“ወደ ግብፅ ለመሻገር ለአውቶብስ 40 ሺህ ዶላር እየተጠየቅን ነው” ከሱዳን የወጡ ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, SAY ATABAN/BBC
ሱዳንን ጥለው የተሰደዱ የቤተሰብ አባላት በሱዳን እና በግብፅ ድንበር ላይ እነሱን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እንደሚገኝ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ስደተኞቹ ወደ ግብጽ ለመሻገር ለአውቶብስ ኪራይ እስከ 40 ሺህ ዶላር መጠየቃቸውንም ተናግረዋል።
ድንበሩን ለማቋረጥ በአውቶብስ መጓዝ የሚችሉትም ልዩ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ብቻ ሲሆኑ፣ በእግር ድንበር ማቋረጥም ተከልክሏል።
ከ10 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ሕጻናትን ጨምሮ ሰባት የቤተሰብ አባላት በዋና መዲናዋ ካርቱም ከሚካሄደው ውጊያ መሸሽ የቻሉት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር።
ፋዲ አታባኒ እንደሚለው የ88 ዓመት ዕድሜ ያላትን ሴት ጨምሮ ቤተሰቦቹ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።
በዋዲ ሃልፋ ከተማ የሚገኘው አታባኒ “እዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ምንም ዓይነት ማረፊያ የለም። ሰዎች ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የሚተኙት” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
አብዛኞቹ ቤተሰቦችም የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት ያላቸው መሆናቸውን የገለጸው አታባኒ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት እንዲረዷቸው ተማፅኗል።
“በረሃ ውስጥ ነው ያለነው።ለልጆቼ ጤና ዋስትና መስጠት አልችልም። በመሆኑም የብሪታኒያ መንግሥት ከዚህ እንድንወጣ ድንበሩን በአውቶብስ ለማቋረጥ እንዲረዳኝ እፈልጋለሁ።” ብሏል።
አታባኒ የአካባቢው አሽከርካሪዎች መንገደኞች የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለትርፍ እየተጠቀሙበት ነው ሲልም ከሷል።
“በመደበኛ ቀን አውቶብስ ለመከራየት የሚከፈለው 3 ሺህ ዶላር ነበር። አሁን ግን 30 ኪሎ ሜትርን አቋርጦ ድንበር ላይ ለመድረስ ሰዎች 40 ሺህ ዶላር እየከፈሉ ነው። ባንኮች ዝግ ናቸው። የኤቲኤም ማሽኖች አይሰሩም። ይህን ያህል ገንዘብ ማን ይኖረዋል?” ሲልም የ53 ዓመቱ አታባኒ ይጠይቃል።
የካርቱም ነዋሪዋ ሆስናም በሱዳን መዲና መውጫ አጥተው የቀሩ ሁለት ልጆች እንዳሏት እና ወደ ድንበር ለመድረስ እያንዳንዳቸው 400 ዶላር እንደተጠየቁ ተናግራለች። ሆስና እንደምትለው ግጭቱ ከመቀስቀሱ በፊት ለዚህ ጉዞ ይከፈል የነበረው ለአንድ ሰው 25 ዶላር አካባቢ ነበር።
ሆስና ወደ ግብፅ ድንበር የደረሰችው ግጭቱ ከመቀስቀሱ በፊት ነው።
“ሴት ልጆቼ በሠፈራችን ላይ የወደቀ የጥይት አረር አይተዋል። እዚህ ላመጣቸው አልቻልኩም። እነሱን የሚረዳልኝ ባልም ሆነ ወንድ ልጅ የለኝም። ገንዘብ ለመቆጠብ ጠዋት ማታ ያለ እረፍት እየሰራሁ ነው” ብላለች።
ሆስና ገንዘብ ለማግኘት የስደተኞች መናኻሪያ በሆነው እና አስዋን አቅራቢያ በሚገኘው የአውቶብስ ማቆሚያ አካባቢ በሚገኝ ሻይ ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት እየሠራች ነው።
“ሱዳን ሙሉ በሙሉ ወድማለች።ተዋጊዎች በየቤታቸው ያሉ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ እያደረጉ ነው” ትላለች።
