አሜሪካዊቷ ሊጠልፈኝ ነበር ያለችውን የታክሲ ሹፌር በጥይት መትታ ለሞት አበቃችው

የፎቶው ባለመብት, EL PASO POLICE DEPARTMENT
አሜሪካዊቷ ሊጠልፈኝ ነበር ያለችው የታክሲ (ኡበር) አሽከርካሪ ላይ ከተኮሰች በኋላ በግድያ ወንጀል መከሰሷን ፖሊስ አስታወቀ።
በቴክሳስ ግዛት የምትገኘው የድንበር ከተማ ኤል ፓሶ ፖሊስ እንዳለው፣ አሜሪካዊቷ ፎኤቤ ኮፓስ ፍቅረኛዋን ለመጠየቅ ወደ ኤል ፓሶ እየተጓዘች ነበር።
በመሃል ግን ያለ ፈቃዷ ተጠልፋ ወደ ሜክሲኮ እየተወሰደች እንደሆነ በማሰብ የታክሲ አሽከርካሪው ዳንኤል ፔድራ ጋርሺያ ላይ መተኮሷን ባለሥልጣናት በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
የ52 ዓመቱ ዳንኤልም ክፉኛ በመጎዳቱ ለበርካታ ቀናት በሆስፒታል ሕክምና ሲደረግለት ከቆየ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።
የፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው ኮፓስ መኪናው ውስጥ እያለች 'ጁዋርዝ፣ ሜክሲኮ' የሚል የትራፊክ ምልክት ተመልክታለች።
ይሁን እንጂ ጁዋርዝ እና ኤል ፓሶ ከተሞች በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ድንበር ጎን ለጎን የሚገኙ ከተሞች ናቸው።
የፖሊስ መረጃ ጨምሮ እንዳስረዳው ግለሰቧ ተጠልፌያለሁ ብላ ካሰበች በኋላ ከቦርሳዋ ውስጥ ሽጉጥ አውጥታ አሽከርካሪው ጭንቅላት ላይ ተኩሳለች። መኪናው ከመቆሙ በፊትም ከአጥር እና ከመሰናክሎች ጋር ተጋጭቷል።
የኬንተኪ ነዋሪ የሆነችው እና ፍቅረኛዋን ለመጠየቅ እየተጓዘች የነበረችው ኮፓስም የአስቸኳይ እርዳታ የጥሪ ማዕከል ወደ ሆነው 911 ላይ የደወለች ሲሆን፣ የአሽከርካሪውን ፎቶ በማንሳትም ለፍቅረኛዋ ልካለች።
ፖሊስም ኮፓስን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ሲያካሂድ ቆይቷል።
ምርመራውም፣ ጠለፋ ተፈፅሟል የሚለውን አሊያም አሽከርካሪው ፔድራ ከኮፓስ መዳረሻ በድንገት አቅጣጫ መቀየሩን እንደማያሳይ የኤል ፓሶ ፖሊስ መግለጫ አስረድቷል።












