በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ችግር ለመፍታት የተላለፉ ውሳኔዎች ምንድን ናቸው?

የሃይማኖት አባቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር

የፎቶው ባለመብት, EBC

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ቀኖና እና ሥርዓት በጣሰ መልኩ የጵጵስና ሹመት ተጥሷል በማለት ካወገዘቻቸው አባቶች ጋር በተያያዘ ተከስቶ የነበረው ችግር ረቡዕ የካቲት 8/2015 ዓ.ም. እልባት አግኝቷል።

ቤተ ክርስቲያኗ ችግሩን በሃይማኖታዊ ቀኖና እና ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ እንደተፈታም አስታውቃ ነበር።

በዚህም የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት እና ሕግ ጥሰዋል ተብለው በቅዱስ ሲኖዶሱ ሥልጣናቸው እንዲሻር እና እንዲወገዙ ውሳኔ የተላለፈባቸው ሊቃነ ጳጳሳትእ ና ተሿሚዎች ወደቀደመ ማዕረጋቸው እንዲመለሱ ተወስኗል።

ከሳምንታት በፊት በቤተ ክርስቲያኗ አካታችነት እና የቋንቋ አጠቃቀም ላይ ለተነሱ ጥያቄያዎች ምላሽ አልተገኘም በማለት 26 ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾም እንዲሁ የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች የተባለ ሲኖዶስ በሚልም ተቋቁሞ ነበር።

ለሳምንታት የቤተክርስቲያኗን ምዕመናንን ያወዛገበው፣ ለሰዎች ሕይወት መቀጠፍ፣ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎችን ለእስር የዳረገው እና ለአገሪቷም አደጋ ጋርጦ የነበረው ችግር መቋጫም አግኝቷል።

ቤተ ክርስቲያኗ አቀራራቢ ባለቻቸው አቡነ ናትናኤል፣ አቡነ ኤርምያስ፣ አቡነ ሩፋኤልና እና የአገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት ውይይት ተደርጎ እልባት እንደተበጀለት ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ችግር በመነጋገር ለመፍታት ከሁለቱም ወገን ያሉ አባቶች ተገናኝተው እና ተወያይተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በውይይታቸውም ላይ በሁለቱም ወገን ያሉ አባቶች የቤተ ክርስቲያን እና የአገር አንድነት የሚያጸና፣ መለያየትን የሚያጠፋ፣ አገልግሎትን የሚያሰፋ መንገድ መከተል እንደሚገባም አጽንኦት መስጠታቸውን የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች ከቋንቋ እና ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር የተነሳው ጥያቄ በቤተ ክርስቲያኗ እንዲመለስ እና የተጀመረውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

በአባቶቹ መካከል የተደረሰው ስምምነት አስር ነጥቦች

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠት የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች የካቲት 8/2015 ዓ.ም. ያደረጉት ውይይት አስር ነጥቦችን በማሳለፍ ተጠናቋል። በዚህም

  • ቤተ ክርስቲያኗ ሥልጣናቸውን ሽራ ያወገዘቻቸው ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ቀደመ አገረ ስብከታቸው እና ማዕረጋቸው እንዲመለሱ፤ እንዲሁም ተሿሚዎቹ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመታቸው ተሽሮ ወደነበሩበት የክህነት ማዕረግ እንዲመለሱ ተወስኗል። ከተሾሙት መካከል በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት መመዘኛውን የሚያሟሉት በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲሾሙ ይደረጋል ተብሏል።
  • በኦሮሚያ ክልል በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት፣ ቅዳሴ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲሰጡ የተጀመረው ሥራ የሕዝቡን ጥያቄ ባማከለ መልኩ እንዲጠናከር
  • በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች የተዳከሙ አብያተ ክርስቲያናትን ቋንቋውን በሚያውቁ አገልጋዮች እና በአገልግሎት ማጠናከር
  • በእነዚህ አካባቢዎች ቋንቋውን እንዲያውቁ የሚያሰለጥኑ ተጨማሪ ኮሌጆች እና ማሠልጠኛዎች እንዲከፈቱ
  • ለኦሮሚያ አህጉረ ስብከት ቋንቋውን የሚያውቁ እና የሚያገለግሉ ኤጲስ ቆጶሳት በቀጣይ የግንቦት የካህናት ጉባኤ ላይ ተወስኖ እንዲሾሙ
  • በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በፋይናንስ፣ በምደባ፣ በቅጥር የሚታዩ ክፍተቶችን በጥናት ማሻሻል እና ማጠናከር
  • የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከር እና ለትውልድ አርዓያ የሚሆን ቤተ ክህነት እንዲኖር ለማድረግ አሰራሯን በጥናት አሻሽሎ ቤተ ክርስቲያኗን ለትውልድ ማሻገር
  • ጥላቻን የሚያባብሱ ነገሮችን ከማድረግ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ መምህራን እና አባቶች እንዲቆጠቡ እንዲሁም ይሄንን ተግባር ሆን ብለው የሚያደርጉም ተወግዘዋል
  • ቤተ ክርስቲያኗ የገጠማትን ፈተና ውስጧን ለመፈተሽ፣ አንድነቷን ለማጠናከር እና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ለማስፋፋፋት ለበጎ መጠቀም የሚሉት ተጠቅሰዋል።

