ሴቶች ለጉዳት ዳርጎናል ባሉት የፀጉር መንከባከቢያ ምርት ላይ ክስ መሰረቱ

የፎቶው ባለመብት, OLAPLEX
ታዋቂው የፀጉር መንከባከቢያ ምርት የሆነው የኦላፕሌክስ ምርቶች ፀጉራችንን በመነቃቀል፣ ቁስለት እና ሌሎችንም ችግሮች አስከትሎብናል ያሉ 28 ሴቶች በአሜሪካ ክስ መሰረቱ።
ይህ ኦላፕሌክስ የተባለው የፀጉር መንከባከቢያ አምራች የተጎዳ ፀጉርን “የሚጠግኑን እና መልሶ እንዲያገግም የሚያደርጉ ናቸው” የሚላቸውን የፀጉር መንከባከቢያ እና መታጠቢያዎችን ያመርታል።
ነገር ግን የቀረበበት ክስ እንደሚለው የኦላፕሌክስ ምርቶች ጎጂ ኬሚካሎችን የሚጠቀም በመሆኑ የሴቶችን የጭንቅላት ቆዳ እና ፀጉርን አደገኛ ሁኔታ ላይ ጥሏል ተብሏል።
በኦላፕሌክስ ላይ ክስ የመሠረቱት ሴቶች ለደረሰባቸው ጉዳት በጋራ የ75,000 ሺህ ዶላር ካሳ ጠይቀዋል።
ኦላፕሌክስ ግን ምርቶቹ ደኅንነታቸው ተጠበቀ መሆኑን የሚያመለክት የምርመራ ውጤት ይፋ አድርጎ፣ መሠረተ ቢስ ነው ያለውን ክስ አጥብቆ እንደሚከላከለው በማኅበራዊ ገጹ ላይ አመልክቷል።
ከዘጠኝ ዓመት በፊት አሜሪካ ካሊፎርኒያ ውስጥ ምርቶቹን ይፋ ያደረገው ኦላፕሌክስ፣ የተፈቀዱ የንጥረ ነገር ውህዶችን በመጠቀም ምርቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳ ፀጉርን እንዲያገግም እንደሚያደርጉ መረጋገጡን ይናገራል።
ምርቱ በመላው ዓለም የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይ ፀጉራቸውን ለሚያቀልሙ ሰዎች የተዘጋጁ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት የኦላፕሌክስ ምርቶች ከፍተኛ ስኬትን ያገኙ ሲሆን፣ ኪም ካርዳሺያን እና ድሪው ባሪሞርን በመሳሰሉ ታዋቂ ሰዎች ጭምር ተቀባይነትን ለማግኘት ችሏል።
ባለፈው ሳምንት ካሊፎርኒያ ውስጥ በኦላፕሌክስ ላይ ክስ ያቀረቡት ሴቶች “አንዳንዶቹ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ፀጉራቸውን እንዳጡ፣ እንዲሁም ሌሎቹ ደግሞ በጭንቅላታቸው ላይ የተመለጡ ቦታዎች እንዲፈጠሩ” ማድረጉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ፀጉራቸው ደረቅ፣ የሚሰባበር እን ወዝ አልባ እንዲሆን አድርጎብናል በማለት በምርቱ ያደረሰባቸውን ጉዳት የሚያሳዩ የፎቶ ማስረጃዎች ከክሱ ጋር ተያይዟል።
አንዳንዶቹ ሴቶችም በጣም ማሳከክ፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት፣ ማቃጠል፣ ቁስል እና ሌሎችም ችግሮች እንደገጠማቸው እና በዚህም ምክንያት ድብታ ውስጥ መግባታቸውን የክስ ሰነዶቹ ላይ ተገልጿል።
በክሱ ላይ እንደተጠቀሰው የኦላፕሌክስ ምርቶች ፀጉርን የሚነቃቅሉ እና በጭንቅላት ቆዳ ላይ የተለያዩ አይነት ጉዳቶችን የሚያስከትሉት ሊሊያን እና ፓንቴኖል የተባሉ የኬሚካል ውህዶች አሉበት።
ሊሊያን የተባለው ንጥረ ነገር ከጤና ጋር በተያያዘ ተጽእኖ አለው ተብሎ ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ኅብረት አስከታገደበት ጊዜ ድረስ ለሽቶ እና ለመዋቢያ ምርቶች ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።
ኦላፕሌክስ እንደሚለው ግን የተባለውን የኬሚካል ንጥረ ነገር በዓለም ዙሪያ ለጥንቃቄ ሲባል ከሁሉም ምርቶቹ ውስጥ ማስወጣቱን ቢገልጽም፣ ከሳሾቹ ግን ኬሚካሉ አሁንም በሽያጭ ላይ በሚገኙ ምርቶች ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
የከሳሽ ጠበቆች እንዳሉት በሴቶቹ ፀጉር እና ቆዳ ላይ ለተከሰቱት ችግሮች ሌሎች ምክንያቶች ካሉ በሚል በጥንቃቄ ምርመራ አድርገው ለችግሩ “ምርቶቹ ብቸኛ ሰበብ ሆነው” ተገኝተዋል ብለዋል።
ኦላፕሌክስ ግን ይህንን ክስ አጥብቆ ያስተባበለ ሲሆን፣ ምርቶቹም “የፀጉር መነቃቀል እና መሰባባርን አያስከትሉም” በማለት ተከራክሯል።
“ገለልተኛ በሆነ የሦስተኛ ወገን ቤተ ሙከራ ውስጥ በተካሄደ ምርመራ የኦላፕሌክስ ምርቶች ደኅንነታቸው ተጠበቀ እና ውጤታማ መሆናቸውን የተገኘው ውጤቱ አሳይቷ” በማለት አምራቹ ሌሎችም ጥናቶችን በማያያዝ በድረገጹ ላይ ምላሽ ሰጥቷል።
የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በትዊተር ገጻቸው ላይ የፀጉር መነቃቀል ከባድ እና ስሜትን የሚጎዳ ነገር ነው፤ “ነገር ግን ምርቶቻቻን ለዚህ ክስተት ምክንያት አይደሉም” ሲሉ አስፍረዋል።