በድንበር አቅራቢያ ያሉትን ሰዎች ለመርዳት ወደ አስዋን ያቀናችው ሱዳናዊ አሜሪካዊቷ ኢስራ ባኒም የአውቶብስ ክፍያ በብዙ እጥፍ ጨምሯል ብላለች።
“ሰዎች አካባቢውን ለቀው የወጡት በራሳቸው ወጪ ነው። ክብር ተነፍገዋል። በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ነው ያለው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ከ15 ቀናት በፊት በሱዳን መደበኛ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩት በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ሰኞ ዕለት የሦስት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ይህም ለተጨማሪ ሦስት ቀናት እንዲራዘም መስማማታቸውን ሐሙስ ዕለት አስታውቀዋል።
ውጊያው 10 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚኖርበት በሚገመተው በዋና ከተማዋ ካርቱም እና አካባቢዋ የተባባሰ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ያለምግብ፣ ውሃ እና ነዳጅ አቅርቦት ቀርተዋል።
ቤተሰቦቹን ይዞ የተሰደደው አታባኒ የተወሰኑ አልባሳትን ብቻ ይዞ ቤቱን ጥሎ እንደወጣ ይናገራል።
“ካርቱምን ጥዬ የወጣሁት ከቤቴ ውስጥ የረባ ነገር ሳልይዝ ነው። ቤቴስ እስካሁን ይኖር እሆን? ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። የቻልነውን ነው አንጠልጥለን የወጣነው” ብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚገኙ ቤተሰቦች የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን እርዳታ ለማግኘት ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረትም ፍሬ አላፈራም።
የዩኬ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ካርቱም አቅራቢያ ከሚገኘው ዋዲ ሴዲና አየር ማረፊያ መውጣት እንደሚችሉ ባለሥልጣናት እንደተነገራቸው ገልጸዋል።ይህም ካሉበት የሁለት ቀን የአውቶብስ ጉዞ ይርቃል።
በራሳችሁ ኃላፊነት ወደ አየር ማረፊያው ሂዱ እንደተባሉ የሚናገረው አታባኒ፣ “ለምን ቤተሰቤን አደጋ ላይ እጥላለሁ?” ሲልም ይጠይቃል።
ሐሙስ ዕለት ቱርክ ዜጎቿን ለማስወጣት ወደ ዋዲ ሴዲና ያመራው አውሮፕላን እንደተተኮሰበት አስታውቃለች።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለቢቢሲ በላከው መግለጫ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ አንስቶ ውስብስብ እና አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ዜጎችን ለማውጣት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
“በሱዳን የሚገኙ ዜጎቻችን ጉዳይ ቅድሚያ የምንሰጠው ነው። መውጣት የሚፈልጉም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ማውጫ ማዕከል በሚችሉት ፍጥነት እንዲጓዙ እናሳስባለን። ወደ አየር ማረፊያው ለመጓዝ የሚያስችል ምንም አይነት እርዳታ ግን ማዘጋጀት አልቻልንም” ብሏል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሐሙስ ምሽት ላይ 897 ሰዎች ከዋዲ ሴዲና አየር ማረፊያ እንዲወጡ ማድረጉን ገልጾ ነበር።
ሆኖም ቢቢሲ ያነጋገረው እና በቀይ ባሕር የሱዳን ወደብ በኩል የወጣው የዩኬ ዜግነት ያለው ሱዳናዊ ዶክተር፣ በርካታ የብሪታኒያ ዜግነት ያላቸው ሱዳናውያን ከሱዳን ወደብ ለቀው ለመውጣት እየተጠባበቁ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ዜጎችን የሚያስወጣ ምንም በረራ አልተደረገም ብሏል።












