነጋጋሪነታቸው እንደቀጠለ ነው።

በብራድፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ደኅንነት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ክስቶፍ ብሉዝ “አሜሪካውያኑ በበራሪ አካላቶቹ የተሰበሰበ መረጃ ካለ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቻይና 'የሰለላ ፊኛ' ተመትታ ስትወድቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና 'የሰለላ ፊኛ' ተመትታ ስትወድቅ

ፊኛዎች ለስለላ ጥቅም ላይ የሚሉት እንዴት ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ተመሳሳይ ነገሮች ከዚህ ቀደም አጋጥመው ነበር። በትራምፕ አስተዳደር ወቅት ሦስት ፊኛዎች በአሜሪካ ሰማይ ላይ ታይተው ነበር። ፊኛዎቹ የተለዩት ግን የአሜሪካን የአየር ክልልን ከለቀቁ በኋላ ነው” ያሉት ደግሞ በሪያል ዩናይትድ ሰርቪስ ተንታኝ የሆኑት ጁሊያና ሱስ ናቸው።

የቻይና የስለላ ፊኛ ነበረች ተብላ የተጠረጠረችው በራሪ አካል መጀመሪያ በአሜሪካ የአየር ክልል ላይ ከተንሳፈፈች በኋላ ወደ ካናዳ ተሻግራለች። ከዚያ መልሳ የአሜሪካ የኑክሌር መሳሪያ መገኛ በሆነችው ሞንታና ግዛት ላይ ታይታለች።

ፔንታገን ይህች የቻይና ፊኛ መጠን ከሦስት ትላልቅ አውቶብሶች ጋር እንደሚስተካከል እና ከ900 ኪሎ ግራም በላይ እንደምትመዝን የገለጸ ሲሆን፤ መረጃ ለመስብሰብ የሚያስችል የፀሐይ ብርሃንን ወደ ኃይል የሚቀየር መሳሪያ ተገጥሞላታል ብሏል።

ፕሮፌሰር ብሉዝ አሁን ላይ ፊኛዎች ለስለላ መጠቀም ብዙ የተለመደ አይደለም ይላሉ። ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት በዝግታ ስለሚንሳፈፉ ነው።

በ18ኛ ክፍለ ዘመን ግን ፊኛዎች ለስለላ በስፋት ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበረ ያስታውሳሉ። ዛሬ ላይ ግን የተለመደ የሚባለው የስለላ ፊኛ የራዳር እና የግንኙነት መስመሮችን የሚሰልል ሲሆን፣ በተገጠመላቸው ካሜራ ምስሎችን የሚወስዱም አሉ።

“አሁን ላይ ፊኛዎች በሳተላይ ቴክኖሎጂዎች ተተክተዋል” የሚሉት ፕሮፌሰር ብሉዝ፤ ሳተላይቶች ከረጅም ርቀት ላይ ሆነው ምድር ላይ ያለ በጣም አስተኛ አካልን በጥራት ማንሳት እንደሚችሉ በመግለጽ ከፊኛዎች ጋር ሲነጻጸሩ እጅግ የረቀቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ታዲያ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን በሰዎች ዓይን ሊታዩ የሚችሉ ፊኛዎች ለምን ጥቅም ላይ ይውላሉ? ለፕሮፌሰር ብሉዝ የቀረበ ጥያቄ ነው።

“ከላይ የሚነሳው ምስል በዝርዝር እና በተሻለ ጥራት የሚታየው ለምድር በቀረበ መጠን ነው። ሳተላይቶች ደግሞ እጅግ በጣም ከፍ ብለው ነው የሚገኙት። ምንም እንኳ የሳተላይት ቴክኖሎጂ የረቀቀ ቢሆንም ለምድር ዝቅ ባለ መጠን የተሻለ ነገር ማግኘት ይቻላል” ይላሉ።

የአሜሪካ ሳተላይት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለስለላ ምን አይነት ቁሶች ጥቅም ላይ ይውላሉ?

