በባሕር ሲጓዙ የነበሩ ከ380 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከመስመጥ አደጋ መታደግ ተቻለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የጂቡቲ ባለሥልጣናት በሕገወጥ መንገድ በባሕር ላይ ለመሻገር ሲሞክሩ የመስመጥ አደጋ ተጋርጦባቸው የነበሩ 383 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከአደጋ መታደጋቸው ተገለጸ።
ባለሥልጣናቱ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያኑን የታደጉት የኤደን ባሕረ ሰላጤ ተብሎ በሚጠራው የባሕር ክፍል ላይ መሆኑን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታውቋል።
ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በጅቡቲ፣ በየመን እና ሶማሊያ በሚዋሰነው የውሃ አካል ላይ ከመስመጥ የዳኑት ባለፈው ሳምንት ውስጥ መሆኑም ተነግሯል።
በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአገሪቱ የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ኃይል ዜጎቹን ለመታደግ ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና አቅቦ፣ 383 ስደተኞቹን ሲያጓጉዙ የነበሩ አዘዋዋሪዎች ሕግ ፊት ቀርበዋል ብሏል።
አይኦኤም የስደተኞች ፍልሰት የዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመቀስቀሱ በፊት ወደነበረበት ተመልሷል ያለ ሲሆን፤ ለስደተኞች ፍልሰት ዋነኛ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ድህነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭት ናቸው ብሏል።
ይህ የተባበሩት መንግሥታት ተቋም ባለፈው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ብቻ ከ150ሺህ በላይ ስደተኞች ‘በምሥራቁ መተላለፊያ መንገድ’ በኩል በየመን አድርገው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት ተሻግረዋል ብሏል።
ይሁን እንጂ በዚህ የስደት ጉዞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰነድ አልባ ስደተኞች ሕይወታቸውን ያጣሉ አልያም በጦርነት እየታመሰች ወዳለችው የመን ከገቡ በኋላ መውጫ ያጣሉ።
“ትክክለኛውን የሟቾችን ቁጥር ልንገልጽ አልችልም፣ ምክንያቱም እኛ ሳንመዘግብ የምንቀረው እና በዚህ በዓለም ላይ አደገኛ በሆነው የጉዞ መስመር የሚጠፋው ሕይወት በርካታ ነው” ሲሉ የአይኦኤም ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዳይሬተሩ እንደሚሉት በርካታ ስደተኞች አደገኛውን መንገድ የሚጀምሩት የተደላደለ ሕይወት እንደሚጠብቃቸው በሐሰት ከተደለሉ በኋላ ነው ይላሉ።
“ብዙዎቹ በየመን ጦርነት እንኳ እንዳለ አያውቁም” ይላሉ ቪቶሪኖ።
ዳይሬክተሩ ሰዎች ስነድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ስደት ጀምረው ስቃይ እና ሞት የሚደርስባቸውን ሰዎች ለመቀነስ ‘ሕጋዊ እና ዘላቂ’ የሆነ አሰራር አማራጭ ነው ይላሉ።
የአይኦኤም ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ እንደ ምሳሌ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ ወደ ሌላ አገር መሸጋገር የሚፈልጉ ስደተኞች በመንግሥታቱ ድርጅት ተመዝግበው እና ሰነድ ይዘው እንደ ጤና ያሉ መሠረታዊ አገልግሎት እያገኙ ከቆዩ በኋላ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ወደ ሦስተኛ አገር እንደሚሸጋገሩ ያወሳሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ይህን መሰል አማራጭ ቢቀርብ እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለስደት የሚወጡ ሰዎች ቁጥርን ይቀንሳል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የሰብዓዊ መብቶች በመጣስ ሰዎችን በሚያዘዋውሩ ቡድኖች ላይ ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል።
“የስደተኞችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን በመጣስ ሰዎችን በሚያዘዋውሩ የተሳሰሩ የወንጀለኛ ቡድን አባላትን በመለየት እና ከሕግ ፊት ለማቅረብ ውጤታማ ተግባራት መከናወን አለባቸው” ብለዋል።












