በኢትዮጵያ አካባቢ የሚበክሉ ትልልቅ ድርጅቶችን በራሱ ወጪ የሚከሰው ጠበቃ

ጠበቃ መልካሙ ኦጎ

የፎቶው ባለመብት, Melkamu

ስለ ቄራ ብክለት ለመናገር ቄራ መወለድ አይጠይቅም። በአካባቢው ውልብ ማለት በቂ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጭምር የመሰከረው ጉዳይ ነው።

ጠበቃ መልካሙ ኦጎ ቄራን ፍርድ ቤት ገትሮታል። አካባቢ በካዮችን እያሰደደ መክሰስ የጀመረው ግን ከቄራ አይደለም። ከተማረበት ዩኒቨርስቲ እንጂ።

አንድ ቀን ማታ ቤት ቁጭ ብሎ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ይመለከታል። ፕሮግራሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሴቶች ዶርም የሚወጣ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ያማረራቸው ነዋሪዎችን ስሞታ ያቀርባል።

ከቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ፋከልቲ ጀርባ በተለምዶ ጎመን ሰፈር የሚባለው ቦታ የሚኖሩ ምስኪን ነዋሪዎች፣ “ኧረ የመንግሥት ያለህ” ሲሉ ይታያሉ።

የዩኒቨርስቲው ፍሳሽ ቀጥታ ወደ ተጎራባቹ ሰፈር ነው የሚገባው። ተማሪዎች በየዓመቱ ተመርቀው ቢወጡም፣ የሽንት ቤቱ ፍሳሹ ወደ ሕዝብ መፍሰሱን አላቆመም።

ሰባት ዓመት የሽንት ቤት ፍሻሹን ሲቀበል የነበረው ሕዝብ የጠበቃ መልካሙን ስሜት ጎዳው።

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲጠየቅ የሰጠው ምላሽ ደግሞ መልካሙን ይበልጥ አስቆጣው።

ለሌሎች አርአያ ይሆናል የሚባል ተቋም ይህን ያህል ለሕዝቡ ሮሮ ግዴለሽ ሲሆን ማየቱ አመመው።

“እንዲያውም ፍርድ ቤት እገትረዋለሁ” ብሎ በድፍረት ተነሳ።

በነገታው 6 ኪሎ ጎመን ሰፈር ሄደ። ነዋሪዎቹን አነጋገረ፤ “እከስላችኋለሁ፤ ከእናንተ ቤሳ ቤስቲን አልፈልግም” አላቸው። ብዙም አላመኑትም። የእነርሱን አቤቱታ አዳምጦ የፍርድ ቤት አቤቱታ ጻፈ።

ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት ግን አንድ ሙከራ ማድረግ ነበረበት። ወደ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሄደ። እዚያ የጽሑፍ አቤቱታ እና ቅሬታ አስገባ።

እነሱም ግራ ተጋቡ፤ ጠበቃ በግለሰብ ደረጃ አቤቱታ አቅርቦ በግዙፍ ተቋም ላይ ክስ ይመሠርታል ብለው አልጠበቁም ይሆናል።

ባለሥልጣኑ ከጠበቃ መልካሙ ጋር በመሆን ጉዳዩን አጥብቀው ያዙት። ባለሥልጣኑ ባለሙያዎችን ወደ አካባቢው አሰማራ።

ፍርደ ቤት ሊቆም እንደሆነ ያወቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም እርምጃ ወሰደና ችግሩ ተፈታ።

ከዚያ በኋላ መልካሙ ወደዚያው ሰፈር ሄዶ ነዋሪዎችን “እንዴት ነው?” አላቸው። “አሁንስ ችግር አለ?”

አመሰገኑት፤ ተባረክ አሉት። “በቃ ብዙዎቹ አለኝታ እንዳገኙ ነው የተሰማቸው” ይላል መልካሙ።

ጠበቃ መልካሙ ኦጎ

የፎቶው ባለመብት, melkamu

የምስሉ መግለጫ, ጠበቃ መልካሙ ኦጎ

አንድ ግለሰብ ቄራን ፍርድ ቤት ማቆም ይችላል?

