መኪና ውስጥ ከኋላው ተቀምጦ በነበረው ፖሊስ በተገደለው ታዳጊ ዙሪያ ምርመራ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, POLICE HANDOUT
የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ቢሮ መኪና ውስጥ ከኋላው ተቀምጦ በነበረው ፖሊስ የተገደለውን የዋሽንግተን ዲሲ ታዳጊ ሞት ሊመረምር መሆኑ ታውቋል።
የፖሊስ መኮንኖች የተሰረቀውን መኪና ከፍተው ሲገቡ የ17 ዓመቱ ዳላኔዮ ማርቲን ተኝቶ ነበር ሲል ፖሊስ አስታውቋል።
ልብስ ላይ የተገጠመ ካሜራ እንደሚያሳየው ፖሊስ በቁጥጥር ስር ሊያውለው ወደ ተሽከርካሪው በድብቅ ሲገባ ያሳያል። ጥቁሩ ተጠርጣሪ ታዳጊ ፖሊሱ ከኋላ ወንበር እንደተቀመጠ መኪናውን በፍጥነት አስነስቶ ያሽከረክራል።
የፖሊስ መኮንኑ መኪናውን እንዲያቆም ከነገረው በኋላ ታዳጊው ወጣት ላይ ከኋላው ተኩስ ይከፍትበታል።
የፍትህ ቢሮ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ "የህይወት መጥፋት በተለይም የታዳጊ ሞት ሁሌም አሳዛኝ ነው" ብሏል።
ልብስ ላይ የተገጠመውን ቪዲዮ ምስል "በጣም የሚያናድድ" ብሎታል። ለታዳጊው ቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመዶችም መጽናናትን ተመኝቷል።
የፖሊሱ ማንነት የማይታወቅ ሲሆን ከዋሽንግተን ዲሲ ሜትሮ ፖሊስ ጋር ባደረገው ምርመራ የአሜሪካ ፓርክ ፖሊስ አባል መሆኑ ብቻ ታውቋል።
ማክሰኞ የተለቀቀው ምስል የፖሊስ መኮንኖች ተጠርጣሪውን ሞተሩ ባልጠፋ መኪና ውስጥ እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ሲማከሩ ያሳያል። ክስተቱ ቅዳሜ ከምሽቱ 3፡00 በፊት መፈጸሙ ታውቋል።
እንደ ጊዜያዊ መስኮት የሚያገለግል ፕላስቲክ በመቁረጥ ከመንዳቱ በፊት እንዴት መከልከል እንዳለባቸውም ተወያይተዋል።
አንድ የዋሽንግተን ፖሊስ “እባክህ [በተሽከርካሪው ውስጥ] ውስጥ እንዳትሆን” ሲል የፓርክ ፖሊስ አባልን ሲመክር በቪዲዮው ላይ ይሰማል።
"ሰውዬ አቁም! በቃ ልቀቀኝ! ልሂድ!" ብሎ የፖሊስ መኮንኑ ላይ ሲጮህ ይሰማል።
አከታትሎ ከመተኮሱ በፊት "አቁም! አቁም! አለበለዚያ እተኩሳለሁ!" ሲል ይናገራል።
ከሰኮንዶች በኋላ መኪናው ከአንድ ቤት ጋር ተጋጭቷል። ፖሊሶች ለታዳጊው የህክምና እርዳታ ሲያደርጉ ታይተዋል። ከመኪናው ውስጥ ሽጉጥ መገኘቱን ፖሊሶች ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፓርክ ፖሊስ ህብረት ሊቀ መንበር ለፖሊሱ ተሟግተዋል።
"በመኪናው ውስጥ የገባበት ህጋዊ ምክንያት አለ። ኃይል መጠቀሙም ትክክል ነበር። ማህበሩ መኮንኖቹ የወሰዱትን እርምጃ ይደግፋል” ሲሉ ሊቀ መንበሩ ስፔንሰር ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።
የታዳጊዋ እናት ጥይት የተኮሰው ፖሊስ ከሥራ ታግዶ ህግ ፊት እንዲቀርብ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
"ክስተቱ በጣም ያማል” ሲሉ ቴራ ማርቲን ረቡዕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።












