በውሃ እጥረት ምክንያት እየተወዛገቡ ያሉት አሜሪካ እና ሜክሲኮ

በሰሜን ምሥራቅ የሚገኘው ቶሮንቶ ሐይቅ
የምስሉ መግለጫ, በሰሜን ምሥራቅ የሚገኘው ቶሮንቶ ሐይቅ የያዘው የውሃ መጠን እጅግ በጣም የቀነሰ ነው

ለሰላሳ ተከታታይ ወር ዝናብ ባለመዝነቡ በሜክሲኮ ሰሜናዊ የቺዋዋ ግዛት የሳን ፍራንሲስኮ ዴ ኮንቾስ ከተማ ነዋሪዎች ፈጣሪ ጣልቃ በመግባት ዝናብ እንዲያዘንብላቸው ለመለመን ተሰባስበዋል።

ለግዛቱ እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነው እና በቶሮንቶ ሐይቅ ዳርቻ አንድ ቄስ የአካባቢውን ገበሬዎች ሰብስቦ ለፀሎት ይወስዳቸዋል። እየረገጡት የሚራመዱት ድንጋያማ መሬት በአንድ ወቅት እንደ አሁኑ ውሃው ከመሸሹ በፊት የሐይቁ አካል ነበር።

አንገታቸውን ደፍተው ፈጣሪያቸውን ከሚለማመኑት መካከል ለ35 ዓመታት ለግዛቱ የውሃ ባለሥልጣን ላቦኪላን በፈቃደኝነት ሲሠራ የኖረው ራፋኤል ቤታንስ ይገኝበታል።

ወደ ደረቅ ነጭ ቋጥኞች እየጠቆመ "ይህ ሁሉ በውሃ መሸፈን አለበት" ይላል። "ግድቡ የሞላው እና ለመጨረሻ ጊዜ ትንሽ ተርፎ የፈሰሰው (እአአ) በ2017 ነበር" ሲሉ ቤታን ያስታውሳል።

"ከዚያ ጀምሮ፣ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ሄዷል። በአሁኑ ጊዜ ከከፍተኛ የውሃ ምልክት በታች 26.52 ሜትር ላይ እንገኛለን፤ ይህም ከመያዝ አቅሙ 14 በመቶ ያነሰ ነው።"

ራፋኤል ቤታንስ
የምስሉ መግለጫ, ራፋኤል ቤታንስ ላለፉት ስምንት ዓመታት በግድቡ ያለው የውሃ መጠን እየቀነሰ መጥቷል ይላል

የአካባቢው ማኅበረሰብ ዝናብ እንዲዘንብለት ፈጣሪውን ቢለምን ምንም አያስደንቅም።

አሁንም ጥቂቶች 42 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚሞቀው አካበባቢ ጠብታ ዝናብ አግኝተው መቀዝቀዝ ያስባሉ።

ከአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ጋር የረዥም ጊዜ የቆየ አለመግባባት ውስጥ የምትገኘው ሜክሲኮ በዚህ ምክንያት ወደ ከፋ ውጥረት ውስጥ እየገባች ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እንደ አውሮፓውያኑ በ1944 የውሃ መጋራት ስምምነት መሠረት ሜክሲኮ በዓመት 430 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ከሪዮ ግራንዴ ወደ አሜሪካ መልቀቅ አለባት።

ውሃው በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል የውሃ መጋራትን የሚቆጣጠራቸው በዓለም አቀፉ የድንበር እና ውሃ ኮሚሽን ባለቤትነት ወደተያዙ እና ወደ ግድቦች በማከፋፈያ ቱቦዎች በኩል ይላካል።

በምላሹ አሜሪካ የሜክሲኮ የድንበር ከተሞችን ቲዋና እና ሜክሲካሊ ከኮሎራዶ ወንዝ የራሷን ድርሻ፣ በዓመት 1.85 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ ውሃ ትለቃለች።

ሜክሲኮ የውሃ ውዝፍ ዕዳ አለባት። በአብዛኛው በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠበቅባትን የውሃ መጠን ለመልቀቅ አዳግቷት ቆይታለች።

በቴክሳስ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሕግ አውጪዎች ያደረጉትን ግፊትን ተከትሎ፣ የትራምፕ አስተዳደር ሜክሲኮን 81 ዓመት በሞላው ውል መሠረት የሚጠበቅባትን ግዴታ እስካልወጣች ድረስ ከኮሎራዶ ወንዝ ውሃ ልትከለከል እንደምትችል አስጠንቅቋል።

በሚያዝያ ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ሜክሲኮን "ሰርቃለች" ሲሉ ወንጅለዋል።

