የሱዳን ግጭት ሊያመራ የሚችልባቸው ሦስት አማራጮች

ሄሊኮፍተር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሱዳን ጉዳይ ተንታኞች በአገሪቱ የተቀስቀሰው ግጭት ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ትንታኔያቸውን ሰጥተዋል።

እንደ ባለሙያዎቹ ትንተና ከሆነ የሱዳን ግጭት ሦስት መልክ ሊይዝ ይችላል።

1. ወታደራዊ ድል

ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች ያሰቡትን በኃይል ያሳካሉ ብሎ መገመት ከባድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አንዱ ሌላኛውን አሸንፎ ስልጣን ሊይዝ የሚችልበት እድልም ጠባብ መሆኑን የሚናገሩት ተንታኞች አጋጣሚው ሊኖር ይችላል ይላሉ።

የአገሪቱን መደበኛ ጦር የሚመሩት ጀነራል አብደለ ፋታህ አል-ቡርሃንም ሆኑ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መሪ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ግጭቱን ማሸነፍ የሚያስችላቸው ዕድል ስላለ አሁን ላይ አንዱ አሸናፊ፤ ሌላኛውን ተሸናፊ አድርጎ መሳል ከባድ ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ በካርቱም ያሉ አስተያየት ሰጪዎች የሄሜቲ ጦር ከመደበኛ ሠራዊቱ በላይ በመዲናዋ የበላይትን የያዘ ይመስላል ይላሉ።

የሄሜቲ ጦር በሽምቅ ውጊያ የተካነ ነው። ሄሜቲ በአውደ ውጊያዎች ባህሪውን እየቀያየረ ሊዋጋ የሚችል ሠረዊት አላቸው። ይህ ባህሪያቸው በካርቱም መዲና በሚደረጉት ውጊያዎች የበላይነት እንዲይዙ ሳያስችላቸው አይቀርም።

በተቃራኒው የአገሪቱ ጦር ደግሞ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በላይ የጦር መሳሪያ አቅርቦት አለው። ታንኮች፣ ከባድ ጦር መሳሪያዎች እና የአየር ላይ የበላይነት ያለው በ አል ቡርሃን እጅ ነው።

የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ባልደረባ የሆኑት አለን ቦስዌል በመዲናዋ ካርቱም የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላቱ የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ቤትን እየበረበሩ መኖሪያቸው እያደረጉት ነው ይላሉ።

ይህ አካሄድ የአገሪቱ ጦር ከተማዋን እንዲያፈርስ የሚያደርግ ነው ይላሉ። ተንታኙ ሁለቱ ጀነራሎች በወታደራዊ አማራጭ ድል ማድረግ እንደሚችሉ ማመናቸውን ከቀጠሉ በሱዳን ላይ ሊያደርስ የሚችለው ውድመት እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

2. የተራዘመ ግጭት

ይህ ግጭት የተለያዩ መልኮችን ይዞ ተራዝሞ ሊዘልቅ ይችላል። ለዚህ ደግሞ ቁጥር አንድ ተጎጂው ሱዳናውያን ናቸው።

ሱዳናዊው ሞሐናድ ሃሺም ይህ ግጭት ወደ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀይሮ እንዲራዘም ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ ይላሉ።

እስላማዊ አጀንዳ የሚያራምዱ የቀድሞ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር እና ፓርቲያቸው ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦች ተገልለው ቆይተዋል።

አል-በሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በሱዳን የተከሰተው የጸጥታ ከፍተት የተለያዩ አጀንዳ ያላቸው ሚሊሻዎች እና እስላማዊ አጀንዳዎች እንዲጨምሩ ሊያደርግ ይችላል ይላሉ።

በሱዳን ጉዳይ ተንታኝ የሆኑት ጆናስ ሆርነር ደግሞ ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች ከውጪ ኃይሎች ድጋፍ የሚጠይቁ ከሆነ ግጭቱን ሊያራዝም ከሚችሉ ምክንያቶች አንዱ ነው ይላሉ።

የግብጽ ባለስልጣናት በሱዳን ጉዳይ ገለልተኛ አቋም ነው የምናራምደው ይበሉ እንጂ ካይሮ የአል ቡርሃን ጠንካራ ደጋፊ ናት።

ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፣ የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር እና ሌሎች በቀጠናው ኃይል ያላቸው ሚሊሻዎች ድጋፍ እንዳለው ይታመናል።

ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ጀነራሎች አለመግባባታቸውን የብሔር መልክ በማስያዝ ግጭቱን የሱዳናውያን ሊያደርጉት ይችላሉ።

“ግጭቱ ከመቀስቀሱ በፊት ሄሜቲም ሆኑ ጀነራል ቡርሃን ወደ ትውልድ ቀያቸው እየሄዱ ከፋፋይ የሆነ ንግግር ሲያደርጉ ተመልክተናል” ይላሉ ሃሺም።

3. የሰላም ስምምነት

አረብ አገራትን ጨምሮ በቀጠናው ያሉ መንግሥታት እና ምዕራባውያን ሁለቱ የጦር ጀነራሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ለማደራደር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ግጭቱን በኃይል ማሸነፍ እንደሚችሉ የሚያምኑት ሁለቱ የሱዳን ጀነራሎች ግን የድርድር ጥያቄ የሚቀበሉ አይመስልም።

ከትናንት በስቲያ የተባበሩት መንግሥታት የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቮልከር ፐርዝስ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በዘላቂነት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ለድርድር የመቀመጥ ፍላጎት የላቸውም ሲሉ ተናግረው ነበር።

በሱዳን በድርድር ልዩነቶችን መፍታት አስቸጋሪ የሚያደርገው የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ቁጥር ብዙ መሆኑ ነው።

በቀጠናው ያሉ አገራትም ሱዳንን እንዲመራ የሚፈልጉት ግለሰብ የተለያየ ነው። ይህ ደግሞ ለሱዳናውያን ጥሩ ዜና አይደለም ይላሉ ሆርነር።

“አሁንም ቢሆን ለሰላም ድርድር ጊዜ አለ። ችግሩ ግን በሁለቱም ወገኖች መካከል ግጭት የማብረድ ፍላጎት ፈጽሞ አለመኖሩ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ጊዜያዊ የሆኑት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም የጀነራሎቹ ፍላጎት ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው”

የእነዚህ ሁለቱ ግለሰቦች ፍላጎተ የግል እንጂ የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት አይደለም። ግጭቱ የተነሳው የስልጣን ጥምን ለማርካት፣ የኃይል ፍላጎትን እውን ለማድረግ እና ሃብት ለማጋበስ እንጂ የሕዝብ ፍላጎትን አስቀድሞ የተጀመረ አይደለም።

ለዚህም ከፍያው ቀላል አይሆንም። ለሁለቱ ኃያላን ጀነራሎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ የሚሆኑት የሱዳን ሕዝብ ነው።