ተቀናቃኞቹ የሱዳን ጄኔራሎች ውጊያውን ለማቆም ፍላጎት የላቸውም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የበላይነትን ለመያዝ ባላቸው ፍላጎት የተነሳ ሦስት ሳምንቱን ሊይዝ የተቃረበውን ውጊያው ለማብቃት አስቸጋሪ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናገሩ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በቀይ ባሕር ዳርቻ የምትገኘውን የወደብ ከተማ ፖርት ሱዳንን ከጎበኙ በኋላ እንደተናገሩት፣ ተዋጊ ኃይሎቹ በግጭቱ ለመቀጠል ባላቸው ፍላጎት የተነሳ ግጭቱን ለማስቆም አስቸጋሪ ሆኗል።
“አገር አቀፍ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ለማድረግ የተደረጉት ሁሉም ጥረቶች፣ በተዋጊ ኃይሎቹ መካከል በግጭቱ ለመቀጠል ባላቸው ግትር ፍላጎት የተነሳ እንቅፋት ገጥሞታል” ብለዋል ግሪፊትስ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የእርዳታ ከፍተኛ ባለሥልጣኑ በሱዳን ውስጥ ያለው ቀውስ እየተስፋፋ ያለበት ፍጥነት “በጣም፣ በጣም በእጅጉ የሚያሳስብ ነው ብለዋል።
የሱዳን ቀውስ ያሳሰባቸው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከቀናት በፊት ወደ ኬንያ በመጡበት ጊዜ ግጭቱ ወደ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ከመሻጋገሩ በፊት ተዋጊዎቹ ጄኔራሎች በአስቸኳይ ግጭቱን እንዲያቆሙ ጥሪ ቢያቀርቡም ሰሚ ያገኙ አይመስሉም።
ሰብአዊ እርዳታ በአስቸኳይ በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ ከተፋላሚዎቹ ጄኔራሎች ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ጠይቀው የነበሩት ማርቲን ግሪፊትስ፣ ሁለቱም ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ መርሆዎችን እንደሚያከብሩ ቢናገሩም፣ ግጭቱን ለማቆም ግን ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም ብለዋል።
ከሦስት ሳምንት በፊት ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ከ500 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እንዲሁም ከ100 ሺህ የሚልቁ ሱዳናውያን አገራቸውን ለቀው ሲሰደዱ፣ ከ300,00 በላይ የሚሆኑ ደግሞ እዚያው ሱዳን ውስጥ ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ከዚህም በኋላ ከ800 መቶ ሺህ በላይ ሱዳናውያን ሊሰደዱ ይችላሉ በሚል እራሱን እያዘጋጀ ነው። እነሱንም ከቀጣይ አምስት ወራት ለመርዳት 450 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚያስፈልገውም አሳውቋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁለቱ ወገኖች ንግግር ጀምረው ግጭቱ የሚያበቃበትን መንገድ እንዲፈልጉ ቢወተውቱም ተቀባይነት አላገኙም።
የጦር ሠራዊቱ አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሐን፣ ከሥልጣን ሊገለብጠኝ ነው ካሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጄኔራል አህመድ ዳጋሎ ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ፍላጎት እንደሌላቸው መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ነገር ግን የተኩስ አቁም እንዲደረግ በአሜሪካ እና በበሳዑዲ አረቢያ አሸማጋይነት የሚደረገውን ጥረት እንደሚቀበሉ፣ ንግግር የሚደረግም ከሆነ በአቀራራቢዎቹ አማካይነት ብቻ እንደሚሆን ተገልጿል።
ሁለቱም ወገኖች ንግግር ከመጀመሩ በፊት ተቀናቃኛቸውን ማዳከም እና ይዞታቸውን በማስፋት ላይ በማተኮር ውጊያ እያደረጉ ነው።
ፈጥኖ ደራሹ ኃይል አብዛኛውን የካርቱም ክፍልን የተቆጣጠረ በመሆኑ በጎዳናዎቿ ላይ አንድም የጦሩ ወታደር ወይም ፖሊስ አይታይም። በዚህም ሳቢያ በከተማዋ ውስጥ ሠራዊቱ የአየር ጥቃቶችን እየፈጸመ መሆኑ ተዘግቧል።
የዐይን እማኞች እንዳሉት በካርቱም ጎዳናዎች ላይ ከባድ ፍንዳታዎች እና ተኩስ እየተሰማ ነው። የዋና ከተማዋ አዋሳኝ በሆኑት ኦምዱርማን እና ባህሪ ከተሞች ውስጥ የከባድ መሳሪያ እና የቦምብ ፍንዳታዎች እንደነበሩ ተዘግቧል።
የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አባላት ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል ማረክናቸው ያሏቸውን ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን እና የጦር መሳሪያዎችን ፎቶግራፎች እያጋሩ ነው።
በሱዳን ውስጥ ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም. በአገሪቱ ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ ለመሠረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት እና ከአገሪቱ መውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች እድል ለመፍጠር እስካሁን ለሦስት ጊዜ በቅጡ ያልተተገበሩ የተኩስ አቁም ታውጆ ነበር።
የመጀመሪያዎቹ ሁለት የተኩስ አቁሞች ለሦስት ቀናት እንዲሁም አሁንም “ተግባራዊ እየሆነ ያለው” ደግሞ ለሰባት ቀናት ይቆያል የተባለ ቢሆንም፣ ዋና ከተማዋ ካርቱምን ጨምሮ ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ ናቸው።
ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር በምትመለስበት እና አንድ መቶ ሺህ የሚሆኑት የሰለጠኑ አባላት ያሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ አገሪቱ ሠራዊት በሚካተትበት ዕቅድ ላይ በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ነበር ወደ ውጊያ የገቡት።
ሁለቱ ጄኔራሎች ከኦማር ሐሰን አልበሽር ከሥልጣን መውረድ በኋላ የተቋቋመውን የሽግግር አስተዳደር በመፈንቅለ መንግሥት በማስወገድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የነበረውን ዕቅድ ሲያዘገዩት ቆይተዋል።
ለዚህም ምክንያቱ ጄኔራሎቹ እና ደጋፊዎቻቸው ከመሪነት መንበሩ ከተነሱ ከ20 ዓመት በፊት ዳርፉር ውስጥ ከተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተጠያቂ እንሆናለን የሚል ስጋት ስላላቸው እንደሆነ ይነገራል።