ከቄራ መልከ ብዙ ብክለት ነው የሚያወጣው። ብዙ ሕዝብ ሽታውን ነው የሚያውቀው። ነገር ግን ውሃው ይበከላል፤ የአካባቢው አፈርም ይበከላል።

መልካሙ መረጃ አሰባስቦ መጀመሪያ ወደ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በማምራት አቤቱታ አቀረበ።

ባለሥልጣኑ በቄራ ላይ ብዙ ማስጠንቀቂያ ጽፏል። ብክለቱ እንዲቆም ጥሯል፤ ግሯል። ባለሥልጣኑ ያልወሰደው እርምጃ አንድ ብቻ ነው። ቄራ ሥራውን አቁሞ እንዲታሸግ ማድረግ።

ይህን ማድረግ ቀላል ነው እንዴ?

“አዎና! ብክለቱን ካላቆመ ሥራ ማቆም ነው ያለበት፤ መታሸግ ካለበትም መታሸግ አለበት፣ ካልሆነም እንደ አማራጭ ከከተማ መሀል እንዲነሳ መደረግ አለበት” ይላል መልካሙ ፈርጠም ብሎ።

ስለዚህ መልካሙ ለባለሥልጣኑ በድጋሚ ቄራ ላይ ይህን እርምጃ እንዲወስድ አቤቱታ አቀረበ።

“...እርምጃ መውሰድ ይችላል፤ በአዋጅ የተሰጠ ሥልጣን ነው።”

ማንም ሊገምታቸው በሚችላቸው ምክንያቶች ግን እርምጃው አልተወሰደም።

መልካሙ በዚህ ጊዜ “መቼስ ምን ይደረጋል” ብሎ ፋይሉን አልቆለፈበትም።

ዶሴውን አደራጅቶ ልደታ ፍርድ ቤት ሄዶ የክስ መዝገብ አስከፈተ።

ከሳሽ፡ መልካሙ ኦጎ፤

ተከሳሽ፡ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት

ይህ ነገር ዳኞችን ግራ አጋባ።

መልካሙ ማን ነው? የቄራ ነዋሪዎች ተወካይ ነው? አይደለም።

በቄራ ምክንያት ጉዳት ደርሶበታል? አልደረሰበትም።

ማንን ወክሎ ነው ታዲያ የሚከራከረው? ኅብረተሰቡን።

ኅብረተሰቡ ወክለኝ ብሎታል? አላለውም።

በመኖሪያ ሰፈር አቅራቢያ የሚገኘው የቁም ከብት መገበያያ

የፎቶው ባለመብት, MELKAMU

የምስሉ መግለጫ, በመኖሪያ ሰፈር አቅራቢያ የሚገኘው የቁም ከብት መገበያያ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ነገር ፍርድ ቤቱን ብዙ አወዛገበ። ምክንያቱም ግለሰብ ተቋምን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል በራሱ ተነሳሽነት ሲከስ በኢትዮጵያ ብዙም ስላልተለመደ።

“ይህ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ያልተለመደ ክርክር ስለሆነ ብዙ አወዛግቦናል” ይላል መልካሙ።

ይህ የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ክርክር (Public Interest Litigation) በተቀረው ዓለም የተለመደ ነው።

መልካሙ ፈተና ገጠመው። የተከሳሽ ጠበቆች አጣደፉት።

“ጠበቃ መልካሙ ክስ በመሠረተበት ጉዳይ ላይ ያለው አግባብነት (Vested interest) በግልጽ ይቀመጥልን” አሉ።

ይህ ምን ማለት እንደሆነ መልካሙ በአጭሩ ሲያብራራ እንዲህ ይላል።

አንድ ሰው ክርክር በሚያደርግበት ጉዳይ ላይ መብት እና ጥቅም ያለው መሆኑን ማስረዳት አለበት። በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በጉዳዩ ላይ መብቱ የማይነካ ከሆነ ክርክሩን ማቅረብ አይችልም።

ታዲያ መልካሙ በቄራ ምክንያት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መብቱ ተነክቷል? አልተነካም።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ተከራከርልን ብሎ ወክሎታል? አልወከለውም።

በቄራ የአየር ብክለት ሳምባው ተጎድቷል? አልተጎዳም።

ታዲያ እንዴት ክርክሩ ይቀጥል?

