በትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት የሚመሠረትበት ሰነድ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ተገለጸ

ምሥረታውን ለማካሄድ የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Tigray Television/ Facebook

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት የሚመሰረትበት ሰነድ በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚሆን ተገለጸ።

ምሥረታውን ለማካሄድ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ የካቲት 8/2015 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጊዜያዊ መንግሥቱ የሚተዳደርበትን ሰነድ የማዘጋጀቱ ሥራ እየተገባደደ መሆኑን አስታውቀዋል።

እስከዚህ ሳምንት መጨረሻም ሕዝብን እና ተቃዋሚ ፓርቲን ያሳተፉ ውይይቶች በክልሉ ውስጥ በስፋት እንደሚካሄዱም ተገልጿል።

ኮሚቴው የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ታደረሰ ወረደ እና አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያምን ጨምሮ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሦስት ከትግራይ ኃይሎች፣ ሦስት ከህወሓት እና ሦስት ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ ናቸው።

የኮሚቴው አባላት ጊዜያዊ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ጥቅም በማስጠበቅ መሥራት እንዳለበት ተስማምተዋል ብለዋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች እንደነበሩት ያወሱት ጄኔራሉ አንደኛው የፀጥታ እና ሰብአዊ እርዳታን የሚመለከት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በፖለቲካ ጉዳይ ላይ በሁለቱ ተፈራራሚ ፓርቲዎች የሚቋቋም ጊዜያዊ መንግሥት ጉዳይን የሚመለከት እንደነበረ አስታውሰዋል።

“ጊዜያዊ መንግሥት መመሥረቱ የፕሪቶሪያ ስምምነት ግድ ስለሚያደርገው ብቻ ሳይሆን ውስጣችንም ያን እንድናደርግ ስለሚያስገድደን፣ አስፈላጊነቱን ስላመንበት እንዲሁም የፖለቲካ ባህላችን ላይ ጭምር ለውጥ ለማምጣት ሲሆን፣ ይህም ለትግራይ ሕዝብ ወርቃማ እድል ነው” ብለዋል ጄኔራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ቀጣይ ለሚከናወኑ ሥራዎች እንዲሁም አስተማማኝ ሰላም በትግራይ ለማስፈን ወሳኝ እንደሆነም ጄኔራሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥትን ለመመሥረት በትግራይ በኩል አስተባባሪዎች ሆነው ከተሰየሙ በኋላ እየተሠሩ ያሉ ቁልፍ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

ጊዜያዊ መንግሥቱን ለመመሥረት የሚያስችለውን የሥራ ሂደት ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በሆነ ሁኔታ ለማካሄድ እንደተሞከረም ጄኔራሉ አውስተዋል።

ጄኔራል ታደሰ ይህ ሂደት ለትግራይ ሕዝብ ወሳኝ የታሪክ ሂደት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

ኮሚቴው እንደገለጸው በትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ላይ ከፌደራል መንግሥት ጋር ጥሩ መግባባት ላይ መድረሱን አስታውቋል።

ሰነዱ ከጸደቀ በኋላ ሰነዱ ከፌዴራል መንግሥት ጋር መደራደሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል ጄኔራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ውይይት ላይ የበጀት ጉዳይ በተነሳበት ወቅት በቀዳሚነት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ እንደሚለቀቅ ተገልጾ ነበር።

ከበጀትም ጋር በተያያዘ የጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡንም የትግራይ ተደራዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ አስታውቀው ነበር።

ጄኔራሉ የትግራይ ሉአላዊ ግዛቶችን በተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ሂደት መጀመር ባለበት ደረጃ እንዳልተጀመረ ጠቅሰዋል በመግለጫቸው።

የኤርትራ ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች በትግራይ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ሁለቱም ኃይሎች ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ ሁኔታዎች እያተመቻቹ ነው ብለዋል።

“መላው ትግራይ ገና ነፃ አልወጣም” ያሉት ጄኔራሉ ነገር ግን የሰላም ስምምነቱ የሚደናቀፍበት መንገድ እንደሌለና “ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ መመለስ የለም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እና የመተግበሪያ ሰነድ፣ የትግራይ ኃይሎች ከባድ መሳሪያ የሚፈቱት የውጭ ኃይል እና ከመከላከያ ውጭ ያሉ ኃይሎች ሲወጡ በተመሳሳይ ወቅት መሆኑን ማስቀመጡ ይወሳል።

ሆኖም ስምምነቱ ከተፈረመ ከወራት በኋላ በትግራይ ያሉ ቦታዎች በኤርትራ እና በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መሆኑን ከትግራይ በኩል እየተሰማ ነው።

በቅርቡም አቶ ጌታቸው ኤርትራ “እንደ ጦር ከአብዛኞቹን የትግራይ አካባቢዎች ለቀው ወጥተዋል። ነገር ግን አሁንም ያልወጡባቸው ቦታዎች አሉ” ሲሉም ተናግረዋል።

አክለውም “በተመሳሳይ የአማራ ኃይሎች ከብዙ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በፀለምት፣ በምዕራብ ትግራይ እንዲሁም በደቡብ ትግራይ የተወሰኑ አካባቢዎች ያልተሰራ ሥራ እንዳለ እንረዳለን” ብለዋል።

በትግራይ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በጦርነቱ የተሳተፈው የኤርትራ ጦር መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈጽሟል በሚል የሚወነጀል ሲሆን፣ ከሰላም ስምምነቱ መፈረምም በኋላ ጥቃቶች መቀጠላቸውን የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኤርትራ ጦር ሠራዊት አባላት በአሁኑም ወቅት በመድፈር ወንጀል እና ጥቃቶች ክስ እየቀረበባቸው ይገኛሉ።

በቅርቡ በኬንያ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የጦር ሠራዊታቸው በትግራይ ስለፈጸመው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በማጣጣል ምላሽ ሰጥተዋል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የኤርትራ ጦር በትግራይ የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች መፈጸሙን ባወጧቸው ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ቢገልጹም ፕሬዚዳንቱ “ፈጠራ ነው” ብለውታል።