ከአሜሪካ የተገኘው አሃዝ እንደሚጠቁመው ከሆነ ቻይና በዋናነት ለስለላ ተግባር የሚውሉ እርስ በርሳቸው የተያያዙ ከ300 በላይ ሳተላይቶች አሏት።

ይህ ሁሉ ሳተላይት ላላት ቻይና ግን አንዳንዴ የስለላ ፊኛዎች የተሻለ ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ፣ የሚሉት ጁሊያና ሱስ ናቸው።

“ፊኛዎች ውጪያቸው አነስተኛ ነው፤ በፍጥነት ማስማራትም ይቻላል፤ ሳተላይቶች ቀድሞ በተቀመጠላቸው አቅጣጫ ብቻ ላይ እየተሸከረከሩ ነው መረጃ የሚሰበስቡት እንጂ እንደ ፊኛ ሰፊ ቦታ ላይ ለረዥም ጊዜ ቅኝት እያደረጉ ለውጦችን ማሳየት አይችሉም” ሲሉ ጁሊያና ሱስ ያስረዳሉ።

ብሉዝ ከፊኛዎች እና ከሳተላይቶች ውጪ የጦር አውሮፕላኖች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ለሰለላ ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ይጠቅሳሉ።

በተለይ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አሜሪካውያን የጦር አውሮፕላኖቻቸው በሶቪዬት ኅብረት እየተመቱ ከመውደቃቸው በፊት ለቅኝት ሥራዎች የጦር አውሮፕላኖችን አብዝተው ይጠቀሙ ነበር።

የቻይና እና የአሜሪካ ፍጥጫ

አራት በራሪ አካላት በሰሜን አሜሪካ ሰማይ ስር ተመትተው ከወደቁ በኋላ የአሜሪካ ጦር በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል።

የሰላላ ነች የተባለችው ፊኛ ተመትታ መውደቅ በሁለቱ ኃያላን አገራት መካከል ያለውን ውጥረት አባብሷል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ወደ ቻይና ሊያደርጉ የነበረውን ጉብኝት በፊኛዋ ምክንያት ሰርዘዋል።

ፊኛው የአየር ትንበያ መከታተያ መሳሪያ ነበረች ስትል የቆየችው ቻይና፤ አሜሪካም ባለፈው ዓመት ብቻ 10 ጊዜ የአየር ክልሌን ጥሰው የገቡ ፊኛዎችን አሰማርታ ነበር ብላለች።

ሦስቱ ምንነታቸው ያልተገለጹት በራሪ አካላት መነሻ እና አላማ ሲረጋገጥ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ውጥረት ሊያካርር ወይም ሊያረግብ ይችላል።

ብሉዝ እንደሚሉት ግን እነዚህ ምንነታቸው እስካሁን ያልታወቁት ዓላማቸው የሰላላ ስለመሆኑ እስካሁን ማረጋገጫ አለመገኘቱን እንዲሁም ይንሳፈፉበት የነበረው ከፍታ ተግባራቸው ሰላላ ላይሆን እንደሚችል የሚጠቁም ነው።

“በሂደት አሜሪካ እና ቻይና በመካከላቸው ያለውን ውጥረት ማብረዳቸው አይቀርም። የትኛው አይነት በራሪ አካል እንደሚፈቀድ፣ እንዲሁም ቀድሞ ማሳወቅ ላይ ከስምምነት ይደርሳሉ” ሲሉ ብሉዝ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ለተንታኟ ጁሊያና ሱስ ግን ብዙ አሜሪካውያን በቻይናው ፊኛ መበሳጨታቸው ውሃ የሚቋጥር ጉዳይ አይደለም። ጁሊያና ሰዎች በፊኛዋ የተበሳጩት ምናልባት ስለተመለከቷት ነው ይላሉ።

“ሰዎች በየዕለቱ ለደኅንነት ተግባር የሚውሉ ፎቶግራፎች የሚያነሱ በርካታ ሳተላይቶች እንዳሉ ይዘነጋሉ” ይላሉ።