በቴክሳስ የገበያ ማዕከል በተፈጸመው የተኩስ ጥቃት ከሰለባዎቹ መካከል ሦስቱ ሕጻናት ናቸው

እያለቀሱ ያሉ ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት በደረሰው የተኩስ ጥቃት ከሰለባዎቹ መካከል ሦስቱ ሕጻናት መሆናቸው ተገለጸ።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት የሦስት ዓመት ህጻን ልጅ ከወላጆቹ ጋር፣ ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና አንድ ህንዳዊት ወጣት መሃንዲስ ሕይወታቸው ተቀጥፏል።

ጄምስ ቾ የተሰኘው ሕጻን ከወላጆቹ ቾ ክዪ ሶንግ እና ካንግ ሺ ያንግ ጋር ሕይወቱ እንዳለፈ ሪፖርቶች ወጥተዋል። በዚህ ጥቃት የሕጻኑ የስድስት ዓመት ወንድም ቢቆስልም ሕይወቱ ተርፏል።

ባለሥልጣናቱ የጥቃቱ ሰለባዎችን ከመለየት ጎን ለጎንም ጥቃቱ አድራሹ ከጽንፈኛ ቀኝ አክራሪ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንደነበረውም እየመረመሩ ይገኛሉ።

በዚህ ጥቃት በአጠቃላይ ስምንት ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን በርካታ ተጎጂዎችም በሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ይገኛል።

በቾ ቤተሰብ የተከፈተ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ጎ ፈንድሚ ገጽ መሰረት ቤተሰቡ አለን ፕሪሚየም አውትሌትስ በተሰኘው የመገበያያ ማዕከል የተገኙት የስድስት ዓመት ልጃቸው የተበረከተለትን የልደት ስጦታ ልብስ ለመቀየር እንደነበር አትቷል።

“በብርሃን፣ በፍቅር እና በደስታና በፈንጠዝያ መሞላት የነበረበት የከሰዓት ውሎ በአሳዛኝ የጅምላ ጭፍጨፋ ተተካ” ሲሉም የቤተሰቡ ወዳጆች በዚህ የገንዘብ ማሰባሰቡያ ገጽ ላይ ጽፈዋል።

በቴክሳስ የሚገኘው የኮሪያ ቆንስላ ባለሥልጣናት ለዳላስ ሞርኒንግ ኒውስ ጋዜጣ እንደተናገሩት የቾ ቤተሰብ የኮሪያ ዝርያ ያላቸው አሜሪካውያን ዜጎች መሆናቸውንና ዲፕሎማቶች ቤተሰቡንም እያናገሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የዚህ ጥቃት ሌላኛዎቹ ሰለባዎች የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሆኑት እህትማማቾቹ ዳንኤላ እና ሶፊያ ሜንዶዛ ናቸው። እናታቸው አይዳም በዚህ ጥቃት በከፋ ሁኔታ ተጎድታ በሆስፒታል ውስጥ እንደምትገኝ የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

የ27 ዓመቷ ህንዳዊቷ መሃንዲስ አይሽዋርያ ታቲኮንዳ እንዲሁም የ20 ዓመቱ የጥበቃ ሰራተኛ ክርስቲያን ላኮር በዚህ ጥቃት ተገድለዋል።

ሰኞ አመሻሽ ላይ የቴክሳስ ባለሥልጣናት የመጨረሻውን ሰለባ የ32 ዓመቱ ኤሊዮ ኩማና-ሪቫስ መሆኑን አሳውቀዋል።

በሰሜን ዳላስ ከተማ በደረሰው በዚህ ጥቃት ስድስቱ ወዲያውኑ በስፍራው ሕይወታቸው ሲያልፍ ሁለቱ ደግሞ በሆስፒታል መሞታቸው ተዘግቧል።

የ33 ዓመቱ ተጠርጣሪ ማውርሲዮ ጋርሲያ ፖሊስ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል።