በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በከባድ ሙቀት ምክንያት በቤታቸው እንዲቆዩ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

በውሃ ፋውንቴን አካባቢ ቆማ ራሷን የምታቀዘቅዝ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአገሪቱ ግማሽ ያህሉ በሙቀት ማዕበል እየተመታ በመምጣቱ በመላው አሜሪካ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው።

ስለሙቀቱ ማሳሰቢያ እና ምክር የሚሰጠው ብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት በመካከለኛው ምዕራብ፣ በደቡብ ምሥራቅ እና በሰሜን ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች 168 ሚሊዮን አሜሪካውያን ተጠቂ ናቸው ብሏል።

የኒውዮርክ አስተዳዳሪ ካቲ ሆቹል የግዛቲቱ ነዋሪዎች ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ጎረቤቶቻቸውን እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

እንደ አስተዳዳሪው ከሆነ በግዛቲቱ ውስጥ ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ወይንም ሙቀት፣ ቀዳሚው የሞት መንስኤ ነው።

ከባድ አውሎ ነፋስ በቀጠናው የሚነፍስ ከሆነ ከአንድ ቀን በኋላ ሐሙስ የአየር ሁኔታው እንደሚቀዘቅዝ ተነግሯል።

"ይህ ከፍተኛ ሙቀት አደገኛ እና ለሕይወት አስጊ ሊሆን ይችላል" ሲል የኒውዮርክ የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር በኤክስ ገፁ ላይ ለጥፏል።

አክሎም ሰዎች "በተቻለ መጠን አየር ማቀዝቀዣ ባለባቸው ስፍራዎች በቤት ውስጥ መቆየት አለባቸው" ሲል መክሯል።

ጥድፊያ በሚበዛበት ማክሰኞ ማለዳ በኒውዮርክ ከተማ በተፈጠረ የመብራት መቆራረጥ በርካታ የምድር ውስጥ ባቡር መስመሮችን ቆመዋል።

ይህንን ተከትሎም ባለስልጣናቱ በሙቀት ምክንያት መሆኑን እያጣራን ነው ብለዋል።

የምድር ውስጥ ባቡር አሽከርካሪ ናታሊ ሄንሪ "በቂ አየር መንቀሳቀስ የሚችል ቢሆንም በበርካታ ሰዎች ጥቅጥቅ ብሎ ነበር" ስትል ተናግራለች።

በኒውዮርክ ግዛት ውስጥ የመዋኛ ሰዓት የተራዘመ ሲሆን ሰዎች ከሙቀት ራሳቸውን እንዲከላከሉ ለመርዳት የማቀዝቀዣ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል።

የኒውዮርክ የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር የመጀመሪያ መረጃ እንደሚያሳየው፣ የከተማዋ ላጋርዲያ አውሮፕላን ማረፊያ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ 37.7 ዲግሪ ሴልሺየስ ይሞቅ የነበረ ሲሆን በሐምሌ ወር ከፍተኛ የሙቀት መጠን ሆኖ ተመዝግቧል።

ነገር ግን ይህ እአአ በሐምሌ 3/1966 በላጋርዲያ አውሮፕላን ማረፊያ ከተመዘገበው የምንጊዜም ከፍተኛ የ107° ፋራናይት ያነሰ ነው።

እሁድ ዕለት፣ በፍሎሪዳ ሰንሻይን ግዛት ውስጥ የምትገኘው ታምፓ 100 ዲግሪ ፋራናይት ሙቀት የተመዘገበ ተመዝግቧል።

በግዛቲቱ እአአ በ2020 99 ዲግሪ ፋራናይት ሙቀት ተመዝግቦ ነበር።