ትምህርት በተጀመረባት ትግራይ ጠፍጣፋ ድንጋይ በመጠቀም እያስተማሩ ያሉት መምህር

መምህር ጽገ በማስተማር ላይ

የፎቶው ባለመብት, MATIOS/DESTA GIRMAY FB

በትግራይ ከሁለት ዓመት በላይ ተቋርጦ የቆየው ትምህርት መጀመሩን ተከትሎ መምህር ጽገ አበራ የነተበ ልብሳቸውን እና ኮንጎ ጫማቸውን አድርገው ወደ ሥራ ተመልሰዋል።

ነገር ግን የመማሪያ መጽሐፍት፣ እስክሪብቶ ወይም ጥቁር ሰሌዳ የለም።

“ልብስ የሌለው፣ ቤቱ ቤት የማይመስል አስተማሪ አለ እንዴ? ግን ችግሮቻችንን ይዘን ሥራውን መሥራት አለብን” ይላሉ።

የብዙ መቶ ሺዎች ሕይወትን የቀጠፈውን ጦርነት ተከትሎ ላለፉት 17 ዓመታት ወደ አስተማሩበት ነበለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመመለሳቸው መምህር ጽገ ደስተኛ ናቸው።

በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሁለቱንም ወላጆቹን አጥቶ እንባው በደረቀበት ልጅ ይመስሉታል።

የነበለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በአምባ ሰነይቲ ወረዳ ይገኛል።

አካባቢው ከፍተኛ ውጊያ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት ተዋጊዎች እየሰፈሩበት እንደ ምሽግም ይገለገሉበት ነበር።

በርካታ የትምህርት ቁሳቁሶች ተቃጠለው ከጥቅም ውጪ እንደሆኑ፣ እንደወደሙ መምህሩ ይናገራሉ።

“ትምህርት ቤታችን ሀብታም፣ አርአያ እና የአምባ ሰነይቲ ቅርስ ነበር። ብዙ ንብረትም ነበረው። አሁን የትምህርት ጥራትን ይደግፋሉ ተብለው የሚታሰቡት ቁሳቁሶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፣ ተበላሽተው፣ የተቃጠሉ ንብረቶችን ብቻ ቀርተዋል፤ ኮምፒውተሮች የሉም።”

በጦርነቱ ወቅትም ወደ ትምህርት ቤቱ መመላለስ ያላቆሙት መምህር ጽገ “አዝነን እያለቀስን ነው የምንሄደው” ይላሉ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ።

የትግራይ ትምህርት ቢሮ እንዳስታወቀው በክልሉ ከ88 በመቶ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ወድመዋል። ወደ 2.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ህጻናት እና ወጣቶች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።

“መጽሐፍት የለኝም”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መምህር ጽገ አበራ በነበለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች የሂሳብ ትምህርት ያስተምራሉ።

ነገር ግን ትምህርት ቤቱ መምህራኖቹን ሙሉ በሙሉ ስላልተቀበለ ሂሳብ እና ባዮሎጂን ለአራተኛ እና ሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች የማስተማር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

ተማሪዎቹም ቢሆኑ እስክሪብቶ ወይም ደብተር የላቸውም። አንዳንዶች ሳይለብሱ እና ተርበው ነው የሚመጡት ይላሉ።

መምህሩ እንደሚሉት በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተቃጠሉ እና በጥይት የተደበደቡ ክፍሎች ይታያሉ። አስተማሪ ተማሪዎቹን የሚያስተምርበት መጽሐፍት እና ጥቁር ሰሌዳዎች የተሟሉ አይደሉም።

መምህር ጽገ ግን ለዚህ ችግር መፍትሔ ያሉት መላ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል። ይህም ጠፍጣፋ ድንጋይን እንደሰሌዳ ተጠቅሞ ተማሪዎቻቸውን እያስተማሩ መሆናቸው ነው።

