ከሱዳን በመሸሽ ወደ መተማ የገቡ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቁጥር ከ12 ሺህ በላይ ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሱዳን ተፋፍሞ የቀጠለውን ጦርነት ሸሽተው ድንበር አቋርጠው በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) እንዳስታወቀው በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በድንበር በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ሲሆን ቁጥሩም እየጨመረ ነው።
ሦስት ሳምንት ባለፈው የሱዳን ጦርነት ምክንያት በመተማ በኩል እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ዜጎች ቁጥርም በአጠቃላይ ከ12 ሺህ በላይ መድረሱን ኦቻ ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሱዳን እና ኢትዮጵያ በሚዋሰኑበት ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ በኩል ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ አገሪቱ እየገቡ ካሉት መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ የሌሎች አገራት ዜጎችም እንደሚገኙበት የመንግሥታቱ ድርጅት መሥሪያ ቤት መረጃ ያሳያል።
ከሦስት ቀናት በፊት ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም. በመተማ በኩል 1 ሺህ 113 ተፈናቃዮች የገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ የሱዳን፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ የአሜሪካ፣ የሶሪያ፣ የጋና እና የሌሎችም አገራት ዜጎች ይገኙበታል።
በድንበር በኩል ከሚገቡት ስደተኞች መካከል መካከል በርካቶቹ የውጭ አገር ዜጎች ተገቢውን የኢትዮጵያ ቪዛ ካገኙ በኋላ የድንበር አካባቢውን ለቀው ወደ አገራቸው፣ ወይም ወደ ሌሎች መዳረሻዎች እየሄዱ ይገኛሉ ተብሏል።
ኦቻ እንዳለው የተወሰኑትም በኢትዮጵያ ለመቆየት የመረጡም አሉ። በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ አገራቸው እየተመለሱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎችም በድንበር አቋርጠው ከገቡ በኋላ ወደመጡባቸው ስፍራዎች እየተመለሱ ነው ብሏል።
ሆኖም ተመድ እንዳለው በድንበር ላይ አሁንም በርካታ ዜጎች ያሉ ሲሆን፣ አብዛኞቹም አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።
ኦቻ በድንበር አካባቢ ያሉ ተፈናቃዮችን መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማሟላት የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ እንዲለግስ ተጠይቋል። ቀጠናዊ የስደተኞች ምላሽ ዕቅድ የሆነውን 76.9 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ኢትዮጵያ እንድትሰጥ በተመድ ተጠይቃለች።
በድንበር በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱም የጤናን ጨምሮ መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ማሳደግ ሁኔታውን እንዳይባባስ ያደርጋል ብሏል።
ለተፈናቃዮቹ ምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የአስቸኳይ ጊዜ መጠለያ እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
ኦቻ በድንበር ከተማዋ መተማ የጤና አጋሮች ባደረጉት ፈጣን ግምገማ የጤና አገልግሎቶች ላይ ውስንነት መታየቱን ጠቅሶ፣ በአሁኑ ወቅት የጤና ተቋማቱ መሠረታዊ የሚባሉ እና የሕይወት አድን መድኃኒቶች እጥረት አለባቸው ብሏል።
አስፈላጊ የሚባሉ አስቸኳይ እርዳታዎችን ማጠናከር ሁኔታዎች እንዳይባባሱ እና በሽታዎችን ለመከላከል አስፈላጊ መሆናቸውን አሳስቧል።
በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተቀሰቀው ግጭት ሳቢያ ቢያንስ ስምንት ኢትዮጵያውያን እንደተገደሉ በአገሪቱ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሁለት ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር።
ለሦስት ሳምንታት ያህል በቀጠለው ከባድ ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ወደ 450 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ከ115 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት አገራት እንደተሰደዱም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የሚሊዮኖች ሕይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መካከል ሁለት ተፋላሚ ጄኔራሎች በባላንጣነት በካርቱም እና በሌሎችም ከተሞች ውስጥ ከባድ ውጊያ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ እና አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መሪ ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄሜቲ ጋር በመረረ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ናቸው።
ባለፉት ሳምንታት ሁለቱ ኃይሎች ለቀናት የሚቆዩ በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ላይ ደርሰው ያላከበሩት ሲሆን፣ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በሳዑዲ አረቢያ የፊት ለፊት ንግግር ሊያደርጉ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ሳዑዲ አረቢያ በተቀናቃኝ ጎራ ተሰልፈው እየተፋለሙ ያሉትን የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉን ተወካዮች ቅዳሜ ሚያዝያ 28/2015 ዓ.ም. ተቀብላ እያስተናገደች ነው።
በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል “የቅድመ ድርድር ንግግር” በጅዳ መጀመሩን አስመልክቶ አሜሪካ እና ሳዑዲ ባወጡት የጋራ መግለጫ በጎ ጅማሬ ነው ብለውታል።












