ቻይና የአሜሪካ በራሪ ፊኛዎች በተደጋጋሚ የአየር ክልሌን ጥሰዋል ብላ ከሰሰች

አሜሪካ ለስለላ የተሰማራች ናት በማለት መጀመሪያ መትታ የጣለቻት የቻይና ፊኛ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ለስለላ የተሰማራች ናት በማለት መጀመሪያ መትታ የጣለቻት የቻይና ፊኛ

በአሜሪካ የአየር ክልል ሲንሳፈፉ ተገኙ በተባሉት ግዙፍ ፊኛዎች ምክንያት ውዝግብ ውስጥ የገቡት ቻይና እና አሜሪካ ሉዓላዊነትን በመጣስ እየተካሰሱ ነው።

ባለፉት ቀናት በአየር ክልሏ ውስጥ ያገኘቻቸውን የቻይና ፊኛዎች በተዋጊ አውሮፕላኖች መትታ መጣሏን ያሳወቀችው አሜሪካ፣ ወደ ቻይና ተመሳሳይ ፊኛዎችን አሰማርታ እንደነበር ቻይና ገለጸች።

ውዝግቡ እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት አሜሪካ ወደ ቻይና የአየር ክልል ከ10 ጊዜ በላይ ፊኛዎችን መላኳን ገልጿል።

ቻይና ለአየር ሁኔታ ጥናት ያሰማራሁት ፊኛ ነው ያለችው እና አሜሪካ ግን ለስለላ የተላከ ነው ብላ የጠረጠረችውን ፊኛ ከሳምንት በፊት መትታ መጣሏ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ተበላሽቶ የቆየ ሲሆን፣ ባለፉት ቀናትም ምንነታቸው ያልተለዩ ተጨማሪ በራሪ አካላትን አሜሪካ መትታ እንደጣላች አስታውቃለች።

ዛሬ ሰኞ በጉዳዩ ዙሪያ ቻይና ለቀረበላት ጥያቄ በሰጠችው ምላሽ፣ አሜሪካ በተመሳሳይ የአየር ክልሏን የሚጥስ ድርጊት በተደጋጋሚ መፈጸሟን ገልጿለች።

“በአሜሪካ ጭምር የሚፈጸሙ በሕገ ወጥ ሁኔታ የሌሎች አገራትን የአየር ክልል የመጣስ ድርጊቶች ብዙም ያልተለመዱ አይደሉም” ሲሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“ባለፈው ዓመት ብቻ፣ የአሜሪካ ፊኛዎች ከቻይና ባለሥልጣናት ምንም አይነት ፈቃድ ሳያገኙ ከአስር ጊዜ በላይ በሕገ ወጥ መንገድ በቻይና የአየር ክልል ላይ ተንሳፈዋል።”

ጨምረውም “አሜሪካ ቻይናን በመክሰስ ስም ከማጥፋቷ በፊት ወደ ውስጧ በመመልከት፣ ከድርጊቱ እራሷን ማንጻት መጀመር አለባት” ሲሉ መክረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ የአሜሪካ የአየር ክልል ጥሰት ባጋጠመበት ጊዜ ቻይና ምላሽ የሰጠችው “ኃላፊነት በተሞላበት እና ሙያዊ በሆነ መንገድ ነው” ብለዋል - ቃል አቀባዩ።

“አሜሪካ ወደ ቻይና ግዛት በሕገ ወጥ ሁኔታ ስላስገባቻቸው በከፍተኛ ርቀት ላይ ስሚጓዙ ፊኛዎች የበለጠ ለማወቅ ከፈለጋችሁ፣ የአሜሪካንን መንግሥት እንድትጠይቁ ነው የምመክራችሁ” ብለዋል።

ይህንን የቻይና ክስን በተመለከተ አሜሪካ አስካሁን ያለችው ነገር የለም።

በአሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻይና ፊኛ ሲንሳፈፍ በመገኘቱ ምክንያት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንክን ወደ ቻይና ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝት ተሰርዟል።

ክስተቱንም ብሊንከን “ተቀባይነት የሌለው እና ኃላፊነት የጎደለው” ብለውታል።

ትናንት እሁድ አሜሪካ ከካናዳ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ ሰው አልባ በራሪ አካል መትታ መጣሏን ያሳወቀች ሲሆን፣ ይህም በስምንት ቀናት ውስጥ አራተኛው ነው።

በተጨማሪም ከሦስት ቀናት በፊት በአላስካ ግዛት እና በሰሜን ካናዳ ውስጥ የጦር አውሮፕላኖች ምንነታቸው ያልተለዩ በራሪ አካላትን መትተው መጣላቸው ተዘግቧል።

ነገር ግን የቻይና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ የሆኑት ዋንግ ስለተባሉት በራሪ አካልት “የሚያውቁት ነገር እንደሌለ” ገልጸዋል።

“ነገር ግን ለሁሉም ማሳወቅ የምንፈልገው ነገር ቢኖር፣ አሜሪካ ምንነታቸው ያልታወቁ ነገሮችን ለመምታት የምትተኩሳቸው ዘመናዊ ሚሳኤሎች ከሚያስፈልገው በላይ ኃይል እየተጠቀመች መሆኑን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት አዛዥ የሆኑት ግሌን ቫንሄርክ እንዳሉት፣ እነዚህ በራሪ አካላት ጉዳትን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሚያመለክት ነገር የለም።

ጄኔራሉ ጨምረውም እነዚህ በራሪ አካላት “በጋዝ የሚንቀሳቀሱ አይነት ፊኛዎች” ወይም “አንዳች አይነት በሞተር የሚታገዙ በራሪ አካላት” ሊሆኑ ይችላሉ በማለት፣ ነገር ግን ከሌላ ዓለም የሚመጡ በራሪ አካላት ሊሆኑም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።