ይህ ጉዳይ ብዙ አወዛገበ።

“እኔ እንደማንም ሰው በቄራ በኩል ሳልፍ ሸቶኝ ያውቅ እንደሁ እንጂ የቄራ ልጅም አይደለሁም” ይላል።

ዞሮ ዞሮ ቄራዎች ድርጅት የራሱን መከራከርያ ይዞ ቀረበ። ብክለቱን ለማስቀረት ብዙ ርቀት እንደሄደ አስረዳ።

መልካሙ ግን ብክለቱ ካልቆመ መታሸግ አለበት ብሎ ሽንጡን ገትሮ ተከራከረ።

እነሆ ብዙ ዳኞች የተፈራረቁበት ክስ አሁን ሁለት ዓመት አልፎታል። ሄዶ ሄዶ ሰበር ደርሷል። ሰበር የሚወስነው ውሳኔ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

“ሰበር የሚወስነው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ታሪካዊ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ውሳኔው ታች ላሉት ፍርድ ቤቶችም ሆነ ወደፊት ለሚመጣ ክስ መሠረት የሚጥል።”

ከራስ ኪስ ገንዘብ እያወጡ መሟገት ያዋጣል?

በሌሎች አገሮች ልምድ ግለሰብ ለሕዝብ ጥቅም ብሎ ሲከራከር የሚበረታታ ስለሆነ ወጪውን ከኪስ እንዲያወጣ አይገደድም።

በጎ መንፈስ ይዘው የሚነሱ (Public spirited citizens) ይበረታታሉ። ስለዚህ ወጪያቸው በተቋማት ይሸፈናል።

መልካሙ ግን ከኪሱ ነው የሚሸፍነው። ባልደረቦቹም በበጎ ፍቃድ ያግዙታል።

በዚህ መንገድ ብዙ ርቀት ሄዷል።

አንድ ሁለቱን ለመጥቀስ ያህል በሐዋሳ ትልቁን ቆሻሻ መድፊያ ለማዘጋት ጫፍ ደርሷል።

በተለምዶ ቆሼ የሚባለው ቦታ የከተማው ቆሻሻ በሙሉ እዚያ ይደፋል። ለነዋሪዎች ብክለት ሆኖባቸው ታመሙ።

እነ መልካሙ መረጃ አሰባስበው ክስ አደራጅተው ተነሱ።

ለክልሉ አካባቢ ጥበቃ አቤቱታ አቀረቡ። ምላሽ አላገኙም። ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወሰዱት። ከእልህ አስጨራሽ ክርክር በኋላ ታሪካዊ ውሳኔ ተሰወነ።

ፍርድ ቤቱም ክርክር በተነሳበት ቦታ ላይ ቆሻሻ እንዳይጣል፣ አካባቢው ጸድቶ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዲመለስ በማለት የፍትሐብሔር ክርክር መብታቸውን በመጠበቅ ውሳኔ ሰጥቷል።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ መልካሙ እና ባልደረቦቹ አሁን የአፈጻጸም ፋይል ከፍተው እየተከታተሉ ነው።

ከዚህ ሌላ በየካ አባዶ ኮንዶሚንየም ግቢ የነዋሪዎችን ፍሳሽ በሙሉ ይዞ የሚወጣ ትቦ ነበር። በአግባቡ አልተገነባም። አካባቢን እየበከለ ነበር። ይህ ፍሳሸ ሄዶ ጣፎ ወንዝ ይገባል። በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ሰውነታቸውን ይታጠቡበታል። ልብስ ያጸዱበታል።

