ከሰላም ስምምነቱ በኋላም የኤርትራ ወታደሮች በመድፈር ወንጀል ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
- ፀሐፊ, ካትሪን ባይሩሃንጋ
- የሥራ ድርሻ, የቢቢሲ ኒውስ፣ የአፍሪካ ዘጋቢ
የሰሜን ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት በዘላቂነት ለማስቆም የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ከስምምነት ከደረሱ ከወራት በኋላም የኤርትራ ሠራዊት አባላት በመድፈር ወንጀል ክስ እየቀረበባቸው ነው።
የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች የኤርትራ ጦር አባላት በጾታዊ ትንኮሳ ተግባራቸው ቀጥለዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት ተወካዮች በፈገግታ ተሞልተው የሰላም ስምምነቱን በተፈራረሙበት ዕለት ምሽት፤ ለታይ በተሸሸገችበት ድልድይ ላይ ለሊቱን በሙሉ የከባድ ጦር መሳሪያ ፍንዳታ ሲደርስ ነበር።
ለታይ በኤርትራ ወታደር ተደፍራለች። “ካጋጠመኝ በኋላ (አስገድዶ መደፈሩ) ለረዥም ሰዓታት እራሴን አላውቅም ነበር፤ እራሴን ካወቅኩ በኋላ ወታደሮቹ እስኪሄዱ ድረስ መደበቅ ነበረብኝ” ትላለች።
የለታይን ጨምሮ በዚህ ዘገባ ውስጥ ታሪካቸውን ያጋሩን ሴቶች ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ስማቸውን ቀይረናል።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው አስከፊ ጦርነት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች ሆነ ተብሎ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በተባበሩት መንግሥታት፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና በጋዜጠኞች ተሰንደዋል።
የትግራይ ኃይሎችም ቢሆኑ በመልሶ ማጥቃት ወደ አዲስ አበባ አቅጣጫ በገሰገሱ ወቅት በጾታዊ ጥቃቶች ተጠያቂ ተደርገዋል።
በሁለቱም ወገን ያሉት አካላት ትግራይን ለመያዝ ለሁለት ዓመታት ያደረጉት ደም አፋሳሽ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወታቸውን አሳጥቷል።
ሁለቱ አካላት ግን ከጥቂት ወራት በፊት ግጭቱን በዘለቂነት ለማቆም ሲስማሙ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ያቆማል የሚል ተስፋን ፈንጥቆ ነበር።
ይሁን እንጂ ሴቶች፣ የጤና ባለሙያዎች እና የእርዳታ ድርጅቶች አሁንም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አለመቆሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጋዜጠኞች ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ የፌደራል መንግሥቱ ባለመፍቀዱ ለታይን በስልክ ማነጋገሩ ብቸኛው አማራጭ ሆኗል።
“ሁለት ግዜ ነው ያጋጠመው (መደፈሩ)። ምን አጥፍቼ ነው? ተመኝቼው ያገኘሁት ነው የሚመስለው።” ትላለች ለታይ።
ለታይ ጥር 2013 ዓ.ም ላይ በሁለት የኤርትራ ወታደሮች በቡድን ተደፍራለች። ከደፋሪዎቹ ጋር አብሮ የነበረው ሦስተኛው ወታደር ግን ፍቃደኛ ሳይሆን ቀረ ትላለች።
“ሁለቱ የሚፈልጉን ካደረጉ በኋላ ሦስተኛው ወታደር ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ ጠየቁት። እርሱ ግን እምቢ አለ። ‘ምን አድርግ ነው የምትሉኝ? ሬሳ እኮ ነው ተንጋሎ ያለው’" በማለት ለወታደሮቹ መመለሱን ለታይ ታስታውሳለች።
ለታይ ጾታዊ ጥቃት ከደረሰባት በኋላ የአካል እና የአእምሮ ጤና እርዳታ ፍለጋ የጾታዊ ጥቃት ሰላባ ተጎጂዎች ድጋፍ የሚያደርግ ቡድንን ተቀላቅላለች።
የሰላም ስምምነቱ በተፈረመበት ዕለት ለታይ ተመሳሳይ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባትን ታዳጊ ሴት ለመርዳት ትወጣለች።
በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ምን ያክል ሴቶች ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው በትክክል ማወቅ አይቻልም። ይሁን እንጂ ከትግራይ ጤና ቢሮ የተገኘው አሃዝ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በነበሩት ሁለት ወራት 852 የመደፈር ክሶች ድጋፍ ለማድረግ በተቋቋሙ ማዕከላት ደርሰዋል።
በትግራይ የሚሰሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የእርዳታ ድርጅቶች በትግራይ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን መመዝገባቸውን ቀጥለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ድንበር ከተማ የሆነችው የዛላምበሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ኢያማ ደግሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት በኤርትራ ወታደር ጾታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባት ትናገራለች።
“አራት ነበሩ አስገድዶ የደፈረኝ ግን አንደኛው ነው። እኔን የመግደል ዕቅድ ሁሉ ነበራቸው፤ ግን ከደፈረኝ በኋላ ጥለውኝ ሄዱ” ትላለች።
ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ መቀለ ከተማ በሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችን ስትደግፍ የቆየችው ሲስተር ሙሉ መስፍን በሆስፒታሉ ኮሪደሮች እየተንቀሳቀሰች የድምጽ መልዕክት ለቢቢሲ ልካ ነበር።
“በምሰራባቸው ማዕከላት በርካታ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች አሉ። ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ነው የሚመጡት። አብዛኛዎቹ ባለፈው አንድ ወይም ሁለት ወራት መደፈር የደረሰባቸው ናቸው” ብላለች።
እንደ ሲስተር ሙሉ ከሆነ በትግራይ ሴቶች ላይ አብዛኛውን የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን እየፈጸሙ ያሉት የኤርትራ ወታደሮች ሲሆኑ የኢትዮጵያ እና የአማራ ሚሊሻዎችም በዚህ ወንጀል ተጠያቂዎች ናቸው ትላለች።
በትግራይ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር የምትጋራው ኤርትራ፤ ከትግራይ አስተዳዳሪዎች ጋር ለረዥም ዓመታት የዘለቀ ቂም በቀል አላት።
በቅርቡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኬንያ ያደረጉት ጉብኝት ማጠናቀቂያ ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ከውጪ አገር ጋዜጠኞች ፊት ቆመው ነበር።
የፕሬስ ነጻነት ከሌለባት አገር የመጡት መሪ፤ ጋዜጠኞች ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ሲያነሱባቸው ብስጭታቸው በግልጽ ይታይባቸው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ወታደሮቻቸው በትግራይ ፈጽመውታል ስለተባለው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት አላሳዩም።
“ሁሉም ሰው [በኤርትራ ወታደሮች ተፈጽሟል ስለተባለ] የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ዘረፋ፣ መድፈር ያወራል ይህ ቅዠት ነው። ይህን ፈጥረው የሚያወሩ ናቸው፤ እኔ ይህን ውሸት የሚያመርት ፋብሪካ ነው እለዋለሁ” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ዘገባ ውስጥ በቀረቡ ክሶች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር እና የሰላም ድርድሩን ያሸማገለው የአፍሪካ ኅብረት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ሁለቱም ምላሽ አልሰጡም።
ባለፈው ጥቅምት የተደረሰው የሰላም ስምምነት በትግራይ ውስጥ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል። በአሁኑ ወቅት ጦርነት የለም። በተለይ የምግብ እና የመድኃኒት እርዳታዎች ወደ በርካታ አካባቢዎች እየደረሱ ሲሆን፣ የባንክ እና የኮምዩኒኬሽን አገለግሎቶች ሥራ ጀምረዋል።
