የሱዳን ቀውስ ከሶሪያ እና ከሊቢያ ሊከፋ እንደሚችል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቀድሞው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ሐምዶክ በአገራቸው የተከሰተው ግጭት ከሶሪያ እና ከሊቢያ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስጠነቀቁ።
ውጊያው የሚቀጥል ከሆነም “ዓለምን የሚያስጨንቅ ቅዠት” ሊሆን ይችላል ብለዋል አብዳላ ሐምዶክ።
በተፋላሚዎቹ ጄኔራሎች መካከል እንዲራዘም ከስምምነት የተደረሰው የተኩስ አቁም በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች እየተጣሰ መሆኑ ተነግሯል።
ሁለት ሳምንት የሆነው ውጊያ አስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ አስር ሺዎችን ደግሞ ከአገራቸው እንዲሰደዱ አድርጓል።
ለሦስት ቀናት የቆየው የተኩስ አቁም ሐሙስ ዕለት ለተጨማሪ ቀናት እንዲራዘም የተደረገው በሱዳን ጎረቤት አገራት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነው።
ነገር ግን ለ72 ሰዓታት የተራዘመው የተኩስ አቁም እየተከበረ እንዳልሆነ ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው። በአንዳንድ የካርቱም አካባቢዎች የአየር፣ የታንክ እና የመድፍ ጥቃቶች ቀጥለዋል ተብሏል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ በኬንያ ዋና ከተማ በተካሄደ ጉባኤ ላይ ሁለቱን ተቀናቃኝ ጄኔራሎች ወደ ሰላም ንግግር ለማምጣት የተባበረ ዓለም አቀፍ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
“ሱዳን የተለያዩ ሕዝቦች ያሉባት ግዙፍ አገር ናት...ግጭቱ ዓለምን እንቅልፍ የሚነሳ ቅዠት ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ” ሲሉም ተናግረዋል ሐምዶክ።
“ይህ በአገሪቱ ሠራዊት እና በትንሽ አማጺ ቡድን መካከል የሚካሄድ ጦርነት አይደለም። በደንብ በሰለጠኑ እና በታጠቁ ሁለት ሠራዊቶች መካከል የሚካሄድ አይነት ጦርነት ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK
አሁን ውጊያ በገጠሙት ጄኔራሎች በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከመወገዳቸው በፊት ለሁለት ዓመት ያህል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገሪቱን የመሩት አብዳላ ሐምዶክ፣ በሱዳን የተከሰተው ቀውስ በሶሪያ እና በሊቢያ ካጋጠመው የእርስ በርስ ጦርነት የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ለዓመታት በሶሪያ እና በሊቢያ በተካሄዱት ደም አፋሳሽ ጦርነቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሚሊዮኖች ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል። በተጨማሪም በዙሪያቸው ባሉ አገራት ውስጥም አለመረጋጋትን አስከትለዋል።
በአገሪቱ ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን የሥልጣን ፉክክር ተከትሎ ነበር ወታደራዊ ግጭቱ ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው።
አሁን ለተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያቱ አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር በምትመለስበት እና አንድ መቶ ሺህ የሚሆኑት የሰለጠኑ አባላት ያሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ አገሪቱ ሠራዊት በሚካተትበት ዕቅድ ላይ በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ነው።
ከ20 ዓመት በፊት ዳርፉር ውስጥ ከተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ደጋፊዎቻቸው በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተፈላጊ በመሆናቸው ሁለቱም ጄኔራሎች በሱዳን መንግሥት ውስጥ ያላቸውን ሥልጣን ማጣት በእጅጉ ያስፈራቸዋል።
በውጊያው ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የካርቱም ነዋሪዎች በምግብ፣ በውሃ እና በነዳጅ ችግር እየተሰቃዩ ይገኛሉ።
ከዋና ከተማዋ ባሻገር በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በተለይ በዳርፉር ውስጥ የሚሊሻ ቡድኖች የገበያ ስፍራዎችን በመዝረፍ በእሳት ማጋየታቸው ተዘግቧል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄኔራል ሔሜቲ የተኩስ አቁሙ ከተራዘመ በኋላ በተዋጊዎቻቸው ላይ “ያልተቋረጠ” ጥቃት እየተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጦርነቱ አስካላበቃ ድረስ ድርድር እንደማይኖር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሱዳንን ማውደም አንፍልግም” ያሉት ሔሜቲ፣ ለጦርነቱ ተቀናቃኛቸውን የሠራዊቱን ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐንን ተጠያቂ አድርገዋል።
ጄኔራል አልቡርሐን በጊዜያዊነት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከሔሜቲ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወቃል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን ባገኙት የመጓጓዣ ዘዴ ሁሉ በመጠቀም ከጦርነቱ ለመሸሽ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሱዳን ጉረቤት አገራት እየተሰደዱ ነው።
ከሱዳናውያን በተጨማሪ የተለያዩ አገራት የተራዘመውን የተኩስ አቁም ጊዜ በመጠቀም ዜጎቻቸውን በየብስ፣ በባሕር እና በአየር ከአገሪቱ ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ነው።












