የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አገራት እርስበርስ መካሰስ ይችላሉ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት፣ የምድራችን ሙቀት ጨማሪ ጋዞች ልቀትን ጨምሮ፣ አገራት እርስ በርስ እንዲካሰሱ መንገዱን ጠርጓል።
በሄግ፣ ኔዘርላንድስ የሚገኘው የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ዳኛ ረቡዕ እንደተናገሩት የትኛውን የአየር ንብረት ለውጥ አካል ማን እንዳስከተለው ለመረዳት ከባድ ሊሆን ይችላል።
ፍርዱ አስገዳጅ ባይሆንም የሕግ ባለሙያዎች ሰፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ለሆኑ እና ችግሩን ለመቅረፍ ዓለም አቀፋዊ መሻሻል ባለማግኘታቸው ብስጭት ተሰምቷቸው ፍርድ ቤት ለቀረቡ አገራት ግን እንደ ድል ይቆጠራል።

የፎቶው ባለመብት, Dorka Bauer
በዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ታይቶ የማያውቀው ይህ ጉዳይ በ2019 ሃሳቡን ያመነጨው ከዝቅተኛው የፓሲፊክ ደሴቶች የመጡ ወጣት የሕግ ተማሪዎች ቡድን በአየር ንብረት ለውጥ ግንባር ነው።
ከእነዚያ ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው የቶንጋው ሲኢሲዋ ቬይኩን ውሳኔውን ለመስማት ሄግ ውስጥ ነበር።
"ቃላት አጠሩኝ። ይህ በጣም አስደሳች ነው። ብዙ ስሜቶች በእኛ ውስጥ እየተመላለሱ ነው። ይህ በኩራት ወደ ቤታችን ወደ ማኅበረሰባችን የምንወስደው ድል ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በፓስፊክ ደሴት ቫኑዋቱ ነዋሪ የሆነችው ፍሎራ ቫኖ፣ "ዛሬ ማታ በቀላሉ እተኛለሁ። ፍርድ ቤቱ የኖርንበትን ነገር ተገንዝቧል፤ ስቃያችንን፣ ፅናታችንን እና የወደፊት መብታችንን" ስትል አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለከፋ የአየር ሁኔታ በጣም የተጋለጠች ናት ስትል ተናግራለች።
"ይህ ድል ለእኛ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የአየር ንብረት ተጋላጭ ማኅበረሰብ እንዲሰማ የሚያደረግ ትግል ነው።"
አይሲጄ የዓለም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን ዓለም አቀፋዊ ስልጣን አለው።
ጠበቆቹ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሀሳቡ ከአይሲጄ ውጭ ያሉ ብሔራዊ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ።
የዘመቻ አድራጊዎች እና የአየር ንብረት ጠበቆች አስደናቂው ውሳኔ አሁን በታሪክ እጅግ በጣም ብዙ ቅሪተ አካላትን ያቃጠሉ እና ለዓለም ሙቀት መጨመር ተጠያቂ ከሆኑ አገራት ለካሳ መንገድ ይከፍታል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ ።
የበለጸጉ አገሮች እያደገ የመጣውን ችግር ለመቅረፍ የገቡትን ቃል መፈጸም ተስኗቸዋል በማለት ብዙ ድሃ አገሮች ጉዳዩን በብስጭት ደግፈውታል።
ነገር ግን ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ያደጉት አገራት የአየር ንብረት ስምምነቶች፣ የ2015 ታሪካዊውን የተባበሩት መንግሥታት የፓሪስ ስምምነትን ጨምሮ በቂ ናቸው ስለሆነም ምንም ተጨማሪ የሕግ ግዴታዎች ሊጣሉ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Dorka Bauer
ነገር ግን ረዑዕ ላይ ፍርድ ቤቱ ያንን ክርክር ውድቅ አድርጎታል።
ዳኛ ኢዋሳዋ ዩጂ በተጨማሪም አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ እጅግ በጣም ትልቅ ዕቅድ ካላዘጋጁ ይህ በፓሪስ ስምምነት ላይ የገቡትን ቃል መጣስ ይሆናል ብለዋል።
ሰፋ ያለ ዓለም አቀፍ ሕግም ተግባራዊ ይሆናል። ይህም ማለት የፓሪሱን ስምምነት ያልፈረሙ፣ ወይም እንደ አሜሪካ መውጣት የሚፈልጉ አገራት አሁንም የአየር ንብረት ስርዓቱን ጨምሮ አካባቢን መጠበቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የፍርድ ቤቱ አስተያየት ምክራዊ ነው፤ ነገር ግን ዩናይትድ ኪንግደም ባለፈው ዓመት የቻጎስ ደሴቶችን ለሞሪሸስ ለማስረከብ የተስማማችበትን ጊዜ ጨምሮ የቀደሙት የአይሲጄ ውሳኔዎች በመንግሥታት ተግባራዊ ሆነዋል።