“ትምህርቱን የጀመርነው በድንጋይ ላይ ወይም በጥላ ስር እናስተምራለን በሚል ሀሳብ ነው” ሲሉ መምህር ጽገ ተናግረዋል።

“ትግራይም ውስጥ የተቀረው ድንጋይ ነው፤ ሌላው በሙሉ ወድሞል ወይም ተወስዷል። እኔ ግን ያገኘኋትን ድንጋይ ተጠቅሜ ያሰብኩትን እያስተማርኩ ነው” ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ መምህራን በጦርነቱ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የቀሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለሳቸው ከገቡበት የሥነ ልቡና ቀውስ እንዲያገግሙ እንደሚረዳ ተስፋ ያደርጋሉ።

“ከቤቱ የሚመጣው ተማሪ ደብተር፣ እርሳስ፣ እስክርቢቶ ብቻ ሳይሆን የሚለብሰው ልብስ፣ የሚበላው ምግብ የለውም። ብዙ ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለበት ተማሪ ነው ያለን። እኛ ግን የተማሪውን ትኩረት ወደ መደበኛው ሕይወት እንዲመልስ እየሰራን ነው” ሲል ያስረዳል።

አብዛኛዎቹ መጽሐፍቶች እና ሌሎች የማስተማሪያ መሳሪያዎች ተቀዳደው የትም ተጥለው እንደሚታዩ ትምህርት ቤቱን የጎበኙ ግለሰቦች ይናገራሉ።

“አሁን የያዝኳት መጽሐፍ የተቀደደች ናት። መጽሐፍት ፈጽሞ የሌላቸው ክፍሎችም አሉ። ነገር ግን፣ መጽሐፍ የለኝም፣ ጥቁር ሰሌዳ የለኝም የሚለውን ከጭንቅላታችን አውጥተን ትምህርት ቤቱ ውስጥ እንውላለን፤ በዚህም ተማሪዎች እንዲመጡ እናበረታታለን” ይላሉ መምክር ጽገ።

መምህር ጽገ በማስተማር ላይ

የፎቶው ባለመብት, DW

ዳግም አርአያ መሆን የሚፈልጉት መምህር

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሞቱበት እና ሚሊዮኖች ለችግር በተዳረጉበት የሁለት ዓመት ጦርነት ውስጥ በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች እንደተፈጸሙ የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ የመብት ተሟጋቾች ሪፖርት አድርገዋል።

የስድስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት መምህር ጽገ አበራም በጦርነቱ ወቅት ከከባድ የጦር መሳሪያዎች ጥቃት ለመሸሽ ሲሉ ከልጆቻቸው ጋር ከቤታቸው ርቀው በሄዱበት ጊዜ በረሃብ ያሳለፏቸውን አስቸጋሪ ጊዜያት ያስታውሳሉ።

በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት ቤተሰባቸውን እና በርካታ ዘመዶቻቸውንም አጥተዋል።

“አሁን በህይወት የሌሉ ከስምንት በላይ የቤተሰብ አባላት አሉኝ። በከባድ መሳሪያ የሞቱ የቤተሰብ አባላት አሉኝ። በአድዋ ከተማ በእንዳባገሪማ አካባቢ በግፍ ከተገደሉት መካከል መላ ቤተሰብ የጠፋበት ዘመድ አሉኝ።

“በህክምና እጦት በሆስፒታል ውስጥ የሞቱ ዘመዶች አሉኝ እንዲሁም ጦርነት ውስጥ የሞቱ ዘመዶችም አሉኝ። የወንድሜን አስከሬን አላገኘሁትም። . . . እዛ ውስጥ መግባት አልፈልግም ምክንያቱም ስሜታዊ ያደርገኛል . . .” በማለት እንባ እየተናነቃቸው የጀመሩትን መጨረስ አልቻሉም።

ከሰኮንዶች ዝምታ በኋላ “በሥራዬ አርአያ፣ የተመሰገንኩ አስተማሪ ነበርኩ። አሁንም በሥራዬ አርአያ መሆን ብቻ ነው የምፈልገው” ሲል በጦርነት የተጎዳው የተማሪዎቻቸውን የሥነ ልቦና መጠገን ላይ ማተኮር እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

ከደብተር፣ ከመጻሕፍት እና ከሌሎች ቁሳቁሶች በተጨማሪ ተማሪዎች እና መምህራን የሥነ ልቦና ድጋፍ፣ ምግብ እና አልባሳት ያስፈልጋቸዋልም ብለዋል።