ደቡብ አፍሪካን ለሩሲያ የጦር መሳሪያ በማቅረብ የወነጀሉት የአሜሪካ አምባሳደር ይቅርታ ጠየቁ

ሌዲ አር በመባል የምትታወቀው የሩስያ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እየሸጠች ነው በማለት የከሰሱት የአሜሪካ አምባሳደር ይቅርታ መጠየቃቸውን የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሐሙስ እለት የአሜሪካው አምባሳደር ሩበን ብሪጌቲ በታህሳስ ወር አንድ የሩሲያ መርከብ ጥይቶች እና የጦር መሳሪዎች ከኬፕታውን ጭኖ ወጥቷል ሲሉም ክስ አቅርበው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የሸጥኩት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ሬከርድ የለኝም ስትል ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንዲጣራ አዘው ነበር።

የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት ቃለ አቀባይ ጆን ከርቢ በክሱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለማቅረብ አንገደድም ብለው ነበር።

ሆኖም ቃለ አቀባዩ “ጉዳዩ የከበደ ነው” በማለትም አገራቸው በዩክሬን ለሚደረገው ጦርነት አገራት ለሩሲያ ድጋፍ እንዳይሰጡም የምታሳስበውን ማስጠንቀቂያም ተናግረዋል።

አሜሪካዊው አምባሳደር ከደቡብ አፍሪካ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር ከተገናኙ በኋላም “በአደባባይ ላይ በሰጠሁት አስተያየት የተፈጠሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶች ለማረም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ” ሲሉም በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ውይይቱ “በደቡብ አፍሪካና አሜሪካ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት እንዲሁም መሪዎቻችን የሰጡንን ጠቃሚ አጀንዳ ያረጋገጥንበት ነው” ብለዋል አምባሳደሩ ።

የደቡብ አፍሪካ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በምላሹ አሜሪካ እያደረገችው ያለው “የጩኸት ዲፕሎማሲ” ነው ሲል ወቅሷል። አክሎም “ደቡብ አፍሪካ ለአሜሪካ አትንበረከክም” ብሏል።

“አሜሪካ ናት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ የጣለችው። ከሩሲያ ጋር ባላቸው የባላንጣነት ጉዳይ ጎትተው ሊያስገቡን አይገባም” ሲሉም የፕሬዚዳንቱ ሚኒስትር ኩምቡድዞ ንትሻቭሄኒ ለደቡብ አፍሪካው የህዝብ ሚዲያ ኤስኤቢሲ ተናግረዋል።

የሚኒስትሯ ጠንከር ያለ አስተያየት የተሰጠው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከደቡብ አፍሪካ አቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በስልክ መነገጋራቸው ክሬምሊን ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ነው።

ሌዲ አር በመባል የምትታወቀው የሩስያ መርከብ በታህሳስ ወር በኬፕታውን አቅራቢያ በሚገኘው የባህር ኃይል ጣቢያ ላይ መታየቷ በወቅቱ በአካባቢው ፖለቲከኞች ዘንድ ጥያቄ አስነስቶ ነበር።

መርከቧ ወደ ሩሲያ ከመመለሷ በፊት የጦር መሳሪያ መጫኗ የታወቀ ነገር የለም።

ውንጀላው እውነት ከሆነ ደቡብ አፍሪካ “በጭቆና፣ በጥቃት ወይም በሽብርተኝነት ከተሰማሩ መንግሥታት ጋር የጦር መሳሪያ አትገበያይም” የሚለውን የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህጓን የጣሰ ነው።