የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በሳዑዲ አረቢያ ንግግር ሊያደርጉ ነው

በካርቱም ያለው ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በርካታ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ላይ ደርሰው ያፈረሱት የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በሳዑዲ አረቢያ የፊት ለፊት ንግግር ሊያደርጉ ነው።

በዚህም ሳዑዲ አረቢያ በተቀናቃኝ ጎራ ተሰልፈው እየተፋለሙ ያሉትን የሱዳን ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉን ተወካዮች ቅዳሜ ሚያዝያ 28፣ 2015 ዓ.ም ተቀብላ ታስተናግዳለች።

በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል “የቅድመ ድርድር ንግግር” በጅዳ መጀመሩን አስመልክቶ አሜሪካና ሳዑዲ ባወጡት የጋራ መግለጫ በጎ ጅማሬ ነው ብለውታል።

ሆኖም ትናንት ሚያዝያ 27 2015 ዓ.ም በካርቱም ግጭቶች ስለመቀጠላቸው ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የሱዳን ጦር ስለ ውይይቱ ሰብዓዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ቢያስታውቅም ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኩል ይፋዊ አስተያየት አልተሰጠም።

የሱዳን ጦር በዚህ ንግግር ላይ የሚሳተፉ ልዑካን መላኩን አረጋግጧል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች በሱዳን ጦርነት ያስከተለው ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ እልባት እንዲያገኝ ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ።

ለሦስት ሳምንታት ያህል በቀጠለው ከባድ ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ወደ 450 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎችም ቀያቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።

ከነዚህም ውስጥ ከ115 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት ሃገራት እንደተሰደዱም ከተመድ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የሚሊዮኖች ሕይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል ሁለት ጄኔራሎች በባላንጣነት በጽንፍ ስፍራ ተቀምጠዋል።

የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥና አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉት አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ጋር በመረረ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል።

የአሜሪካ እና የሳዑዲ አረቢያ መንግሥታት “ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ለአገሪቷ እና ለሱዳን ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ግጭቱን ለማስቆም በሚደረገው ውይይት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ፤ ይህም ሁኔታ ለተቸገረው ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የሚያረጋግጥና የሱዳንን ሕዝብ ስቃይና መከራ የሚታደግ መሆኑን” አሳስበዋል።

የሁለቱ መንግሥታት የጋራ መግለጫ ሁሉንም የሱዳን አካላትን ያሳተፈ የድርድር ሂደት በቅርቡ እንደሚጀመርም ተስፋውን አስፍሯል።

የዩኒሴፍ ቃለ አቀባይ ጄምስ ኤልደር በሱዳን ግጭት የመጀመሪያዎቹ 11 ቀናት ብቻ 190 የሚገመቱ ሕጻናት ሲገደሉ 1 ሺህ 700 መቶ መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

ይህ አኃዝ በካርቱም እና በዳርፉር ከሚገኙ የጤና ማዕከላት የተገኘ ሲሆን “ዕውነታው ከዚህም በጣም የከፋ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

የጦርነቱ መባባስ እርዳታ እንዳይደርስም እክል ፈጥሯል። በዳርፉር የዘር ፍጅትን ባስከተለው ጦርነት የአረብ ሚሊሻን ሲመሩ የነበሩት ጄነራል ቡርሃን እና ጄነራል ሄምቲ ግጭቱን በሰላም ለመቋጨት ያላቸው ዝግጁነት አናሳ ነው ተብሏል።