ኤለን መስክ ለትዊተር አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሾመ

ሊንዳ ያካሪኖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤለን መስክ ለትዊተር አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ መሾሙ ተገለጸ።

የተሾመችው የቀድሞው የኤንቢሲ ዩኒቨርሳል የማስታወቂያ ክፍል ኃላፊት ሊንዳ ያካሪኖ ናት።

ገቢ ለማግኘት እየታገለ ባለው ትዊተር የንግድ እንቅስቃሴን የምትቆጣጠር ይሆናል።

ትዊተርን ከስድስት ወራት በፊት መምራት የጀመረው ኤለን በዋና ኃላፊነት እና በዋና የቴክኖሎጂ ኃላፊነት ቦታው የሚቀጥል ይሆናል።

አምና ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር የገዛው ኤለን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሾመ ከቀናት በፊት ሲገልጽ ነበር።

ማንነቷን ይፋ ካደረገ በኋላ “ከሊንዳ ጋር ትዊተርን ሁሉም ነገር ወደሚከናወንበት መተግበሪያ እስክናደርሰው ጓጉቻለሁ” ብሏል።

ትዊተርን በሌላ ሰው ኃላፊነት ሥር አድርጎ ሌሎች ንግዶቹ ላይ እንዲያተኩር ጫና እንዳደረበትም ገልጿል።

ከቴክኖሎጂ ተቋሞች መካከል በሴት የሚመሩት ከ10% በታች ናቸው። በአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሠራችው ሊንዳ ከጥቂቶቹ አንዷ ሆናለች።

የጣልያናዊ አሜሪካዊ ውህድ ቤተሰብ ስትሆን አባቷ ፖሊስ እናቷ ደግሞ ኮሌጅ ያልገቡ ናቸው።

ሊንዳ የተመረቀችው ከፔን ስቴት ዩኒቨርስቲ ሲሆን ለ15 ዓመታት በራሷ ንግድ ላይ ቆይታ ኤንቢሲ ዩኒቨርሳልን ተቀላቅላለች።

2 ሺህ ሰዎችን በመራችበት በዚህ መሥሪያ ቤት የበይነ መረብ ቀጥታ ስርጭት እንዲጀመርም አድርጋለች።

ከአፕል ኒውስ፣ ስናፕቻት እና ዩቲዩብ ጋር ትስስር አላት።

የ9 እና የ13 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች እናት ናት።

የሙያ ሕይወቷን በቅርበት ስትከታተል የነበረችው የቢዝነስ ዴይሊ ጋዜጠኛ ክሌር አቲክሰን እንደምትለው፣ ሊንዳ ከማስታወቂያ ዘርፍ መምጣቷ ትዊተርን ለማሳደግ ይረዳል።

“ትዊተር ገንዘብ ማግኘት ከፈለገ ሊንዳ ትክክለኛዋ ምርጫ ናት” ብላለች።

ዋል ትስሪት ጆርናል እአአ በ2012 ባወጣው ዘገባ ሊንዳ ‘ቬልቬት ሀመር’ በሚል ቅጽል ስም እንደምትጠራ ገልጿል።

ትዊተር ገንዘብ እያጣ እንዲሁም ሐሰተኛ ዜና እና የጥላቻ ንግግር ስርጭትን በተመለከተ ከፍተኛ ትችት ውስጥ በወደቀበት ጊዜ ነው ወደ አመራር የመጣችው።

ኤለን ከማስታቂያ ይልቅ ይዘት ላይ ማተኮር እንደሚፈልግ ከዚህ ቀደም ገልጿል።

ገጹን ለገንዘብ ልውውጥ፣ ለስልክ ጥሪ፣ ለሚሥጥራዊ መልዕክት ልውውጥ አውሎ የማስፋፋት ዕቅድም አለው።

ይህን ዕቅዱን X ሲል ይጠራዋል።

የጥላቻ ንግግርን የሚያስወግዱን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ማባረሩ ሲያወዛግብ ቆይቷል።

ስጋት የገባቸው ተቋሞች ገጹ ላይ ማስተዋወቅ ስላቆሙ የሚያገኘው ገቢ መቀነሱን ኤለን ተናግሯል።

ሊንዳ ኤለን የተቋማትን ማስታወቂያ ለመመለስ ምን ማድረግ እንደሚችል ባለፈው ወር የተካሄደ የማስታወቂያ ውይይት ላይ ጠይቃው ነበር።

ሊንዳ በፖለቲካው ወደ ወግ አጥባቂ ቀረብ ማለቷ በሹመቷ ደስተኛ ያላደረጋቸው አሉ።

በቀኝ ዘመሞች ትችት የቀረበበት ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ መሥራቷ አንዱ ምክንያት ነው።

በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመን በዋይት ሀውስ የአካል ብቃት ዘርፍ መሳተፏም ይነሳል።

ኤለን ለስፔስ ኤክስ እና ተስላ ተቋሞቹ ሴቶችን በአመራር በመሾም ሲታወቅ፣ ከሠራተኞቹ ብዙ በመጠየቅና ለመገመት አስቸጋሪ በመሆን ይገለጻል።