ባይደን ‘ስትሰልል’ የነበረችውን ፊኛ መትተን በመጣለችን ቻይናን ይቅርታ አንጠይቅም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው የስለላ መሳሪያ ነች በማለት መትታ የጣለቻትን ተንሳፋፊ ፊኛን በተመለከተ ቻይናን ይቅርታ እንደማትጠቅ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ የአየር ክልል ውስጥ ተመትታ የወደቀችው በራሪ አካል የስለላ ተግባር ስትፈጽም ነበር ብለዋል።
አሜሪካ ባለፉት ሳምንታት ይህችን ፊኛ ጨምሮ አራት በራሪ አካላትን መጥታ ጥላለች። ሦስቱ በራሪ አካላት መነሻም ይሁን ተልዕኳቸው ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ፕሬዝዳንቱ ክስተቱን በተመለከተ ሲናገሩ አገራቸው ተመሳሳይ በራሪ አካላትን መለየት የሚያስችላትን ቴክኖሎጂ ታጠናክራለች ብለዋል።
ባይደን በጉዳዩ ዙሪያ ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር እንደሚነጋገሩም ጨምው ተናግረዋል።
ባይደን ከኤንቢሲ ኒውስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ከቻይና ፕሬዝዳንት ጋር መቼ እንደሚነጋገሩ ባይገልጹም፤ “ዢ በአሁኑ ወቅት ፈጽሞ የማይፈልጉት ነገር ቢኖር ከአሜሪካ እና ከእኔ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማበላሸት ነው” ብለዋል።
“በዚህ ጉዳይ ላይ እስከ መጨረሻው መረጃው ይኖረናል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ ግን ፊኛውን መትተን በመጣላችን ይቅርታ አልጠይቅም” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ቻይና በተደጋጋሚ ተመትታ የወደቀችው ፊኛ ተልዕኮዋ ስለላ አለመሆኑን ስትገልጽ ቆይታለች።
ቤይጂንግ ፊኛው የእርሷ መሆኑን ባትክድም ዓላማዋ ግን የአየር ንብረት ሁኔታን መከታተል መሆኑን እና ወደ ሰሜን አሜሪካ የበረረችው በነፋስ ተገፍታ መሆኑን ገልጻ ነበር።
ባይደን ግን በ40ሺህ ጫማ (12 ኪሎ ሜትር) ከፍታ ላይ ስትበር የነበረችው ፊኛ የቅኝት ሥራ ስታከናውን ነበር ብለዋል።
ባይደን ከዚህች ፊኛ በተጨማሪ በአላስካ እንዲሁም በአሜሪካ እና በካናዳ ድንበር አቅራቢያዎች ተመትተው ስለወደቁት ሦስት በራሪ አካላት ሲናገሩ፤ “ቁሶቹ ምናልባት ለምርምር ተግባር የተሰማሩ ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።
የአሜሪካ ደኅንነት ተቋማት ግምት በራሪ አካላቱ “የግል ኩባንያዎች ወይም የጥናት ተቋማት፣ለመዝናኛ ነት ወይም ለምርምር ያሰማሯቸው ሊሆኑ ይችላሉ” የሚል ግምት እንዳላቸው ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ተናግረዋል።
ባይደን የቻይና ፊኛ በአሜሪካ ሰማይ መገኘትን ተከትሎ አስተዳደራቸው የአገሪቱን የአየር ክልል በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል የራዳር ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማዘዛቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ወደፊት አደጋ ሊፍጥሩ የሚችሉ እና ጉዳት የማያስከትሉ ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት መለየት እንዲቻል እና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ቴክኖሎጂው ተግባራዊ እንዲሆን ትዕዛዝ መስጠታቸውን አብራርተዋል።
ይህ የባይደን አስተያየት የተሰጠው አሜሪካ ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላትን መትታ መጣሏ ኪሳራ ነው የሚሉ አስተያየት ከተሰሙ በኋላ ነው።
ዴሞክራቱ የምክር ቤት አባል ጂም ሂም “ፊኛን መትቶ ለመጣል ወታደራዊ ተልዕኮ ማከናወን እጅግ እጅግ በጣም ውድ ነው። በዚህ ላይ በደንብ መታሰብ አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደ ፊኛ ያሉ በዝግታ የሚጓዙ በራሪ አካላት ምድር ላይ ባሉ ሰዎች ላይ የሚያስከትሉት ቀጥተኛ አደጋ አለመኖሩን በመግለጽ በራሪ አካላቱ ተመትተው እንዲወደቁ የተደረጉት የአገር ጥቅም ለማስከበር እና የበረራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ነው የሚሉ አስተያየቶችን ሲሰጡ ነበር።
በሌላ በኩል የካናዳ ፖሊስ በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ከፍል ተመትቶ የወደቀውን በራሪ አካል ስብርባሪ መፈለጉን እንደሚያቆም አስታውቋል።
የአገሪቱ ፖሊስ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ሰብርባሪውን የማግኘቱ ዕድል አነስተኛ በመሆኑ ነው ብሏል።












