ከትግራይ መውጣት አለመውጣቱ እያነጋገረ ያለው የኤርትራ ሠራዊት

የፎቶው ባለመብት, sm
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መውጣትን በተመለከተ አስካሁን እርስ በእርሱ የሚቃረን መረጃ እየወጣ ነው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን ባለፈው አርብ ጥር 19/2015 ዓ.ም. በትግራይ ውስጥ ከፌደራሉ ጦር ውጪ ሌላ ኃይል የለም ያሉ ሲሆን፣ አንዲት የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ግን የኤርትራ ሠራዊት አሁንም ትግራይ ውስጥ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ፌደራል መከላከያ ሠራዊት የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ለተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በትግራይ ውስጥ የሚንቀሰቀሳው የአገሪቱ ሠራዊት ነው ብለዋል።
“በትግራይ ክልል ከኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት ውጪ በግዳጅ ላይ ያለ ሌላ የፀጥታ ኃይል የለም” በማለት ከፍተኛ መኮንኑ መግለጻቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።
ነገር ግን በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የኤርትራ ወታደሮች ምንም እንኳን ወደ ድንበር አካባቢ ቢንሳቀሱም፣ አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ መናገራቸውን ሮይትርስ የዜና ወኪል እሁድ ጥር 21/2015 ዓ.ም. ዘግቧል።
አምባሳደሯ በጎረቤት ኬንያ እያደረጉት ባለው ጉብኝት ወቅት ናይሮቢ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ኤርትራውያንን በተመለከተ ወደ ድንበር አካባቢ እንደተንቀሳቀሱ ተረድተናል፣ ለቀው እንዲወጡ ተጠይቀዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የኤርትራ ወታደሮችን በተመለከተ ምንም አይነት ማስረጃም ሆነ ምንጭ አልጠቀሱም። የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀልም ከሮይትርስ ስለጉዳዩ ተጠይቀው መልስ አልሰጡም።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ የተናገሩትን በመተመለከተም የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ላይ የሚቃረን ምላሽ አስፍረዋል።
አቶ ጌታቸው ከፌደራሉ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች መውጣትን በተመለከተ ምልክቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ነገር ግን “በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች ትግራይ ውስጥ ይገኛሉ” ብለዋል።
ጨምረውም ከኃይሎቹ መውጣት ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በስምምነቱ መሠረትም የአፍሪካ ኅብረት የትግበራ ተቆጣጣሪ ቡድን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ብለዋል።
ቅዳሜ ጥር 13/2015 ዓ.ም. የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አሕመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት ባስቆመው ስምምነት ትግበራ ዙሪያ የስልክ ውይይት አድርገው ነበር።
በተደረሰው ግጭትን የማቆም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ወታደሮች መውጣት መጀመራቸውን ጨምሮ እየታዩ ያሉት እርምጃቻዎችን በበጎ እንደሚቀበሏቸው ብሊንከን መጥቀሳቸው ተዘግቧል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አጠቃላይ ስምምነት በመድረሳቸው ጦርነት ቆሞ ስምምነቱ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
በስምምነቱም በዘላቂነት ጦርነቱ እንዲቆም፣ እርዳታ ያለቀገድብ እንዲቀርብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ደግሞ ትጥቅ እንዲፈቱ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፎ በትግራይ የተለያዩ አከባቢዎች ተሰማርቶ የቆየው የኤርትራ ሠራዊት መውጣት የሚጠበቅ የስምምነቱ አንድ እርምጃ ነው።
ባለፉት ሳምንታትም ሽረ፣ አክሱም፣ አድዋን እና ሌሎች አካባቢዎችን ጨምሮ የኤርትራ ሠራዊት አባላት እየለቁ ሲወጡ መመልከታቸውን የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል ነበር። ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች የኤርትራ ጦር መኖሩ ተዘግቧል።
በተለይ ከአንድ ሳምንት በፊት የኤርትራ ሠራዊት በከፍተኛ ቁጥር ከአክሱም እና አድዋ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና በአውቶቡሶች ተጭኖ ሲወጣ መመልከታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ይህም የኤርትራ ጦር እንቅስቃሴ ከዚህ በፊት ከታየው ከፍተኛ እንደሆነ እና ከባድ መሳሪዎችም ተጭነው መውጣታቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
ይህንን የኤርትራ ሠራዊት መውጣት በተመለከተ ግን ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ መንግሥታት እንዲሁም ከህወሓት መሪዎች በኩል በይፋ የተባለ ምንም ነገር የለም።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት አማፂያን መካከል ሲካሄድ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነትን ተከትሎ ኤርትራ ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ሠራዊቷን አሰልፋ ቆይታለች።
የተባበሩት መንግሥታትም እና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች የኤርትራ ወታደሮችን ጨምሮ ሁሉም በጦርነቱ የተሳተፉ ወገኖች ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈፀማቸውን ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል።