ሜክሲኮ ለቴክሳስ ያለባትን ዕዳ እስክትልክ ድረስ "ታሪፍ ምናልባትም ማዕቀብ" ለመጣል አስፈራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ማስፈራራታቸውን ይቀጥሉ እንጂ እንዲህ ዓይነት እርምጃ ሊወሰድበት በሚችልበት ጊዜ ምንም ዓይነት ቀነ ገደብ አልሰጡም።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም፣ በውሉመሠረት መፈጸም የሚገባቸውን አለማከናወናቸውን አምነው፤ ነገር ግን በእርግጠኝነት መፍትሄ ያሉትን ከመናገር ታቅበዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሜክሲኮ 75 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን በድንበር አካባቢ በሚገኘው በአሚስታድ የጋራ ግድብ በኩል ለአሜሪካ አስተላልፋለች። ነገር ግን ይህ ሜክሲኮ ካለባት ከ1.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ውስጥ ትንሹ ነው።

በዚህ የድንበር ተሻጋሪ ውሃ መጋራት የተነሳ በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ውጥረት ተከስቷል።

እአአ በመስከረም 2020 ገበሬዎች ውሃው እንዳይሄድ ለማስቆም ሲሞክሩ በላ ቦኪላ አካባቢ የሚገኙ የብሔራዊ ዘብ አባላት ጋር በተፈጠረ ግጭት ሁለት የሜክሲኮ ዜጎች ተገድለዋል።

በአስከፊው ድርቅ መካከል፣ በቺዋዋ የተስፋፋው አመለካከት "ከሌለው ነገር ላይ መውሰድ አይችሉም" የሚል መሆኑን ራፋኤል ቤታንስ ተናግረዋል።

ነገር ግን ሰብሎቹን ውሃ ለማጠጣት ይህ እንደማይረዳው ብራያን ጆናስ ይናገራል።

በቴክሳስ የሪዮ ግራንዴ ሸለቆ ገበሬ የሆነው ጆናስ ላለፉት ሦስት ዓመታት በቂ የመስኖ ውሃ ስለሌለው የእርሻውን ግማሹን ብቻ ነው መዝራት የቻለው።

"ከሜክሲኮ ጋር እየተፋጠጥን ነበር። ምክንያቱም እነሱ በስምምነቱ መሠረት የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ አይደለም" ሲል ተናግሯል።

የምንጠይቀው በስምምነቱ መሠረት የእኛ የሆነውን ብቻ ነው፣ ምንም ተጨማሪ ነገር የለም ሲል ያክላል።

ጆንስ እአአ በጥቅምት 2022 ግዛቱ ከበቂ በላይ ውሃ እንዳገኘ ያምናል፤ ነገር ግን "ምንም" ለአሜሪካ እንዳልለቀቁ በመጥቀስ ጎረቤቶቹን "ውሃ በመያዝ እና ሰብል በማምረት ከእኛ ጋር ለመወዳደር" ይፈልጋሉ ሲል ይወነጅላቸዋል።

በዛፎች መካከል የተኛ ውሃ

በሜክሲኮ በኩል ያሉ ገበሬዎች ደግሞ ስምምነቱን በተለየ መንገድ ነው የሚያዩት።

ሜክሲኮ የራሷን ፍላጎት ካረካች በኋላ ወደ አሜሪካዋ ግዛት መላክ አንደምትችል በመግለጽ የቺዋዋ ቀጣይነት ያለው ድርቅ ምንም ትርፍ ውሃ የለም ማለት መሆኑን በመጥቀስ ይከራከራሉ።

ከውሃ እጥረቱ ባሻገር በግብርና ውጤታማነት ላይም ክርክሮች አሉ።

የዎልነት ዛፎች እና አልፋልፋ በቺዋዋ ሪዮ ኮንቾስ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙት ዋና ሰብሎች መካከል ሁለቱ ናቸው።

ሁለቱም ብዙ ውሃ ማጠጣት የሚያስፈልጋቸው ዛፎች ናቸው።

የዋልነትት ዛፎች በቀን በአማካይ 250 ሊትር ውሃ ያስፈልጋቸዋል።

በተለምዶ የሜክሲኮ ገበሬዎች በመስኖ ውሃ በማጠጣት ማሳቸውን አጥለቅልቀዋል።

በሸለቆው ዙሪያ ሲነዱ የዋልነት ዛፎች በውሃ ኩሬ መካከል ቆመው ይታያሉ።

ከቴክሳስ የቀረበው ቅሬታ ግልጽ ነው። ይህ ሁኔታ ውሃ አባካኝ እና በቀላሉ የበለጠ ኃላፊነት በተሞላበት እና በዘላቂ የግብርና ዘዴዎች ሊወገድ የሚችል ነው።