ችግሩ መፍትሔ ማግኘቱን በተመለከተ መግለጫ በተሰጠበት ጊዜ የቤተክርስቲያኗ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ አቡነ አብረሃም “ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሦስቱ አባቶች መመለስ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች” ብለዋል።

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ ከመፍታት ባሻገር በቤተ ክርስቲያኗ ቀኖና እና ሥርዓት መሠረት እንዲፈታ ታላቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ተገልጿል።

ከሰሞኑ ከቤተክርስቲያኗ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ አበይት ጉዳዮች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቤተ ክርስቲያኗ የተወገዙት አባቶች ሕጋዊ በምትላቸው ይዞታዎቿ እንዳይገኙም ለማድረግ የእግድ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ማቅረቧ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ቤተ ክርስቲያኗ የእግድ አቤቱታ ያቀረበችባቸው ሦስት ጳጳሳት እና ተሿሚዎች ወደ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይገቡ የተላለፈው ጊዜያዊ እግድ እስከ ቀጣይ ቀጠሮ ድረስ እንዲቆይ ብያኔ መተላለፉን የቤተ ክርስቲያኗ ጠበቃ አቶ አያሌው ቢታኔ ገልጸዋል።

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ግድያዎች፣ እስሮች፣ መዋከቦች እና እንግልቶች መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል።

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመናል ያሉ ጳጳሳት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን መያዛቸውን የተቃወሙ ምዕመናን ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና ተባባሪዎቻቸው ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል መጠቀማቸው ተገልጿል።

በዚህም በጥይት እና በድብደባ ስምንት ሰዎች ሻሸመኔ ውስጥ መገደላቸውን ኢሰመኮ ገልጾ ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ያለ ነው ብላለች።

በተለያዩ ቦታዎችም አዲሱን ሲኖዶስ አቋቁመናል ያሉትን ጳጳሳት በተቃወሙ ምዕመናን እና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጪ እስራት ተፈጽሟል ብሏል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ሃይማኖታዊ ቀኖና እና ሥርዓት ጉዳዩን እልባት እንዲያገኝ መንግሥት ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም ጠይቃ ይህ ካልሆነ አገራዊ ሰላማዊ ሰልፍ ለየካቲት 05/2015 ዓ.ም. መጥራቷ ይታወሳል።

ከዚያም ቀደም ብሎም ለሦስት ቀናት በነበረው ነነዌ ጾም ምዕመናኑ በሱባዔ፣ በጾም እና በጸሎት እንዲሁም ጥቁር ልብስ እንዲለብሱ በተጠየቀው መሠረት በአገሪቱ አብያተ ክርስቲያናት በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ተሰባሰበው ታይተዋል።

የሲኖዶሱን ትዕዛዝ ተከትለው ጥቁር የለበሱ ሰዎች እስር፣ ወከባ፣ ከሥራ ቦታ እና አገልግሎት መነፈጋቸውን ቢቢሲ የዘገበ ሲሆን፣ ኢሰመኮም በመግለጫው ይህንኑ ጉዳይ አንስቷል።

ሆኖም ሰላማዊ ሰልፍ ከመካሄዱ በፊት በነበሩ ቀናት የሃይማኖቱ አባቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በተደረገ ውይይት ጥያቄዎቹ ሙሉ በሙሉ ምላሽ እንደሚያገኝ እና ሰልፉም መራዘሙንም ገልጻ ነበር።

ሆኖም ከዚያ በኋላ በነበሩ ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን መታሰራቸውን እና አብዛኛዎቹም ወደ አዋሽ ሰባት የጦር ካምፕ መወሰዳቸውን የቤተ ክርስቲያኗ የሕግ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የተወሰኑት ደግሞ በአዲስ አበባ በሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ አሲረዋል በሚል በሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የተከሰተው ችግር አሁን እልባት ማግኘቱንም ተከትሎ በእስር ላይ የሚገኙ ምዕመናን በጥቂት ቀናት ጉዳያቸው ታይቶ እንደሚፈቱ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አቡነ አብረሃም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ እስሮችን በተመለከተ የተወሰኑ ግለሰቦች በፍርድ ቤት ወይም በፖሊስ ጣቢያ ዋስትና መለቀቃቸውን ኢሰመኮ የካቲት 8/2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሆኖም ከቤተ ክርስቲያኗ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በተለያየ ዓይነት ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል የተወሰኑ ሰዎች ዋስትና ተከልክለው በእስር ላይ እንደሚገኙም አስታውሷል።

“ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ተያይዞ የዚህ ዓይነቱ እስር የዘፈቀደ እስር ሊሆን ስለሚችል የመንግሥት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት በሙሉ በበቂ ምክንያት በወንጀል የተጠረጠረን ሰው በሕጉ መሠረት ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ እንዲያስተናግዱ” የኢሰመኮ መግለጫ አሳስቧል።