በዓለም አቀፍ የአካባቢ ሕግ ማዕከል (ሲአይኤል) ከፍተኛ ጠበቃ ጆይ ቻውዱሪ "ውሳኔው ወሳኝ ሕጋዊ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
"በዛሬው ሥልጣን ባለው ታሪካዊ ውሳኔ፣ ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እንደተለመደው የንግድ ሥራውን አቋርጦ ታሪካዊ ማረጋገጫ ሰጥቷል፤ በአየር ንብረት ውድመት ምክንያት የሚሠቃዩት የአየር ንብረት ጉዳትን ጨምሮ የካሳ ክፍያን የማግኘት መብት አላቸው" ሲሉ አክለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ፣ የኮመንዌልዝ እና ልማት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ዝርዝር አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ውሳኔውን ለመመልከት "ጊዜ እየወሰዱ" መሆኑን ቢገልጹም "የአየር ንብረት ለውጥን መዋጋት አሁንም ወደፊትም አስቸኳይ የዩናይትድ ኪንግደም እና ዓለም አቀፋዊ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። አቋማችን ይህ በተሻለ ሁኔታ የሚተገበረው ባሉት የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ስምምነቶች እና ዘዴዎች ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፍርድ ቤቱ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለደረሱ ጉዳዮች ካሳ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ወስኗል።
የአንድን አገር ክፍል መመለስ በማይቻልበት ጊዜ መንግሥት ካሳ ሊጠይቅ እንደሚችልም አክሏል።
ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው መሆኑ ከተረጋገጠ ለተለየ ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተት ሊሆን ይችላል ነገርግን ዳኛው ይህ በየጉዳይ ሊወሰን ይገባል ብለዋል።
ቫኑዋቱን እና ማርሻል ደሴቶችን በመወከል በዶውቲ ስትሪት ቻምበርስ ጠበቃ ጄኒፈር ሮቢንሰን "ይህ ለአየር ንብረት ተጋላጭ ሀገራት ትልቅ ድል ነው። ይህንን ጉዳይ የመራው እና የአየር ንብረት ተሟጋቾችን ገጽታ ለመቀየር ለቫኑዋቱ ትልቅ ድል ነው።" ብለዋል።
የትኛውም የይገባኛል ጥያቄ ከተሳካ አንድ አገር ለጉዳት ምን ያህል መክፈል እንዳለበት ግልጽ አይደለም።
ነገር ግን በኔቸር የታተመው ያለፈው ትንታኔ ከ2000 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ 2.8 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል፤ ይህ ማለት በሰዓት 16 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ነው።
በታህሳስ ወር በተካሄደው የማስረጃ ማሰማት ወቅት፣ ፍርድ ቤቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በባህር ከፍታ የተነሳ የተፈናቀሉ በደርዘን የሚቆጠሩ የፓሲፊክ ደሴት ነዋሪዎችን ምስክርነት ሰምቷል።
የማርሻል ደሴቶች ደሴታቸው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመላመድ የሚወጣው ወጪ 9 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጄኒፈር ሮቢንሰን "ይህ የማርሻል ደሴቶች 9 ቢሊዮን ዶላር የላትም። የአየር ንብረት ለውጥ እነሱ ያላስከተሉት ችግር ነው፣ ነገር ግን ዋና ከተማቸውን ለማዛወር እንዲያስቡ ይገደዳሉ" ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ከካሳ ክፍያ በተጨማሪ አገራት በግዛታቸው ውስጥ ለሚሰሩ ኩባንያዎች የአየር ንብረት ተፅእኖ ተጠያቂ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
በተለይ ለነዳጅ ኢንዱስትሪ ድጎማ ማድረግ ወይም አዲስ የነዳጅ እና ጋዝ ፈቃድ ማጽደቅ የአንድን አገር ግዴታ መጣስ ሊሆን ይችላል ብሏል።