“ለበርካታ ጊዜ ሕዝቡ አልቅሷል። ማንም አልሰማም። እኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወሰድነው። ፍርድ ቤት ለእኛ ወስኖ የአፈጻጸም ፋይል ከፈትን። ቦታው አሁን ከብክለት ነጻ መደረጉን አረጋግጠናል። ሕዝቡም እፎይ ብሏል።”

ጠበቃ መልካሙ ኦጎ ችሎት ላይ

የፎቶው ባለመብት, melkamu

የምስሉ መግለጫ, ጠበቃ መልካሙ ኦጎ ችሎት ላይ

ከዚህ ሌላ እነ መላኩ የሸጎሌ የቁም እንሰሳት ገበያ ማዕከል ላይ ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ክስ አቅርበው ነበር።

ፍርድ ቤት ወስኖላቸዋል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ መንደር 8 በሚባለው አካባቢ የአዲስ አበባ ትልቁ የቁም እንሰሳ ገበያ ይገኛል። ይህ ማዕከል ከመኖሪያ ቤቶች ያለው ርቀት ሦስት ሜትር ብቻ ነው።

ለቁም እንስሳት መሸጫ የሚሆን የቦታ ስፋት 20,000 ሜትር ካሬ መሆን ይገባዋል። በሥራ ላይ ያለው የገበያ ማዕከል ስፋት ግን 5,000 ሜትር ካሬ ብቻ ነው።

ይህ የገበያ ማዕከል መልከ ብዙ ብክለቶች በነዋሪዎች ሲያደርስ ቆይቷል። ነዋሪዎች ብሶታቸው ሲያሰሙ ነው የኖሩት።

እነ መልካሙ በዚህ ጉዳይ ላይ ክስ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉለሌ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ካቀረቡ ሁለት ዓመታት አልፏል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ጉዳዩ ሲታይ ቆይቶ ነበር።

ፍርድ ቤት በአስቸኳይ ማዕከሉ ማስተካከያ እንዲያደርግ ቢያዝም መሻሻል አልታየም። ገለልተኛ አካል ተቋቁሞም ለፍርድ ቤት እንዳረጋገጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ አልተፈጸመም።

ይህን ለፍርድ ቤት አቀረቡ።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም. ባስቻለው ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል።

ሕዝብ ደኅንነቱ በተጠበቀ አካባቢ የመኖር መብቱ ሊከበር ይገባል አለ። በመሆኑም ትልቁ የቁም እንሰሳት ገበያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲዘጋ ወሰነ።

የአዲስ አበባ ፖሊስም በአስቸኳይ ይህን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

የሕዝብን እንባ ከማበስ ሌላ ምን እርካታ አለ?

“እኔ በመሠረቱ ከአሁን በኋላ ይህን ሥራ ማቆም የምችልም አይመስለኝም። ራሴን እንደ ተቋም ነው የማየው። ውጤቱን ማየት ስጀምር ወደ ኋላ መመለስ አቃተኝ። እርካታው ከሁሉም ይበልጣል” ይላል መላኩ።

አሁን መልካሙ ጠበቃ ባልደረቦቹም እያገዙት ደንበኛ ተቋም እየቆመ ነው። ብቻውን ሲቆም ነበር። አሁን “ቁም ለአካባቢህ” የሚል ተቋም መስርቷል።

ገና ከጅምሩ ሰው እየጎረፈ ነው።

በየአካባቢው በብክለት መኖር የተሳነው፤ ለዘመናት ስቃዩን ያየ፣ በየመሥሪያ ቤቱ ለዘመናት ሮሮ አሰምቶ ምላሽ ያጣ፣ አሁን የእሱን ቢሮ እያንኳኳ ነው።

“በብክለት ጤናቸው የታወኩ ሰዎች ቢሮ መጥተው ያለቅሳሉ” ይላል።

“የእነዚህ ሰዎች እንባ ማበስ ከቻልኩ ከዚህ በላይ ምን እርካታ አለ?”