ከዓመት በላይ ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ መልሰው ለመገናኘት እና ለመነጋገር ችለዋል።
በስምምነቱ አንቀጽ አራት መሠረት ሁሉም ወገኖች የትኛውንም አይነት ወሲባዊ እና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲያወግዙ ያዛል።
“ወሲባዊ ጥቃት ስምምነቱን መጣስ ነው” ይላሉ የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባድር። “የስምምነቱን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ያስችላሉ በሚል ስናነሳቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል፣ ጥሰት ሲፈጸም አሸማጋዮቹ ወጥተው መናገር አለባቸው የሚለውን ነው።”
የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው ድርጅት ገለልተኛ መርማሪዎች እና ጋዜጠኞች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንዲፈቀድላቸው እየጠየቀ ይገኛል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን ሥራው እንዲቆም የሚያደርገው ጥረት በጣሙን ያሳስበናል” ብለዋል ላቲሻ።
ጨምረውም የጥቃት ሰለባዎች ፍትህ እንዲያገኙ እና ለየትኛውም የእርቅ ሂደት የሚደረጉ ምርመራዎች እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ጥቃት ይፈጸምብኛል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር” ትላለች ህሊና።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ህሊና በጎዳና ላይ በቆሎ በመሸጥ ትኖርበት ከነበረው የሁመራ አካባቢ ተፈናቅላ ሽራሮ ውስጥ ትገኛለች።
ኅዳር 10/2015 ዓ.ም. ህሊና አምሽታ ወደ ቤቷ ስትመለስ ሰዓት እላፊ ጥሰሻል ተብላ በሁለት የኤርትራ ወታደሮች ተያዘች። እሷም መታወቂያ እንደሌላት ስትነግራቸው ወደ አንድ ባዶ ቤት ይዘዋት ሄዱ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህሊና እንደምትለው ከወታደሮቹ ገጽታ እና ከቋንቋቸው ዘይቤ በመነሳት ከኤርትራ መሆናቸውን መናገር እንደምትችል ትገልጻለች።
“ወደ ባዶ ቤት ወሰዱኝ። መሳሪያ አውጥተው ‘ዝም የምትይ ከሆነ አንጎዳሽም።’ እኔም የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ነገር ግን እንዳይገድሉኝ ለመንኳቸው።”
ሌሊቱን በሙሉ ሲደፍሯት አድረው ሲነጋ እንደለቀቋት እና ከዚያ በኋላም በማርገዟ በመደፈር ልጅ ከመውለድ ብሞት ይሻለኛል በማለት ጽንሱን እንዳቋረጠችው ተናግራለች።
የእርዳታ ሠራተኞች ለቢቢሲ እንደገለጹት የኤርትራ ወታደሮች ከሽራሮ አቅራቢያ ይገኛሉ።
በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ መውጣት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ ከዋና ዋና ከተሞች በመውጣት ከድንበር አቅራቢያ በሚገኙ የትግራይ አካባቢዎች ውስጥ ይገኛሉ።
ጥራቱ በጣም ደካማ በሆነው የስልክ መስመር ቢቢሲ ያናገራቸው የ80 ዓመቷ አዛውንት ሻሹ እምባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ነበር። በቃለ ምልልሱ መቀጠል ይፈልጉ እንደሆነ ጠይቀናቸው ፈቃደኛ ሆነዋል።
እንደ ለታይ ሁሉ ሻሹ በዚህ ጦርነት ወቅት ሁለት ጊዜ የመደፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። አንደኛው በጦርነቱ ወቅት ሌላኛው ደግሞ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ።
ባለፈው ኅዳር በተፈጸመባቸው አስከፊ የመደፈር ጥቃት ሳቢያ ሰገራቸውን እና ሽንታቸውን ለመቆጣጠር አይችሉም።
“ሁለት ሦስት ሰዎች በአንዲት ሴት ላይ፣ በጣም ነው ግፍ የተፈጸመብኝ። ከዚህ በኋላም የሚጠቅም አካል እንዳይኖረኝ በሚያደርግ ሁኔታ ነው ሰቆቃ የተፈጸመብኝ።”








