በኢትዮጵያ ለአንበጣ የተረጨው ፀረ ተባይ እንዴት 76 ቢሊዮን ንቦች ላይ ጉዳት አደረሰ?

ንብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ ከ2019 - 2021 (እኤአ) የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን ለመከላከል በተጠቀመችው ፀረ ተባይ ኬሚካል ምክንያት 76 ቢሊዮን ንቦቿ ላይ ጉዳት መድረሱን አንድ ዳሰሳ አመለከተ።

ዳሰሳው ‘አግሮኖሚ’ በተባለ ጆርናል ላይ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የወጣ ሲሆን፣ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የተረጨው ኬሚካል 76 ቢሊዮን የሚሆኑ ንቦች ቀፏቸውን ትተው እንዲሄዱ አልያም እንዲሞቱ አድርጓል ይላል።

ከ2019 - 2021 ባሉት ሁለት ዓመታት በ25 ዓመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በምሥራቅ አፍሪካ ተከስቶ ነበር።

ይህም ወረርሽኝ በአካባቢው ሰፊ የእርሻ መሬት ላይ የነበረን እህል በማውደሙ የአካባቢው ሕብረተሰብ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ ጥሎት ነበር።

አግሮኖሚ ጆርናል ላይ በወጣው ዳሰሳ ላይ ከተሳተፉ መካከል አንዱ የሆኑ አቶ አዲስ ቢሆነኝ “አንበጣ በተክሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሲያደርስ ንብን ጨምሮ አበባ የሚቀስሙ ሌሎች ነፍሳት ላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ጉዳት ያስከትላል። ምክንያቱም ተክሎች ከሌሉ ንብ እና ሌሎች ነፍሳት ሊኖሩ አይችሉም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ2019 እስከ 2021 የአንበጣ መንጋ ለማጥፋት የተረጩት ኬሚካሎች ተለይተው የሚታወቁ ሲሆን፣ አንበጣውን ከማጥፋት ባሻገር ንብ ላይ ጉዳት አንደሚያደርስ ተረጋግጧል ይላሉ።

ይህንን ሀሳብ መሠረት በማድረግ ከዚህ በፊት የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች እና ዘገባዎችን እንደ ምንጭ በመጠቀም ዳሰሳውን ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ አዲስ፣ በዚህ ዳሰሳ ኬሚካሉ ንቦች ላይ በተዘዋዋሪ ያደረሰውን ጉዳት እና ያለውን ስጋት ለማወቅ መሞከራቸውን ጠቅሰዋል።

አበባ የምትቀስም ንብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአንበጣ ወረርሽኙ “በምን ያህል ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል እና ሌሎች እጽዋት ላይ ያደረሰውን ጉዳት መሠረት በማድረግ ንቦቹ ላይ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የመጣውን ጉዳት ለማሳየት ሞክረናል” ይላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ንቦቹ ላይ የደረሰው ጉዳት በአገሪቱ የአንበጣ ወረርሽኝ የደረሰባቸው ክልሎች በኦሮሚያ፣ በሶማሊያ፣ በአፋር፣ በምሥራቅ አማራ እና የትግራይ አዋሳኝ ቦታዎችንም አንደሚጨምር ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የተጠቀመቻቸው ፀረ ተባይ ኬሚካሎች የተወሰነውን የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝን ለማጥፋት ካላቸው ጥቅም ባሻገር፣ ኋላ ላይ በአካባቢ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ስለሚያመዝን በአውሮፓ አገራት የተከለከሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ይህ ፀረ ተባይ ኬሚካል በሚረጭበት ወቅት ንቦችም የኬሚካሉ ሰለባ ሆነዋል።

“ማላቲዮን (Malathion) እና ክሎርፒሪፎ (Chlorpyrifo) የተባሉት ኬሚካሎች በተዘዋዋሪ ከአየር፣ ከአፈር እንዲሁም ከውሃ ጋር ስለሚቀላቀሉ የቀሩት ንቦች ከዚያ ወስደው የሚሰሩት ማር ላይም ኬሚካሉ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አለ።”

በሶማሊያ በተመሳሳይ ወቅት በተከሰተው ወረርሽኝ አገሪቱ የተጠቀመችው የኬሚካል ዓይነት የተሻሻለ እንደነበረ ምሁሩ ያስታውሳሉ።

በወቅቱ መንግሥት የነበረውን የአንበጣ ወረርሽኝ ለመቋቋም ከፍተኛ የሆነ የኬሚካል ርጭት በማካሄዱ የአንበጣውን ወረርሽኝ መቆጣጣር ቢቻልም አጠቃቀሙ ግን ተዘዋዋሪ ጉዳት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

ነገር ግን ይህ ኬሚካል በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል ብቻ የሚገኙ የንብ ዝርያዎችን አንዳልጎዳ አረጋግጠዋል።

በዚህ ጥናት ላይ ከ2017 እስከ 2021 በኢትዮጵያ የማር ምርት 80 በመቶ መቀነሱን እና ይህም የ500 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ሰብል አውዳሚ የሆነውን አንበጣ በመቆጣጣር ቢሳካላትም፣ የተረጨው ኬሚካል ቀጥተኛ ያልሆነ ጉዳት እንዳያደርስ የተሻሉ የኬሚካል ዓይነቶችን መጠቀም ይቻል እንደነበር ምሁሩ ተናግረዋል።

የደረሰውን ጉዳትም ለመቋቋም ንቦችን እንደ አዲስ ማራባት እና ዕጽዋቶችን መትከል መፍትሄ መሆኑን አቶ አዲስ ተናግረዋል።