የዋልነት አምራች ገበሬ የሆነው ሃይሜ ራሜሬዝ

ሃይሜ ራሚሬዝ በዎልነት ቁጥቋጦዎቹ ውስጥ ሲዘዋወር፣ የሳን ፍራንሲስኮ ዴ ኮንቾስ የቀድሞ ከንቲባ በዘመናዊ ውሃ የመርጨት ዘዴ እንዴት ውድ ሃብቱን ሳያባክን የዋልነት ዛፎቹ ዓመቱን ሙሉ ውሃ እንደሚያጠጣ ያሳያል።

"በመርጫዎቹ፣ እርሻውን ከማጥለቅለቅ 60 በመቶ ያነሰ እንጠቀማለን" ይላል።

በተጨማሪም ዛፎቹን በተደጋጋሚ ውሃ ማጠጣት ይችላሉ። ይህም በተለይ ሪዮ ኮንቾስ መጠኑ በሚቀንስበት ወቅት የአካባቢውን መስኖ ለመጠቀም ጠቃሚ ነው።

ራሚሬዝ ግን አንዳንድ ጎረቤቶቹ ኅሊና ቢስ እንዳልሆኑ ያምናል። እንደ የቀድሞ ከንቲባነቱ፣ መግባባት እንዲሰፍን ያሳስባል።

አንዳንዶች ውሃውን የመርጨት ዘዴን ለመጠቀም በሚያስፈልጋቸው ወጪ ምክንያት አልተቀበሉም ብሏል።

በሂደት በርካሽ እንደሚሠራ ለሌሎች ገበሬዎች ለማሳየት ሞክሯል፤ ይህም የኃይል እና የውሃ ወጪን ይቆጥባል።

ነገር ግን ራሚሬዝ በቴክሳስ ያሉ ገበሬዎች በቺዋዋ ውስጥ ያሉ አቻዎቻቸው የኅልውና ስጋት እያጋጠማቸው መሆኑን መረዳት አለባቸው ይላል።

"ይህ በረሃማ አካባቢ ነው፤ ዝናቡም አልዘነበም። ዝናቡ እንደገና ካልመጣ በሚቀጥለው ዓመት ምንም ዓይነት ግብርና አይኖርም። ያለውን ውሃ ሁሉ ለመጠጥነት መቆጠብ ይኖርበታል" ሲል አስጠንቅቋል።

በሰሜናዊ ሜክሲኮ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የ1944ቱ የውሃ መጋራት ስምምነት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ብቁ አይደለም ብለው ያምናሉ።

ራሚሬዝ ከስምንት አስርት ዓመታት በፊት ለነበረው ሁኔታ በቂ ሊሆን ይችላል ካለ በኋላ፣ ነገር ግን ከዘመኑ ጋር መላመድ ወይም የሕዝብ ቁጥር መጨመር ወይም የአየር ንብረት ለውጥ ውድመትን በትክክል ከግንዛቤ ማስገባት አልቻለም ሲል ይናገራል።

ድንበር ተሻግሮ የሚገኘው የቴክሳስ ገበሬ ብሪያን ጆንስ ግን ስምምነቱ ብዙ ጊዜ የተሻገረ እና አሁንም ሊከበር የሚገባው ነው ይላል።

"ይህ ውል የተፈረመው አያቴ በግብርና ላይ በነበረበት ወቅት ነው። በአያቴ፣ በአባቴ እና አሁን በእኔ ዘመን አለ" ይላል።

"አሁን ሜክሲኮ አለማክበሯን እያየን ነው። የመስኖ ውሃ ስለሌለኝ ግማሹን መሬት ብቻ መዝራት የምችል መሆኑ በጣም ያናድዳል።"

የትራምፕ ጠንከር ያለ አቋም ለአካባቢው አርሶ አደሮች ተስፋ ሰጥቷቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ድርቁ በቺዋዋ በግብርና ላይ ብቻ ጉዳት አላደረሰም።

የቶሮንቶ ሐይቅ በጣም እየቀነሰ መምጣት ያሳሰበው ቤታንስ የሸለቆው ዕይታ ይህን ያህል አስከፊ አልነበረም ይላል።

ቤታንስ የሐይቁን መቀነስ መጨመር በጥንቃቄ በመመዝገብ ባሳለፈበት ጊዜ ሁሉ እንደ አሁኑ የከፋ ድርቅ አጋጥሞት አያውቅም።

"ዝናብ እንዲዘንብ መጸለይ ብቻ ነው የቀረን" ይላል።